ዋዜማ ራዲዮ- ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ 412 ሚሊየን ብር በተጭበረበረ መንገድ በወሰደው የቱርክ ኩባን ያና ብድሩን በፈቀዱት የባንኩ ሰራተኞች ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው።

ከሶስት ዓመታት በፊት በጨርቃጨርቅ ምርት ዘርፍ ለመሰማራት የቱርኩ አሪ አምባላጅ ቴክስታይል ኩባንያ የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥቶ ይመዘገባል። አሪ አምባላጅ ቴክስታይል በኢትዮጵያ ስሙን ወደ ጊዛል ጨርቃጨርቅ በመቀየርና በሁለትቱርካውን ባለሃብቶች ኢሃን አልፋይ እና ኒሃት አልፋይ በተባሉ ባለሃብቶች ስም ስራውን ለመቀጠል እንቅስቃሴ ይጀምራል፡፡

ኩባን ያው ስራውን ከመጀመሩ አስቀድሞ ቱርክ ሀገር ያለውን ያገለገለ የጨርቃጨርቅ ማምረቻ ማሽን እንደመነሻ ካፒታል እንዲያዝለትና ማሽኑን ከቱርክ ነቅሎ ለማምጣት ይጠይቃል። በተለየ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ያገለገለ ማሽን እንደመያዣ ተቆጥሮ ወደ ሀገርቤት እንዲገባ አይፈቀድም። ከዚህ ቀደም ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ለግል ባለሀብት ሲሸጥ በልዩ ሁኔታ ያገለገለ ማሽን እንዲያስገባ ተፈቅዶለት ችግሮች መከሰታቸው ይታወቃል።

ማሽኖቹ ያሉበትን ሁኔታ የሚያጠናና ግምት የሚያወጣ የል ማት ባንክ ቡድን ወደቱርክ ተጉዞ ግምት ሰርቶ ይመለሳል።በዚህ ቡድን ውስጥ የቴክስታይል እና የሜካኒካል የምህንድስና ባለሙያዎችን ጨምሮ የባንኩ የዘርፍ ሃላፊዎች ጭምር የተካተተበት ቡድን ነበር። የቱርኩ ጊዛል ጨርቃጨርቅ (አሪ አምባላጅ ቴክስታይል) ያገለገሉትን ማሽኖች አነጋጋሪና አወዛጋቢ በሆነ መንገድ መቶ አርባ ሚሊየን ብር ይገመትለታል። በወቅቱ ከኣኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ለማግኘት አሮጌዎቹ ማሽኖቹ የዋስትና መያዣ ሆነው አራት መቶ ሀያ ሚሊየን ብር ብድር ይፈቀድለታል።
አሮጌዎቹ ማሽኖችም ለገጣፎ አካባቢ ድርጅቱ በተሰጠው ቦታ ላይ ተተክለው ፋብሪካው ይከፈታል።

የልማት ባንኩ አሁን እንደደረሰበትና ዋዜማ ጉዳዩን ከሚያውቁ ምንጮችና ከተለያዩ ሰነዶች እንተረዳችው አሮጌዎቹ ማሽኖች ለዳግም ምርት ብቃት የሌላቸውና ተነቅለው ለመጣል የተቃረቡ በዋጋ ግምትም እጅግ ዝቅተኛ የሚባሉ ናቸው።

ጊዛል ጨርቃጨርቅ የቤተሰብ ኩባን ያ ነው። ቱርካውያኑ ባለሃብቶች ኢሃን አልፋይ እና ኒሃት አልፋይ በተባሉ ባለሃብቶች የተመዘገበ ድርጅት። በድርጅቱ ባለንብረቶች መካከል የተካረረ ግጭት ይቀሰቀሳል። ከባለሀብቶቹ አንዱ ወደልማት ባንክ ሀላፊዎች ይቀርብና ድርጅቱ ያስገባው ማሽን አሮጌ መሆኑን፣ ማሽኑ በጥሩ ዋጋ እንዲገመት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ያህል ለልማት ባንኩ ገማቾች ወጪ አድርጎ ጉቦ መስጠቱን ያጋልጣል።

ይህ መረጃ የልማት ባንኩ ቁልፍ ስራተኞችና ሀላፊዎችን ያስደነግጣል። ባንኩ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እያደረገ ነው። ፖሊስም ጉዳዩን እየመረመረ ነው። የልማት ባንኩ የጨርቃጨርቅ ማሽኖቹ ዳግም የዋጋ ግምት እንዲሰራ አድርጓል።

ልማት ባንክ ስለ አሪ አምባላጅ መረጃ ለማሰባሰብ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የቱርክ ኤምባሲ መረጃ ይጠይቃል። ኤምባሲው ኩባን ያው በሀገሩ ጥሩ ስም የሌለውና በወንጀልና ማጭበርበር ስሙ የሚነሳ መሆኑን አልሸሸገም። ኤምባሲው አሮጌዎቹ ማሽኖች ከሀያ ሚሊየን ብር በላይ መገመት አልነበረበትም የሚል የራሱን ግምገማ አድርጓል።
አሁን የ412 ሚሊየን ብሩ ውንብድና ተዋናዮች የሚለዩበትና ህግ ፊት የሚቀርቡበት ሰዓት ተቃርቧል። [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/R-ZefDYid6A