ዋዜማ ራዲዮ-ኳታር ኢትዮጵያና ኤርትራን ለመሸምገል ፍላጎት እንዳላት ማክሰኞ ዕለት (ትናንት) አዲስ አበባን የጎበኙት የሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱራህማን አል ተሀኒ ለጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ መግለፃቸው ተሰማ።
የኳታር የዲፕሎማቲክ ምንጮች እንደገለፁት የኳታር ልዑካን በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ጋር የተነጋገረ ሲሆን፣ የአፍሪቃ ቀንድ የፀጥታ ጉዳይ አንዱ የመነጋገሪያ ርዕስ ነበረ።የየመን ቀውስ፣ የሶማሊያ፣ የሱዳንና የኤርትራ ጉዳይ ላይ በተደረገው የሀሳብ ልውውጥ ኳታር የኤርትራና የኢትዮጵያ ውዝግብ በድርድር እንዲፈታ ለዚህም አዲስ ጥረት የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ገልፃላች። ኳታር ከአምስት አመት በፊት ተመሳሳይ የማደራደር ዕቅድ አቅርባ ሳይሳካ ቀርቷል።
ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ኢትዮጵያ ችግሩ በድርድር እንዲፈታ ፍላጎት እንዳላት ተናግረው ይሁንና የኤርትራ መንግስት ለሰላማዊ መንገድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ በበርካታ ሸምጋዮች የተደረጉ ጥረቶች ሳይሳኩ መቅረታቸውን አመልክተዋል።
በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል እየሻከረ የመጣው ግንኙነት የአፍሪቃ ቀንድን እንዳያውከው ስጋት ያላት ኳታር ሁለቱ ሀገራት አለመግባባቶችን በውይይት እንዲፈቱ መክራለች።
የኢትዮጵያና የኤርትራ ውዝግብ በአፍሪቃ ቀንድ እያደገ የመጣውን የገልፍ ሀገራት ጂኦ-ፖለቲካል ፍላጎት ላይ አደጋ ይደቅናል የሚል ስጋት አለ። የገልፍ ሀገራት ማህበር (Gulf Cooperation Council0 አባል የሆነችው ኳታር ይህንን አጣብቂኝ ለመፍታት ፍላጎት እንዳላት የመረጃ ምንጫችን ጠቁመዋል።
ሳዑዲ አረቢያ፣ ኩዌት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባህሬንና ኳታር የገልፍ ሀገራት ትብብር ማህበር(GCC) አባል ናቸው።
በየመን ቀውስ ኢትዮጵያ ልታበረክት የምትችለው አስተዋፃኦ ላይም ሰፊ ውይይት መደረጉንና ዝርዝሩን መናገር እንደሚቸግራቸው የዋዜማ ምንጭ ጠቁመዋል። በየመን እያደረጉት ያለው ዘመቻ ያልተሳካለቸው ሳዑዲ አረቢያና ሸሪኮቿ ኢትዮጵያ እግረኛ ወታደር በማዋጣት እንድትደግፍ ፍላጎት አላቸው። በዚህ ውይይት ላይ እግረኛ ወታደር ስለማሰማራት የተነሳ ሀሳብ ስለማኖሩ ማረጋገጥ አልቻልንም።
የኳታር ልዑካን በኢንቨስትመንትና ብድር ጉዳዮች ላይም የተነጋገረ ሲሆን የኢትዮጵያ ልዑካን በቀጣይ ወዳ ኳታር ያመራል።