ዋዜማ ራዲዮ- እስከ 50 በመቶ የነበረው ወደ ትግራይ ገንዘብ ለመላክ ለአስተላላፊዎች ይከፈል የነበረው ኮምሽን ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ወደ 25 በመቶ ዝቅ ማለቱን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያሳያል።

ለአስተላላፊዎች ይከፈል የነበረው ገንዘብ የቀነሰው አስተላላፊዎች ስለበዙ እንደሆነ ተረድተናል። 

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል የባንክ አግልገሎት መቋረጡን ተከትሎ፣ ከትግራይ ክልል ውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለቤተሰቦቻቸው በአስተላላፊዎቹ በኩል ኮሚሽን እየከፈሉ ለቤተሰቦቻቸው ብር እንዲደርስላቸው ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ 

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ወደ ትግራይ ገንዘብ የሚልኩ ሰዎች፣ ከሁለት ወራት በፊት ሲከፈል የነበረው 40 እስከ 50 በመቶ የሚደርስ ኮምሽን ካለፈው ሁለት ሳምንት ወዲህ ወደ 25 በመቶ የቀነሰው ገንዘብ በማዘዋወር ሥራው ላይ የተሰማሩ ሰዎች ስለበዙ ነው።

ይህ የላኪዎች መበራከት መንግስት በላኪዎቹ ላይ እርምጃ እንዲወስድ እንዳደረገው ሰምተናል።

በቅርቡ ዋና መተላለፊያ በሆኑት በአማራ ክልል ቆቦና በአፋር ክልል ሰመራ ብር አዘዋዋሪዎች እየተያዙ መሆኑን ጉዳዩን እናውቃለን ያሉ እማኞች ነግረውናል፡፡

በትግራይ የባንክ አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ፣ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ የተደራጁ ግለሰቦች ከትግራይ ክልል ውጭ የሚኖሩ ሠዎች ትግራይ ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው የሚልኩትን ገንዘብ ለማድረስ መቀመጫቸውን አላማጣ አድርገው የኮሚሽን ማስከፈል ከጀመሩ ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡ 

አንድ ከክልሉ ውጭ የሚገኝ ሰው ትግራይ ለሚገኝ ቤተሰቡ ገንዘብ መላክ ቢፈልግ፣ በቅድሚያ ገንዘቡን በሚያዘዋውሩት አካላት የባንክ ሒሳብ ቁጥር ማስገባት አለበት። የላኪውን ገንዘብ የሚቀበለው አዘዋዋሪ አካል አላማጣ በሚገኙ ተወካዮቹ አማካይነት ለተላከለት ሰው እንደሚስረክብ ላኪዎች ይናገራሉ፡፡

የጥሬ ገንዘብ ዝውውሩ የተጀመረው በክልሉ የሚገኙ ሰዎች የኔትወርክ አገልግሎት ለማግኘት ወደ አላማጣ እየተጓዙ ከክልሉ ውጭ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት ከጀመሩ በኋላ ነው። 

በርካታ ሰዎች ወደ አላማጣ እየተጓዙ ከክልሉ ውጭ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ማስላክ ከጀመሩም ሰንብተዋል። 

ይህ የገንዘብ ማስተላለፍ ስራ በአመዛኙ በመተማመን ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች የላኩት ገንዘብ ለቤተሰቦቻቸው በትክክል መድረሱን ማረጋገጥ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]

የአዘጋጁ ማስታወሻ-  ይህን ዘገባ ስናጠናቅር በቦታና በስም የሚታወቁ የመረጃ ምንጮቻችንን ማንነት ደብቀናል።