Book Cover
Book Cover

(ዋዜማ ራዲዮ)- መልከኛ የሚባል ዓይነት ነው። ሲመለከቱትም ሆነ ሲያወሩት ቅልል ያለ። ዕድሜው ሃምሳዎቹ ውስጥ።  ጥቁር እና ገብስማ የተቀላቀለቀበትፀጉሩ ሰውየው የተሻገራቸውን መንግስታት ብዛት ለተመልካች አስቀድመው የሚያውጁ ዓይነት። ስለ መንግስታቱ እና በአገዛዝ ዘመናቸውስለነበረው ኩነት ያለው አተያይም ድብቅ አይደለም። በቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥኑት ከአንድም ሶስት መፅሐፍቱ ሰውየው አጥብቆ የሚወደውን ነገር አደባባይ ያወጡ ናቸው።

በመምህርነት በሰራበት ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ያገለገለ ቢሆንም ለእርሱ ተመራጭ እና ተወዳጅ አጀንዳ አንድ ነው፡፡ ፖለቲካ ። ሊያውም የኢትዮጵያ ፖለቲካ፡፡ ፖለቲካ በቡና ሰዓት እንኳ አይነጠለውም፡፡ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህርሆኖ በሚሰራበት መቀሌ ዩኒቨርስቲ አዲ ሀቂ ካምፓስ መግቢያ ፊት የምትገኝ እና አዘውትሮ የማይጠፋባት “ምድረ ገነት” ግሮሰሪ ለዚህ ሁነኛ ምስክር ነች፡፡ እግር ጥሎት ወደ ግሮሰሪዋ ዘው ያለ ሰውየውን ወይ ጠዋት ከስራ በፊት አሊያም ከሰዓት ከማሰተማር መልስ ከባልደረቦቹ ጋር በጦፈ የፖለቲካ ክርክር ተውጦ ሊያገኘው ይችላል፡፡

[ዘገባውን በድምፅ ለመስማት እነሆ- አንተነህ ኪዳኔ ያሰናዳውን መዝገቡ ሀይሉ ያቀርበዋል]

የሚያውቁት እንደሚመሰክሩለት ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካ ያለው ግንዛቤ እና ንባብ ጥልቅ ነው።  የፖለቲካ ዕውቀቱን ያስመሰከረው ለንባብባበቃቸው ልቦለዶች ብቻ አይደለም። ይልቅስ ብዙ ማገላበጥ እና ማጣቀስ በሚጠይቀው የአካዳሚያዊ ምርምር ስራዎች አሳይቷል።ከግብፅ እስከ ጋና፣ ከአልጄሪያ እስከ ደቡብ አፍሪካ በተጋበዘባቸው መድረኮች የምርምር ስራዎቹን አቅርቧል። ፖለቲካን በጽሁፍ፣ በማስተማር እና በመድረክ ብቻ አይደለም የሚያውቀው፡፡ ኖሮበታል፡፡ ወደ ዩኒቨርስቲ መምህርነት ከመምጣቱ በፊት በከፍተኛየመንግሥት መዋቅሮች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ሰርቷል፡፡

ሀብታሙ አለባቸው ይባላል፡፡ በሁለት ዓመታት ውስጥ “አውሮራ”፣“የቄሳር እንባ” እና  “የሱፍ አበባ” የተሰኙ ረጅም ልብወለዶችን ለአንባቢያን ያደረሰ ጸሀፊ ነው፡፡ የመጽሐፍቱ ጭብጥ የተለያየ ቢሆንም በዘውግ ግን ይመሳሰላሉ፡፡ በታሪካዊ ቀመስ ልብወለድ ዘውግ ውስጥ የሚካተቱት መጽሀፍቶቹ እውነተኛ ሁነቶችን እና በእውን የነበሩ ግለሰቦችን በታሪክ ማዋቀሪያነት እና በገጸ-ባህሪያትነት ይጠቀማሉ፡፡ የዋና ገጸ-ባህሪያቱ አጣብቂኝ የፍቅር ታሪክ በሶስቱም መጽሐፍት እንደ “አዋዜ” አገልግሏል፡፡

“አውሮራ” የተሰኘው የጸሀፊው የበኩር ድርሰት ኤርትራ እንደ ሀገር ዕውቁኝ ካለችበት ጊዜ አንስቶ ከኢትዮጵያ ጋር ስለነበራት ቅጣ አልባ ግንኙነት እና ተከትሎ ስለመጣው መዘዝ ይተርካል፡፡ “ነፋስ አያስገባም” የተባለለት የሁለቱ ሀገር መሪዎች “ፍቅር” እንዴት ወደ ጦር መማዘዝ ሊደርስ እንደቻለ በእውን የተከሰቱ መንስኤዎች እና ሁነቶች ላይ ተንተርሶ የጦርነቱን መነሻ እና መድረሻ ይተነትናል፡፡ ደራሲው የድንበር ጦርነቱ ግም ሲል አስመራ እና ነዋሪዎቿ ምን ይመስሉ እንደነበር ምስል ከሳች በሆኑ ገለጻዎቹ ጥሩ አድርጎ ከትቦታል፡፡

ሀብታሙ የኤርትራ ብሔራዊ ማንነት ጽንስ እና ውልደት፣ ነጻ ሀገር ለመሆን ስለተደረገው ትግል፣ ሻዕቢያ ወደ ስልጣን ከዓመታት በኋላ በባለስልጣናቱ መካከል ተከስቶ ስለነበረው የፖለቲካ ፍጭት ለልብወለድ በሚስማማ መልኩ አሳጥሮ፣ ፍሬ ነገሩን ጨምቆ በማይሰለች መልኩ ያስነብባል፡፡ “ርዕሰ ብሔር” እያለ በወል ስም የሚጠራቸውን የኢሳይያስ አፈወርቂን በር በቀጥታም በተዘዋዋሪም ያንኳኳል፡፡ “ኢሳይያስ አምባገነን እየሆነ ነው፡፡ አንድ ሊባል ይገባዋል” የሚል አቋም በማራመዳቸው በኋላ ደብዛቸው ስለጠፋ የሻዕቢያ ከፍተኛ አመራሮች እና የእነርሱን አመለካከት ይጋሩ ስለነበሩ ባለስልጣናት እና ታጋዮች የፍትህ ሚኒስትር ተደርገው በተሳሉት ገጸ-ባህርይ አማካኝነት አተያያቸውን ያጋራል፡፡

 የርዕሰ ብሔሩን ቀጥተኛ ተልዕኮ ለማስፈጸም ከኤርትራ፣ ሊቢያ፣ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ እንደ ቢራቢሮ የምትዘለው ዋና ገጸ-ባህሪ ፍልየቲ ኤርትራ በወቅቱ ገብታበት የነበረበትን አጣብቂኝ ትወክላለች፡፡ በርሃ ተወልደው በርሃ ካደጉት እና “ቀይህ እምባባ” (ቀያይ አበቦች) ተብለው ከሚጠሩት ወጣቶች መካከል የምትመደበው ፍልየቲ የሀገሯን ተልዕኮ ባመስፈጸም፣ የኢሳይያስ ተቺ በሆኑት የፍትህ ሚኒስትር አባቷ ሁኔታ እና አስመራ በሚኖረው ኢትዮጵያዊ ፍቅረኛዋ ዕጣ ፈንታ ላይ አቋም ለመያዝ ተቸግራ ስትዋልል ትታያለች፡፡ በፍልየቲ ፍቅረኛ አስራደ በኩል በኤርትራ ይሰሩ እና ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በወቅቱ  የነበሩበት ሁኔታ እና ይደርስባቸው የነበረው በደል በጨረፍታም ቢሆን ተነክቷል፡፡

ከድንበር ወዲህ እና ወዲያ ማዶ ያሉ ህዝቦች ያን መራራ የጦርነት ጊዜ እንዴት እንዳሳለፉትም በመጽሐፉ ተዳስሷል፡፡ እንደመጀመሪያ መጽሐፍ በገበያው ዘንድ “ጥሩ ተቀባይነት አግኝቷል” የተባለለት “አውሮራ” ከመጽሐፉ አሳታሚ በተገኘ መረጃ መሰረት እስካሁን ድረስ 15 ሺህ ያህል ቅጂዎች ተሽጧል፡፡

የ“አውሮራ”ን የጽሁፍ ረቂቅ ካነበቡ በኋላ አስተያየታቸውን ከሰጡ ዲፕሎማት እንደተቀነጨበ የተገለጸው እና በመጽሐፉ ጀርባ የታተመ ጥቅስ የሀብታሙን በመረጃ የተደገፈ እና ወደ እውነታ የተጠጋ አጻጻፍ ይትባሃል ለአንባቢያን የሚሰጠውን ትርጉም በግልጽ ያሳየ ነው፡፡ “ይህ መጽሐፍ ልቦለድ ነው ቢሉኝ እንዴት አምናለሁ?” ይላሉ ዲፕሎማቱ “የተኖረን ሕይወት እየተረኩ ‘ልቦለድ’ ብሎ ነገር አለ እንዴ?” ሲሉ ገረሜታቸውን በጥያቄ መልክ ያስቀምጣሉ፡፡

ዲፕሎማቱ በአድናቆት ያነሱት በመጽሐፉ ውስጥ ያለው የእውነታ እና ልቦለድ መስመር መድብዘዝ ግን ለሀያሲዎች ምቾት አልሰጣቸውም፡፡ በጋዜጦች እና መጽሐቶች ላይ የሰላ ትችቶችን በማቅረብ የሚታወቅ አንድ ሀያሲ የሀብታሙ መጽሐፍት ለእኛ ሀገር አንባቢያን አደናጋሪ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ “አንባቢያን ልቦለድ መሆኑን ትተውት እንደ እውነተኛ ታሪክ ነው የወሰዱት” ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመጽሐፉ ሽፋን አሊያም መግቢያ ላይ ታሪካዊ ልቦለድ መሆኑ አለመገለጹ የራሱን አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይናገራል፡፡

የሀብታሙ የአጻጻፍ ዘይቤ ለአንባቢያን መደናገር ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ሀያሲው ያስረዳል፡፡ ደራሲው በሶስቱም መጽሀፍቱ አጠር አጠር ያሉ አረፍተ ነገሮች፣ አንቀጾችን እና ንግግሮችን የተጠቀመ ሲሆን ገለጻዎቹም የማይሰለቹ እና ፍሰት ያላቸው ናቸው፡፡ ጠጣር የሚባሉ ፖለቲካዊ ርዕዮቶችን እንኳ ሲያነሳ ለንባብ ቀለል እንዲሉ አድርጎ ነው፡፡ ልብ ለመስቀል እና ለጡዘት የሚጠቀምባቸው ቴክኒኮችም የአንባቢያንን ቀልብ የሚይዙ ናቸው፡፡

በሀያሲው እይታ ግን የሀብታሙ አጻጻፍ “ዘገባዊ” እና ጥበባዊ ለዛው “ደከም ያለ” ነው፡፡ “የትኛውም ፖለቲካዊ መጽሐፍ በሚጻፍበት መልክ ነው የተጻፈው” ሲል ይተቻል ሀያሲው፡፡ “ቋንቋው የጋዜጣ እና የመጽሔት እንጂ የመጽሐፍ አይደለም፡፡” እንዲህ አይነት አጻጻፍ መጽሐፉ ምናባዊ መሆኑን በግልጽ ካለመቀመጡ ጋር ተዳምሮ አንባቢን እንደሚያሳስት እርሱ የገጠመውን መነሻ አድርጎ ይከራከራል፡፡

“የቄሳር እንባ” የሚል ስያሜ ያለው በመጋቢት 2007 ዓ.ም ለንባብ የበቃው ሁለተኛውን የሀብታሙ መጽሐፍ እንዲያነብ የጋበዙት አንድ የሀገራችን ታዋቂ ሰዓሊ መሆናቸውን ያነሳና ሰዓሊው መጽሐፉን እንደ ታሪካዊ የፖለቲካ መጽሐፍት መቀበላቸውን ያስረዳል፡፡ በእርሳቸው ደረጃ ይሄ አይነት አመለካከት ከተፈጠረ ተራው አንባቢ መጽሐፍቶቹን እንዴት ሊረዳቸው እንደሚችል ያሳስበዋል፡፡

“የቄሳር እንባ” መንግስቱ ኃይለማርያም ወደ ስልጣን ሲንደረደሩ ጀምሮ በአራት ኪሎ ቤተመንግስት መቀመጫቸውን ካደላደሉ በኋላ በጓዳቸው ሲከወን የነበረውን ጭምር የሚያሳይ ነው፡፡ ብርሃኑ ዘርይሁን የአጼ ቴዎድሮስን ማንነት፣ ሕይወት እና ከቅርብ ሰዎቻቸው ጋር የነበራቸውን አኗኗር በ“ታንጉት ሚስጥር” ግሩም በሆነ ምናባዊ አጻጻፍ እንዳስደመመን ሁሉ ሀብታሙም እምብዛም የማይነገርለትን የፕሬዝዳንት መንግስቱን ቤተ-መንግስታዊ ሕይወት፣ የባል እና የአባትነት ሚና፣ ግላዊ አመለካከት እና ለታሪካዊ ክስተቶች ይሰጧቸው የነበሯቸውን ምላሽ በሰው ሰውኛ ዘይቤ ደፍሮ ሊያሳየን ሞክሯል፡፡

Book Cover
Book Cover

የሀብታሙ ሙከራ የብርሃኑን ያህል ብሉይ (ክላሲክ) ደረጃ የደረሰ ባይሆንም ከ“ኦሮማይ” ለጥቆ መንግስቱን በስነጽሁፋዊ ስራዎች በሳቢ እና ለእውነታው በቀረበ አገላለጽ ያቀረበ ያደርገዋል፡፡ ብርሃኑ የገብርዬ ሚስት ታንጉትን ተጠቅሞ አጼ ቴዎድሮስን እንድናውቃቸው እንዳደረገን ሁሉ ሀብታሙም  የውባንቺ (የመንግስቱ ባለቤት) የአክስት ልጅ አድርጎ በሳለው አባይነህ አማካኝነት “ጥቁሩ ቄሳር” የሚላቸውን የፕሬዝዳንት መንግስቱን ገበና ሊገልጥ ይለፋል፡፡

በቤተ-መንግስት ጓዳ ተቀምጦ ለኬጂቢ እና ለሚካኤል ጎርባቾቭ መረጃ የሚያቀብለው አባይነህ የመንግስቱ ቀኝ እጅ ተደርጎ ተስሏል፡፡ ፕሬዝዳንቱ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ጉዳዮን አጣርቶ እሳቸው ብቻ የሚመለከቱት ሪፖርት እንዲያዘጋጅ ወደ የቦታዎቹ የሚልኩት አባይነህን ነበር፡፡ የባለቤታቸው የቅርብ ዘመድ፣ የልጃቸው አስጠኚ፣ የነገሮች በላች የሆነው ዋና ገጸ- ባህሪ ግን መንግስቱን ቢፈራቸውም በተማረበት ራሺያ ቋንቋ በሚመዘግበው የዕለት ውሎ ማስታወሻው ላይ ሲያብጠለጥላቸው እና ሲተቻቸው ግን ለነገ አይልም፡፡ ለጎርባቾቭ አዘጋጅቶ በሚልከው ሪፖርትም ፕሬዝዳንቱ ሰርተዋቸዋል የሚላቸውን ስህተቶች ነቅሶ በማውጣት ያጋልጣቸዋል፡፡

እንደ “አውሮራ” ሁሉ “የቄሳር እንባ”ም በእውን የነበሩ ክስተቶችን አብዝቶ ይጠቀማል፡፡ ይህ አቀራረቡ በ“አውሮራ” ላይ እንደተነሳው ሁሉ በ“የቄሳር እንባ” ላይም አንባቢያን መጽሐፉን እንደ ኢ-ልቦለድ እንዲወስዱት ይገፋል የሚል ትችት ደራሲው ላይ አስከትሎበታል፡፡ በመጽሀፉ ጀርባ ላይ የተጻፈው እና ለደራሲው የተሰጠው እና የንጽጽር ውዳሴም ለአንባቢያን የሚሰጠው አንድምታ የታሰበበት አይመስልም፡፡

የ“አዲስ አድማስ” ጋዜጣ አምደኛ እንደሆኑ የተገለጹት ደረጀ ይመር በመጽሐፍ ጀርባ አስተያያታቸው ደራሲውን እንደ ተስፋዬ ገብረአብ ሁሉ “ሥነ ጽሁፍንና ፖለቲካን ድል ባለ ሰርግ ያጋባ” ሲሉ ያሞካሹታል፡፡ አከራካሪ ቢሆንም ተስፋዬ ገብረአብ የገነነው በእውን የተከሰቱ ጉዳዮችን አጣፍጦ በመጻፍ መሆኑን የመጽሐፉ አዘጋጆች የዘነጉት ይመስላል፡፡ ለነገሩ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደም ሀያሲያን ከሚያቀርቡት “መደናገር” አላመለጠም፡፡

እንዳለጌታ ከቀናት በፊት ለንባብ በበቃው 10ኛ መጽሐፉ “በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ” ማብቂያ ላይ “የቄሳር እንባ”ን በዋቢ መጽሐፍት ዝርዝር ላይ ከአናት አስቀምጦታል፡፡ በውስጥ ገጾች “እንደ ኦሮማይ የልብወለድ ድርሰት ነው” ሲል ለሚገልጸው “የቄሳር እንባ” ምላሽ ለመስጠት ሲሞክር ይስተዋላል፡፡ “እንደ እኔ እምነት ‘የቄሳር እንባ’ እንደሚተርከው በዓሉ [ግርማ] በኦሮማይ ሰበብ ከሥራ ከታገደ በኋላ፣ ከሕንድ ኤምባሲ ጋር የተለየ ቅርበት ፈጥሮ ነበር በሚለው አልስማም” ይላል፡፡

በቅርቡ ለንባብ የበቃው “የሱፍ አበባ”ም የሀብታሙ መጽሐፍት ከሚያስነሱት “የግርታ ስሜት” አላመለጠም፡፡ “የሱፍ አበባ” ታሪኩን በአለፍ ገደም ለመንካት እንኳ ለብዙዎች ስሱ የሆነው የኢህአፓ ታሪክ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው፡፡ ኢህአፓን ዋነኛ ማጠንጠኛ ካደረጉት ውስጥ ከኢ-ልቦለዶቹ “ያ ትውልድ” ከቅጽ አንድ እስከ ሶስት፣ “ኢሕአሠ”፣ “የአሲምባ ፍቅር” እና “ማማ በሰማይ ላይ” ሲጠቀሱ “ምርኮኛ” እና “ከደንቢያ ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ” ደግሞ በልቦለዱ ዘርፍ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይቀመጣሉ፡፡

Book Cover
Book Cover

“የሱፍ አበባ” ከኢህአፓ ግዙፍ አቋሞች እስከ ወሳኝ መሪዎቹ፣ ከህቡዕ ትግል እስከ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች ድረስ ዘልቆ ለማሳየት ይሞክራል፡፡ የፓርቲውን የወቅቱን አቋሞች ከተለያዩ ጽንፎች ያሳይና በዋና ገጸ-ባህሪው ሰመረ (በትግል ስሙ አላምረው) ክፉኛ ይሞግተዋል፡፡

የኢህአፓ መስራቾች በአንድ ወቅት ከባህርዳር ወደ አዲስ አበባ ይበር የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድን አውሮፕላንን እንዴት እንደጠለፉ በመተረክ የሚጀምረው “የሱፍ አበባ” ኢህአፓ በተለይ በአዲስ አበባ የነበረውን እንቅስቃሴ በዝርዝር ያሳያል፡፡ አጋጣሚ ሆኖ በአውሮፕላን ጠለፋው ወቅት በተጓዥነት በቦታው የተገኘው ዋና ገጸ-ባህሪ ከዓመታት በኋላ ከጠላፊዎቹ ጋር በኢህአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የሚታደም እና በቁልፍ የኢህአፓ ተግባራት የሚሳተፍ ይሆናል፡፡

“የሱፍ አበባ”ን ከሀብታሙ ቀደምት ሁለት መጽሐፎች ለየት የሚያደርገው ሁሉን አወቅ በሆነው የደራሲው ትረካ ሳይሆን በዋና ገጸ-ባህሪው አንደኛ መደብ ተራኪነት የቀረበ ነው፡፡ ይህ የአተራረክ ስልት ዋና ገጸ-ባህሪው አላምረው የኢህአፓ ግዙፍ ስህተቶች ተብለው በታሪክ የሚጠቀሱትን ውሳኔዎች እና ሁነቶች በግል አተያዩ እንደልብ እንዲተቸው እድል ሰጥቶታል፡፡ አላምረው ከሁሉ ከሁሉ አጥብቆ የሚያብጠለጥለው ኢህአፓ በአሲምባ የጀመረውን የትጥቅ ትግል ገሸሽ አድርጎ በከተማ እንቅስቃሴ መወሰኑ ነው፡፡ አንዴ “ገበርደኒዝም” ሌላ ጊዜ “ሱፍ አበባዊነት (ሰንፍላወሪዝም)” የሚል የርዕዮት ዓለማዊ ትንተና እየሰጠ የኢህአፓን መሪዎች ሲፈታተን በመጽሐፉ ይነበባል፡፡

 አላምረው እና የቅርብ ጓዱ ሆኖ የተሳለው ኢሳያስ በከተማ ትጥቅ ትግል ላይም ሆነ ከደርግ ጋር በሚመሰረት የጋራ ግንባር ላይ የመረረ ተቃውሞ ቢኖራቸውም “ኢሕአፓ የቱንም ያህል ይሳሳት፣ ታማኝነታችንና ታዛዥነታችን ሁሌም ይቀጥላል” የሚሉ ነበሩ፡፡ የተለየ አቋም ቢያራምዱም “አንጃ” ላለመፍጠር የነበራቸው ጥንቃቄ እና ስጋት፣ በድርጅታቸው የተሰጣቸውን ሚና ለመተግበር ሲሉ የገቡበት የድመት እና አይጥ ጨዋታ የመሰለ የህቡዕ ሕይወት፣ ከድርጅቱ አባል የፍቅር ጓደኛ ጋር እንኳ ለመጋራት ጥብቅ የነበረው የድርጅታዊ ስራ ሚስጥር እና ዲስፕሊን እንደዚሁም ለዓላማ ኖሮ ለዓላማ መሰዋት የሕይወት ፍልስፍና በመጽሐፉ በሚገባ ተከሽኖ ቀርቧል፡፡

የኢህአፓ አባል የነበሩ እና ለዓመታት በእስር የማቀቁ የጹሁፍ ሰው “የሱፍ አበባ”ን “በስነ-ጽሁፍ ይዘትም ሆነ ቅርጽ ካረኩኝ ጥቂት መጽሐፍት አንዱ ነው” ሲሉ ከጥሩዎች ጎራ ያሰልፉታል፡፡ ደራሲውን ደግሞ በኢህአፓ ዙሪያ የተጻፉ ድርሳኖችን “ልቅም አድርጎ ያነበበ” ሲሉ ያወድሱታል፡፡ መጽሐፉ የጊዜውን ሁኔታ በደንብ አድርጎ ያስቀመጠ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ “መጽሀፉ የተጻፈው በመልሶ ምልከታ ነው፡፡ እንዲህ መመልከት ደግሞ ጠቀሜታ አለው” ይላሉ ጸሀፊው፡፡ “የወቅቱ ፖለቲካዊ እና ማህበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች በሌሉበት የሚጻፍ ስለሆነ ብዙ ነገር መመልከትም መተቸትም ያስችላል፡፡”

በሁለት ጎራ ተክፍሎ ከነበረው የኢህአፓ አመራር በተቃረነ መልኩ በአላምረው በኩል የሚቀነቀነው “ሶስተኛው መንገድ” በፓርቲው ውስጥ በ“ግርድፉም” ቢሆን እንደነበር የሚያስታውሱት ጸሀፊው በወቅቱ ይሄን ለመተግበር ግን “ጊዜ፣ ሁኔታ እና አቅም አልነበረም” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

ጸሀፊው በሀያሲው የሚነሳውን “እውነት እና ልቦለድን የማሳከር ጉዳይ” አጽንኦት ሊሰጥበት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡ እርሳቸው መጽሐፉን በተመለከቱበት ወቅት በጀርባው የተጻፈውን በመመልከት ብቻ መጽሐፉ የኢህአፓን ታሪክ የሚያወሳ ኢ-ልቦለዳዊ ስራ መስሏቸው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ከመጽሀፉ ተቆንጽሎ በመጽሐፉ ጀርባ የታተመው የመጽሐፉን ምሉዕ ምስል የማያሳይ እና “አሳሳች” እንደሆነም ያክሉበታል፡፡ የጀርባ ማስተዋወቂያው ብርሃነመስቀል ረዳ ፓርቲውን እንዴት እንደፈጠረው እና ዘርዑ ክህሽን በሰራው ስህተት ለውድቀት እንደበቃ የሚያስረዳ ነው፡፡

“የሱፍ አበባ” የወቅቱ አነጋጋሪ መጽሐፍ ከሆነው የበዕውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር” ጋር በተመሳሳይ ወቅት ለገበያ የበቃ ነው፡፡ “ከአሜን ባሻገር” መሳ ለመሳም ባይሆን ገበያ እየተሻማ መሆኑ ማመላከቻው “የሱፍ አበባ”ን አንብበው ሌሎች የሀብታሙ ስራዎችን ማንበብ የሻቱ አንባቢያን “የቄሳር እንባ”ን ከገበያ እንዲጠፋ ማድረጋቸው ነው፡፡ የሸገር ሁነኛ የተባሉ የመጽሐፍት አከፋፋዮች ዘንድም ሆነ አዟሪዎች ዘንድ መጽሀፉ የለም፡፡ “የቄሳር እንባ” እስካሁን 10 ሺህ ቅጂ የተሸጠ ሲሆን ሶስተኛው እትም በማተሚያ ቤት እንደሚገኝ ከአሳታሚው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡