Abie Sano, newly appointed CBE President- Photo Addis FORTUNE
  • አቶ ባጫ ናጊስ ከስልጣናቸው ለምን ተነሱ?

ዋዜማ ራዲዮ- ያለፉትን ወራት በቀውስና በውዝግብ ያሳለፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ ፕሬዝዳንት እንደተሾመለት ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። አዲሱ ፕሬዝዳንት አቢ ሳኖ ትናንት የሹመት ደብዳቤ የደረሳቸው ሲሆን ዛሬ ስራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

አቶ አቢ ሳኖ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እንዲሁም የባንኮች ማህበር ፕሬዝዳንት በመሆን ሲያገለግሉ ነበር። በቀደሙት አመታትም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ በነበራቸው የአመራርነት ድርሻ በብቃታቸው ከበሬታን ያገኙ ባለሙያ እንደነበሩ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች ነግረውናል።

በ2010 አ.ም ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትነት ከተሾሙ ጀምሮ ብዙ ውዝግብ የተነሳባቸው አቶ ባጫ ጊና ፣ የቀድሞ የብሄራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ለንግድ ባንኩ አዲስ የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው መሾማቸው ከተሰማ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከባንኩ ፕሬዚዳንትነት ተነስተው ከሌሎች የቀድሞ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ጋር ለአምባሳደርነት መሾማቸው ተሰምቷል።

አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ከፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍጹም አስፋው የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበርነትን ከተረከቡና ገና አንድ የቦርድ ስብሰባ ማድረጋቸው ከተሰማ በሁዋላ ነው አቶ ባጫ ጊና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትነት መነሳታቸው የታወቀው።ከሀላፊነት የመነሳታቸው መነሻም በአዲሱ የቦርድ ሊቀመንበር የተደረገ ግምገማ እንደሆነ ሰምተናል።


ዋዜማ ራዲዮ የአቶ ባጫ ከስልጣን የተነሱበትን ምክንያት ለመፈተሽ ሞክራለች።የኢትዮጵያን ግዙፍ ባንክና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ዋና ድርሻን የሚጫወት ባንክን እንዲመሩ በ2010 አ.ም የተሾሙት አቶ ባጫ ጊና ቀድሞም ቢሆን ይህን ወሳኝ ተቋም ከመምራት አንጻር ሰፊ የብቃት ችግር ያለባቸው ናቸው በሚል በባንኩ የቦርድ አባላት ሳይቀር በብዛት እንደሚተቹ ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች። በተለይ ኢትዮጵያ ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF ) የሶስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድር ለማግኘት ድርድር ላይ በነበረችበትም ጊዜ ሆነ የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አመታዊውን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ቁመና በፈተሸበት አርቲክል 4 ኮንሰልቴሽን ማጠናቀቂያ ሪፖርቱ ላይ በኢትዮጵያ ለሚደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወቅታዊ ቁመና መሻሻል እንዳለበት አጥብቆ አሳስቧል። አቶ ባጫ ከዚህ አንጻር ባንኩን የመሩበት መንገድ ይህን ለማሳካታቸው ከፍተኛ ጥርጣሬን ያጭራል ተብለዋል።


የ2012 በጀት አመት የመጀመርያ ስድስት ወራት ንግድ ባንክ ያሳየው የስራ አፈጻጸም በባንኩ ታሪክ ብዙም ታይቶ የማያውቅ ዝቅተኛ ነው።ባንኩ በዚሁ ጊዜ 38.3 ቢሊየን ብር ቁጠባን ከደንበኞቹ ለማሰባሰብ አቅዶ ነበር። ይህ እቅድ መንግስታዊ ቁጠባን አያካትትም (ከደንበኞች ብቻ የሚቆጠበውን ብቻ ነው)። ነገር ግን የንግድ ባንኩ በተጠቀሰው ጊዜ ከደንበኞቹ ያሰባሰበው ቁጠባ 24.6 ቢሊየን ብር ነው።በመቶኛ ሲቀመጥ የቁጠባ አፈጻጸሙ 64 በመቶ ብቻ ነው።ይህም የቁጠባ አፈጻጸም ካለፉት አመታት አንጻር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ተገምግሟል።ባንኩ ከበርካታ አመታት ወዲህ የቁጠባ አፈጻጸሙ የእቅዱ መቶና ከመቶ በመቶ በላይ ነበር የሚፈጽመው። የዚህ የስድስት ወር አፈጻጸም ግን ከባለፈው አመት አንጻር ብቻ ሳይሆን የብዙ አመታት ዝቅተኛው አፈጻጸም ሆኗል።

ለባንኩ አደጋ የፈጠረው ሌላው ገጽታ ግን ንግድ ባንኩ በተመሳሳይ በስድስት ወሩ የሰጠው ብድር ከሰበሰበው ዝቅተኛ ብድር ጋር የማይመጣጠን መሆኑ ነው።40 ቢሊየን ብር ብድር ሰጥቷል ። 50 ቢሊየን ብር አቅዶ ነው 40 ቢሊየን ብር ብድር የሰጠው።የተሰጠው ብድር የተሰበሰበውን ቁጠባ ከ15 ቢሊየን ብር በሆነ ልዩነት ይበልጠዋል።


ከዚህ ቀደም ባንኩ ለሚሰጠው ብድር ከሚሰበስበው ቁጠባ በተጨማሪ የብሄራዊ ባንክ ድጎማን ቢጠቀምም የዚህ አመቱ የባንኩ ቁጠባና የተለቀቀ ብድር አለመመጣጠን ንግድ ባንክን ታይቶ ለማይታወቅ የገንዘብ እጥረት ዳርጎት ታይቷል። የገንዘብ እጥረቱ ግብር በሚከፈልባቸው ወራት የሚያጋጥምና በሁሉም ባንኮች የሚታይ ቢሆንም የዚህ አመቱ ግን ለየት ማለቱን ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች።

መጀመርያ ላይ ንግድ ባንክ ለሰራተኞቹ ይሰጥ ከነበረው የሁለት ዙር የቤት መግዣ ብድር አንዱን ዙር አቆመ። ቀጥሎ ደግሞ ከነጭራሹም ሙሉ ለሙሉ ለሰራተኞቹ ይሰጥ የነበረውን ብድር ለማቆም ተገዷል። ለዚህም በምክንያትነት የቀረበው የገንዘብ እጥረት ነው።ለሰራተኞች ቤት መግዣ የሚቀርብ ብድር በአንጻሩ አነስተኛ ቢሆንም ባንኩ ይህን እንኳ ማቋረጡ የገባበትን ችግር ያሳየና ባንክ ከመስራት ይገኝ የነበረን ቀዳሚና ዋና ጥቅም በማስቀረት ሰራተኞች ላይ ከፍተኛ ቅሬታን የፈጠረ ነው።

ባንኩ በቁጠባ አሰባሰብ ላይ እጅግ ደካማ ሆኖ የታየው የሀገሪቱ ፖሊቲካዊ ችግር ኢኮኖሚውን ስለጎዳው ነው ተብሎ ሊታሰብ ቢችልም የሚለቀቀው ብድር ላይ እጅን ያዝ በማድረግ ባንኩን ከገባበት የገንዘብ ቀውስ መታደግ ይቻል እንደነበር ተነስቷል።
ነገር ግን የተሰጠው 40 ቢሊየን ብድር እንኳ ፍትሀዊነት የጎደለውና በርካታ የብድር ጥያቄዎች ቀርበው ሳለ ማንነት ተኮር በሆነ መልኩ እንዲሰጥ መታዘዙ በአቶ ባጫ ላይ በድክመት ተነስቶባቸዋል።


ከውጭ ምንዛሬ አፈጻጸም አንጻር ከበፊቱ አመራር ብዙም የተለየ ድክመት በአቶ ባጫ ጊና ላይ አልታየም።በበጀት አመቱ ስድስት ወራት 2.7 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ባንኩ አቅዶ 1.9 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ሰብስቧል። የእቅዱን 68 በመቶ እንደማለት ነው። ነገር ግን የውጭ ምንዛሬ አፈቃቀድ ላይ የነበረ ኢ ፍትሀዊነት እና የውጭ ምንዛሬ ጥያቄ ለሚያቀርቡ ለሀብቶች ጥያቄያቸው እንዲስተናገድ የጠየቁት ምንዛሬ በብር ተባዝቶ ሁለት መቶ በመቶውን ያክል እንዲቆጥቡ መገደዳቸው ብዙ በወጪ ገቢ ንግድ ላይ የተሰማሩ የባንኩን ደንበኞች አሽሽቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሮም በወጪ ገቢ ንግድ ላይ በተሰማሩ ባለሀብቶች አይወደድም አሁን የባንኩን ደንበኝነታቸውን ያቋረጡ ኤክስፖርተሮች ምጣኔ ከበፊቱ ያደገ መሆኑንም ሰምተናል።

ከከፍተኛ እስከ በታች አመራር ላይ ያሉ ግለሰቦች አመራረጥ የባጫ ጊና የንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትነት ጊዜ ትልቁ መነጋገርያ ነበር።ዋዜማ ራዲዮ ከባንኩ ከፍተኛ አመራሮች እንደሰማቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ75 በላይ ለሆኑ አመታት የአመራር ክፍት ቦታ ሲኖር ለተለየ ሙያ ካልሆነ ለውስጥ ሰራተኞች ነበር እድል የሚሰጠው። አቶ ባጫ የባንኩ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ግን አሰራሩን ቀየሩት።

ልክ የባንኩ ፕሬዝዳንት እንደሆኑ የህግ ፣የሰው ሀይል ፣ የባንኪንግ ቢዝነስ ፣ የባንክ ኦፕሬሽን ፣የኦዲት ዘርፍና ኮንትሮል ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንቶችንና ከፍተኛ ሀላፊዎችን ከአዋሽ ባንክና ከኦሮምያ ህብረት ስራ ባንክ አምጥተው አሹመዋል።ሁለቱ ባንኮች አቶ ባጫ የንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት የሰሩባቸው ባንኮች መሆናቸው ይታወቃል። የአመራር አሿሿሙም የብሄር ማንነትን መስፈርት ያደረገ በመሆኑ ከፍተኛ ውዝግብ ፈጥሯል። ይህን ለማስተካከልም ከከፍተኛ እስከ ታች አመራር የስራ ቅጥር እንዲወጣ ይወሰናል። ሆኖም በዚሁ የስራ ቅጥር አልፈው የሚቀጠሩት አመራሮችም ከጥቂቶቹ በቀር አብዛኞቹ የስራ ልምዳቸው የአዋሽ ባንክና የኦሮምያ ህብረት ስራ ባንክ መሆኑ የቅጥር አፈጻጸሙን ፍትሀዊነት ጥያቄ ውስጥ ጨምሮታል።በዚህ ረገድ በንግድ ባንኩም ከችሎታ ይልቅ ማንነት ላይ የተመሰረቱ ሹም ሽሮች በዝተው እንደነበር ተነስቷል። ለባንኩ የስራ አፈጻጸም ደካማነት አንዱ መነሻም ይኸው ነው።በዚህ ሁኔታ ላይም ነው ሳይጠበቅ የባንኩ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ባጫ ጊና ከሀላፊነታቸው መነሳታቸው የተሰማው። [ዋዜማ ራዲዮ]

to contact Wazema Editors- You can write to wazemaradio@gmail.com