ዋዜማ ራዲዮ- ጥር15 2011 ዓም ነበር ከህግ እና መመርያ ውጭ ግዥ በመፈፀም የሀብት ብክነት ፈፅመዋል በሚል የወንጀል ድርጊት ነበር የጥረት ኮርፖሬት የቀድሞ ሀላፊዎች እና የኢህአዴግ የቀድሞ ባለስልጣናት የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡

አቃቤ ህግ የመሰረተባቸውን ክስ ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓም ተቀብለው ለ1 አመት ያህል በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ አቶ በረከት ስምዖን እና በመዝገቡ የተካቱት አቶ ታደሰ ካሳ ጥፋተኛ በተባሉባቸው አንቀፆች ዛሬ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡

አቃቤ ህግ በመሰረተው ክስ ዱየት ቢቬሬጅ ለተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ባልተገባ ዋጋ ማለትም 50 ነጥብ 14 በመቶ የሚሆነውን የአክሲዮን ድርሻውን በ90 ሚልዮን ዶላር እንዲሸጥ የተደረገ ሲሆን ይህም የጥረት ኮርፖሬትን ጥቅም የሚነካ ነው በማለት የሚተነትን ክስ ነበር፡፡

ይህን ተከትሎም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ኮርፖሬቱ ማግኘት የሚገባውን የ1.8 ቢሊየን ብር በላይ ጥቅም አስቀርተውበታል ወይንም እንዲጎዳ አድርገዋል የሚሉ እና ሌሎችም የሙስና ወንጀል ድረጊት በክስ መዝገቡ አካቶ ነበር ፡፡

ይህን ለማመሳከርም አቃቤ ህግ የሰው እና ሰነድ ማስረጃዎቹን በችሎት ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በወሰነላቸው መሰረትም ተከሳሾቹ ክሳቸውን ለመከላከል ሞክረዋል፡፡

ሆኖም የአቃቤ ህግ ማስረጃዎች ክሱን በሚገባ የሚያስረዱ ሆነው አግኝቻቸዋለው የያለው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ረፋድ ላይ በተሰየመበት ወቅት የተከሳሾቹን የጤና ሁኔታ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቻን እና ለመንግስት እና ለህዝብ ያገለገሉ መሆናቸውን እንደ ቅጣት ማቅለያ በመውሰድ በአቶ በረከት ስምዖን ላይ የ6 አመት ኑ እስራት እና የ10ሺህ ብር ቅጣት ሲያስተላልፍ በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ ደግሞ 8 አመት እና 15ሺህ ብር ቅጣት አስተላልፎባቸዋል [ዋዜማ ራዲዮ]