ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ ክልል በርካታ ዜጎች ቄያቸውን ለቀው ወደ ተለያዩ ክልሎች እየተሰደዱ መሆኑን የዋዜማ ምንጮች እየገለጹ ነው።
በተለይ በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ አካባቢዎች ጉሊሶ እና ባቦ ገምቤል ወረዳዎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ አርሶ አደሮች ከታጣቂዎች በመሸሽ ክልሉን ለቀው ወደ ቤንሻንጉል ጉምዝ እና ወደ አማራ ክልል እየገቡ መሆኑን ተፈናቃዮቹ ለዋዜማ ተናግረዋል።
ተፈናቃዮቹ እየተሰደዱ ያሉት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ቡሬ እና ባህርዳር ፤ በደቡብ ወሎ ሐይቅ እና ደሴ በሰሜን ወሎ ደግሞ ወልዲያ ፤ ሐራ እና ቆቦ ከተሞች ነው።
ሰሞኑን ከነቀምት ወደ ባህርዳር መስመር በሚጓጓዙ አውቶብሶች ውስጥ ተፈናቃዮች ከወትሮው በርከት ብለው እንደታዩ የዐይን ምስክሮች ለዋዜማ ተናግረዋል።
ከኦሮሚያ ክልል አባይን ተሻግረው ወደ ቡሬ ከተማ እና አካባቢው የደረሱ ተፈናቃዮች በየመንገዱ እና በየእምነት ቤቶች ያለመጠለያ ሜዳ ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል።
“ከአርባ አመት በፊት የደርግ መንግስት ከተለያዩ አውራጃዎች ወደ ምእራብ ኦሮሚያ ወስዶ ካሰፈረን በኋላ አገራችን ነው ብለን ፤ ሀብት እና ንብረት አፍርተን ፤ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ተዋልደን ፤ ድረን ዛሬ አገራችሁ አይደለም ውጡ ስንባል የምንሄድበት አጣን ። አማራ ናችሁ ወደ አማራ ሂዱ ሲሉን ወደ አማራ ክልል መጥተን የምንወድቅበት አጣን” ሲሉ ለዋዜማ እንባ እየተናነቃቸው ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት የተፈናቃዮቹን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ መረጃ እያሰባሰበ መሆኑን አስታውቋል። የደቡብ ወሎ ዞን ከአንድ ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢው መድረሳቸውን ተናግሯል።
“ብዙ ተፈናቃዮች ከአርባ አመት በፊት ጥለውት የሄዱትን ቀበሌ ብቻ ሳይሆን ወረዳው ማን እንደሚባል እንኳ ሊያውቁ ባለመቻላቸው አማራ ክልል ከገቡ በኋላ ከነቤተሰቦቻቸው በየጎዳናው ፈሰዋል” የበታች የአስተዳደር እርከን ላይ ያሉ የሀይቅ ከተማ ሹም እንደነገሩን ።
በተጠጋንበት ቤተ ክርስቲያን እና በየመስጂዱ ህዝቡ እያዋጣ የሚችለውን ያህል እየረዳን እስካሁን ጦም አላደርንም ፤ ቢሆንም በመንግስት በኩል ግን እስካሁን የተደረገልን ድጋፍ የለም ይላሉ ተፈናቃዮቹ።
ሌላው ከዚያው ከምእራብ ወለጋ ወደ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ባምባሴ ወረዳ የተሻገሩ የአማራ ተወላጆች ተመሳሳይ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ለዋዜማ ተናግረዋል።
ወደ ወረዳው የታጣቂዎች ሰርገው ስለሚገቡ ሁሌ ስጋት መኖሩን ተናግረው ወረዳው ተፈናቃዮቹን ለመርዳት እና ለመደገፍ ቀርቶ ከአካባቢው እንድንወጣ በተደጋጋሚ እየገፋን ነው ሲሉ ነው ብለዋል ። [ዋዜማ ራዲዮ]