Karaturiዋዜማ ራዲዮ- ፌደራል መንግስቱ ባሳለፍነው ሳምንት የክልሎችን ሰፋፊ መሬቶች በአደራ ማስተዳደሩን ትቶ ስልጣኑን ለክልሎች መልሷል፡፡ የአሰራር ለውጡ የሚነግረን ነገር ቢኖር የፌደራል መንገስቱ መሬት የማስተዳደር እና በሊዝ የማስተላለፍ አሰራር ከባድ ኪሳራ ውስጥ መውደቁን የሚያረጋግጥ ሆኗል፡፡ ለውጡን መሰረት አድርገን ፌደራል መንግስቱ ለምን ባሁኑ ሰዓት ስልጣኑን ለክልሎች መመለስ ፈለገ? የአሰራር ለውጡ ዓላማ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ ወይስ ኢኮኖሚያዊ መንስዔ ያለው ነው? ለመሆኑ ለውጡ ለክልል መንግስታት ምን አንድምታዎች ይኖሩት ይሆን? የሰፋፊ ለም መሬቶች አስተዳደር እና ልማት የወደፊት እጣ ፋንታ እና ፌደራል መንግስቱ ሙሉ ቁጥጥሩን ላለማጣት ምን ዓይነት አማራጭ አሰራሮችን ሊከተል ይችላል? ሪፖርተራችን ቻላቸው ታደሰ ጊዜ ወስዶ ተመልክቶታል።
ፌደራል መንግስቱ ከአራት ክልሎች ከሦስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ሰፋፊ ለም መሬቶችን በአደራ ተረክቦ ማስተዳደር እና ለባለሃብቶች ማስተላለፍ ከጀመረ ወዲህ ሁለት ለውጦችን አድርጓል፡፡ የመጀመሪያው ባለፈው መጋቢት ሰፋፊ መሬቶችን ለባለሃብቶች ማከራየቱን ላልተወሰነ ጊዜ ማቋረጡ ሲሆን ሌላኛው ደሞ ሰሞኑን በአደራ የተሰጠውን መሬት የማስተዳር እና የማስተላለፍ ስልጣን ለክልሎች መመለሱ ነው፡፡ ነባሩ አሰራር እንዲቀር የተደረገው ጠቅላይ ሚንስትሩ ያዋቀሩት አካል በጋምቤላ ሰፋፊ እርሻ ልማቶች ላይ የደረሰውን ችግር አጥንቶ ባቀረበላቸው ውጤት ላይ ተመርኩዘው መመሪያ በማስተላለፋቸው እንደሆነ ተገልጧል፡፡

የአሰራር ለውጡ የተወሰነው በጋምቤላ ብቻ በተከሰተው ውድቀት ይሁን ወይም በሌሎች ክልሎች ጭምር ግልጽ አልተደረገም፡፡ ለጊዜው የተጠናው ግን ጋምቤላ መሆኑ ተገልጧል፡፡ ውሳኔው የተላለፈው ግን ለባለሃብቶች በተሰጡ ሰፋፊ መሬቶች ላይ ለደረሰው ኪሳራ በፓርላማ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂ የተደረገ አካል ሳይኖር በደፈናው ነው፡፡ በርግጥ ልማት ባንክ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ በጋምቤላ ለተሰማሩ የሰፋፊ እርሻ ባለቤቶች የተበላሸ አምስት ቢሊዮን ብር ማበደሩን ተከትሎ ይመስላል በቅርቡ ስራ አስኪያጁ ከቦታቸው ተነስተዋል፡፡ ከዚህ ውጭ በሰፋፊ ለም መሬቶች ላይ የደረሰው ግዙፍ ኪሳራ እንደተዳፈነ ነው መሬቱን የማስተዳደር ስልጣኑ ለክልሎች የተመለሰው፡፡

የሀገሪቱ ህገ መንግስት ክልሎች የፌደራሉ መንግስት በሚያወጣው ህግ መሰረት መሬት እና ተፈጥሮ ሃብትን የማስተዳደር መብት እንዳላቸው በአንቀጽ 52፣ ንዑስ አንቀጽ 2 ይደነግጋል፡፡ ለዚህም ነበር ላለፉት ዓመታት ፌደራል መንግስቱ ከአምስት ሺህ ሄክታር በላይ የሆኑ ሰፋፊ ለም መሬቶችን ከክልሎች በውክልና ተረክቦ ሲያስተዳድር የቆየው፡፡ መንግስት ውክልናውን የተቀበለው ለአሰራር እንዲያመች መሆኑን ሲገለጽ ኖሯል፡፡ ዋነኛ ምክንያቱ ግን ክልሎች ሰፋፊ መሬቶችን ስመ ጥር ለሆኑ ዓለም ዓቀፍ የውጭ ባለሃብቶች እና ግዙፍ የእርሻ ልማት ኩባንያዎች ለማስተላለፍ እና ለመቆጣጠር አቅም ያንሳቸዋል የሚል እንደሆነ መናገር አያዳግትም፡፡

ፌደራል መንግስቱ በግብርና ኢንቨስትመንት እና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ አማካኝነት ሰፋፊ መሬቶችን በአደራ የተረከበው ገዥው ግንባር ኢህአዴግ በቀጥታ ከሚስተዳድራቸው ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ብቻ አልነበረም፡፡ የኢህአዴግ አጋር በሆኑት ድርጅቶች ከሚመሩት እና በሰፋፊ ለም መሬታቸው ከሚታወቁት ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል እና አፋር ክልሎች ጭምር እንጂ፡፡

በርግጥ በመርህ ደረጃ ፌደራል መንግስቱ በአደራ የተረከበውን መሬት ለባለቤቱቹ መመለሱ ይበል የሚያሰኝ መሆኑ አይካድም፡፡ ስልጣኑ ግን ለሁሉም ክልሎች ባንድ ጊዜ ነው የተመለሰለው፡፡ ትላልቆቹ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎችም አንጻራዊ አስተዳደራዊ ብቃት ስላላቸው ስልጣኑ ቢመለስላቸው እምብዛም አይደንቅም፡፡ በዕድገታቸው እና ብቃታቸው ኋላ ቀር ለሆኑት ሌሎች ክልሎች ጭምር በተመሳሳይ ጊዜ ስልጣኑ መመለሱ ግን ያልተጠበቀ ነው፡፡

ከእስካሁኑ የክልል መንግስታት ባህሪ አንጻር ሲታይ ሰፋፊ መሬቶች ከእስካሁኑ በበለጠ ለሙስና እና ለኪራይ ሰብሳቢነት ሊጋለጡ እንደሚችሉ እና የፖለቲካ ድጋፍ ማግኛም ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ሊሆን እንደሚችል መገት አያስቸግርም፡፡ ለአብነትም በመንግስት እና በሳዑዲው ቱጃር ሞሃመድ አል አሙዲን መካከል በጋምቤላ ክልል በእርሻው ዘርፍ የሚታየው ቅርርቦሽ መንግስትን ምን ያህል ክፉኛ ሲያስተቸው እንደኖረ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚያ ላይ ክልሎች ጸረ ሙስና ተቋም እና ፍርድ ቤትን የመሳሰሉ ጠንካራ የህግ የበላይነት ተቆጣጣሪ ተቋማት አልገነቡም፡፡ በተለይ ብዙ ሰፋፊ መሬት ያላቸው አናሳ ክልሎች ብቃት ያለው አስተዳደራዊ መዋቅር፣ አሰራር እና የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ያለባቸው ናቸው፡፡ ግልጽነት እና ተጠያቂነትም እምብዛም አልሰፈነም፡፡ ክልሎች ከፌደራል ብድር አቅራቢ ባንኮች ጋር ተናበው ለመስራት ምን ያህል እንደሚቸገሩም ከወዲሁ መገመት አይከብድም፡፡

በጣም ሰፋፊ መሬቶችን ለባለሃብቶች ማከራየት የተጀመረው በፌደራል መንግስቱ ስለሆነ ክልሎች በቂ ልምድ የላቸውም ማለት ይቻላል፡፡ መንግስትም ስልጣኑን ለክልሎች ከመመለሱ በፊት ከክልሎች ጋር ስለመምከሩም ሆነ የክልሎችን ዝግጁነት አስቀድሞ ስለማረጋገጡ አንዳች የታወቀ ነገር የለም፡፡ ሰልጣኑ ከተመለሰ በኋላ ሰፋፊ መሬቶች ለባለሃብቶች መተላለፋቸው የሚቀጥል ከሆነ ግን ክልሎች የመሬት አስተዳደር ህጎቻቸውን እና ማስፈጸሚያ መመሪያዎችን እንደገና መፈተሸ እና ጠንካራ ተቋማትን ማደራጀት ግድ ይላቸዋል፡፡

ፌደራል መንግስቱ የመሬት ህግ አውጭ እንደመሆኑ መጠን በ1997 ዓ.ም የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 456ን አውጥቶ በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ አዋጁ መሬት በሊዝ የያዙ ባለሃብቶች የይዘታና የመጠቀም መብት በእያንዳንዱ ክልል እንዲወሰን ስለሚፈቅድ ክልሎችም እንደተጨባጭ ሁኔታቸው ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያዎችን አውጥተዋል፡፡ በአንዳንድ ክልሎች ግን መመሪያዎቹ ግልጽነት እንደሚጎድላቸው እና ተሟልተውም እንደማይገኙ መረጃዎችን ለማሰባሰብ የሞከሩ የፌደራል መንግስት አካላት ሲያማርሩ ይሰማል፡፡

አሁን የሚነሳው ጥያቄ ከዚህ በኋላ የፌደራል መንግስቱ በሰፋፊ እርሻዎች ልማት ምን ሚና ይኖረዋል? የሚለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ እምብዛም ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ግን ክልሎችን ማገዝ የመንግስታቸው ዋነኛ ስራ እንደሚሆን መግለጻቸው ተወስቷል፡፡ ስለዚህ መንግስት ሊከተላቸው የሚችላቸውን ሦስት አሰራሮች ከወዲሁ ታሳቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ አንደኛው ታሳቢ መላ ምት በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ስር የሰፋፊ ለም መሬቶች ልማት ዘርፍ ወይም የክልሎች አማካሪ አካል በማቋቋም ሰፋፊ መሩቶችን በተዘዋዋሪ ማስተዳደር ሊሆን ይችላል የሚለው ነው፡፡ ከኢህአዴግ የማዕከላዊነት ባህሪ አንጻር ሲታይ ይኸኛው የቢሆን ዕድል ሚዛን የሚደፋ ይመስላል፡፡

ሁለተኛው አማራጭ ደሞ እስካሁን ከነጭራሹ ሰፋፊ ለም መሬቶችን ለውጭ ባለሃብቶች መስጠቱን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ወይም ጭራሹን ማቆም ሊሆን ይችላል፡፡ መሬት ማስተላለፉ አሁን ለጊዜው ቢቆምም ጭራሹን ሊቆም የሚችልበት ዕድል ግን የሚኖር አይመስልም፡፡

ሦስተኛው ፌደራል መንግስቱ ራሱ ሰፋፊ የመንግስት እርሻዎችን ወደማልማት ሊገባ ይችላል የሚለው አማራጭ ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድም ላይ ዜጎች ተደራጅተው እና የዘርፉ ባለሀብቶችም ተደጋግፈው ሰፋፊ የእርሻ ልማት እንዲያከናውኑ ይደረጋል የሚል ዕቅድ አስቀምጧል፡፡ መንግስት ይሄን አማራጭ ቢከተልም እንኳ በሀገሪቱ አለኝ የሚለው መሬት ግን በጣም ሰፊ ስለሆነ በመንግስት ብቻ የሚሸፈን አይደለም፡፡ በሌላ በኩል መሬቶቹን በተገቢው መንገድ ለባለሃብቶች ማከራየት ያልቻለ መንግስት ሰፋፊ እርሻዎችን አደራጅቶ መምራት መቻሉ እጅጉን አጠራጣሪ ነው፡፡ መንግስት አሁንም የተወሰኑ ሰፊ የሸንኮራ አገዳ ልማት እርሻዎች ስላሉት እጁን ከሰፋፊ የግብርና ልማቶች አውጥቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ሆኖም የሸንኮራ ልማቱ እና ስኳር ልማቶቹ ከባድ ቀውስ ውስጥ መግባታቸውን በቅርቡ አምኗል፡፡ ለዚህም ነው በቀጥታ በምግብ እና የገበያ ሰብል ወደማምረት ይገባል የሚለው ግምት አናሳ የሚመስለው፡፡

ከዚህ በኋላ ሰፋፊ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ለባለሃብቶች የማከራየቱ ጉዳይ ለክልሎች ውሳኔ ይተዋል? ወይንስ የፌደራል መንግስቱ ውሳኔ ይጠበቃል? የሚለው ጥያቄም ገና ምላሽ ያገኘ አይመስልም፡፡ ያም ሆኖ ከመመሪያው መንፈስ መረዳት የሚቻለው ፌደራል መንግስቱ ካሁን በፊት የተጠቋቋሙትን እንደ ሳዑዲ ስታር ያሉ ሰፋፊ እርሻዎችን ለክልሎች እንደሚያስተላልፍ ነው፡፡ በሌላ በኩል አሁን ፌደራል መንግስቱ ከአስተዳደራዊ ወጭዎች ነጻ ስለሚሆን ወደፊት ከመሬት ኪራይ የሚገኘው ገቢ ክፍፍል እንደገና ሊፈተሸ ይችል ይሀናል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 (የንብረት መብት) ንዑስ አንቀጽ ላይ ‹‹የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው›› ይላል፡፡ መንግሰት በሄክታር 25 ብር ብቻ የሊዝ ዋጋ ተምኖም እንኳ ግዙፎቹ የአውሮፓ እና አሜሪካ የሜካናይዝድ እርሻ ኩባንያዎችን ማማለል አልቻለም፡፡ የክልሎች ዋነኛ የተፈጥሮ ሃብት የሆነውን ለም መሬት ሲቸበችብ የኖረው ለህንድ እና መካከለኛው ምስራቅ ኩባንያዎች ነው፡፡ አንድም ክልላዊ መንግስት ግን በይፋ ተቃውሞ አሰምቶ አያውቅም፡፡ ወደፊትም ክልሎች በገዥው ድርጅት የቁጥጥር መዳፍ ስር እስካሉ ድረስ በሰፋፊ መሬታቸው ላይ ያላቸው ቁጥጥር ከመሰረቱ ይቀየራል ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው፡፡

ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በባለቤትነት የያዘው መሬት አንገብጋቢ ፖለቲካዊ ጉዳይ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ መሬት የስልጣን ህልውናው መሰረት ስለሆነ በመሬት ላይ ያለው ቁጥጥር ከላላ ስልጣኑ እንደሚነቃነቅ ያምናል፡፡ ኢህአዴግ መሬትን እንደውጭ ግንኙነት መሳሪያም ይጠቀምበታል፡፡ የሰሞኑ ለውጥም ቢሆን አስተዳደራዊ እንጂ የፖሊሲ ይዘት ስለሌለው ኢህአዴግ በመሬት ላይ ያለው ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ ቁጥጥሩ ንቅንቅ አላለም፡፡ ባለፈው ዓመት በተነሳው ህዝባዊ አመፅ ግን በተለይ በአማራ ክልል በውጭ ባለሃብቶች የተያዙ የአበባ እርሻዎች ላይ ውድመት መድረሱ ህዝቡ መንግስት አስገኝቸዋለሁ የሚለው ትሩፋት ባዶ መሆኑን በቁጣ ያሳየበት ክስተት ሆኗል፡፡

በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የስራ ዕድል ፈጠራ እና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ብቻ ሳይሆን ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ምግብ ዋስትናን ጭምር በማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ የተሰበከለት የሰፋፊ እርሻዎች ልማት ዕቅድ ብርቱ ቀውስ ውስጥ መግባቱ አሊ የማይባል ሆኗል፡፡ ውድቀቱ በቀጥታ ሁለተኛው የዕድገትና ትራነስፎርሽን ዕቅድ ምሰሶ በሆነው ግብርና-መር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ላይ አሉታዊ አሻራውን እንደሚያሳርፍ እሙን ነው፡፡ በተለይ ብዙ ውዝግብ ያስነሱት የደቡብ ኦሞ እና ጋምቤላ ሰፋ መሬቶች ቅርምት ነበር፡፡ እናም ያሁኑ መመሪያ የሚያሳየው መሬትን የማስተዳደር ስልጣን ለክልሎች መመለሱ መፍትሄ ሆኖ መገኘቱን ነው፡፡

በአጠቃላይ የሰሞኑ የአሰራር ለውጥ የሰፋፊ መሬቶች ልማት መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኑን ጠቋሚ ነው፡፡ ሆኖም ወደነበረው አሰራር መመለሱ የመሬት አስተዳደር እና ልማትን የበለጠ ቢያወሳስበው እንጂ ሊያቃልለው ይችላል የሚለው ተስፋ እምብዛም ነው፡፡