FM Demeke Mefonen- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግስት በበርካታ ሀገራት ያሉ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ፅህፈት ቤቶች የሚሰሩ ሰራተኞች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ማዘዙን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች አረጋግጣላች።


ባለፉት ቀናት ከአራት መቶ በላይ ደብዳቤዎች ተፅፈው በተለያዩ ሀገራት ላሉ የዲፕሎማሪክ ስራተኞች መድረሳቸውን ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። መንግስት ሰራተኞቹን የጠራው በአዲስ የዲፕሎማሲ አደረጃጀት ላይ የተዘጋጀውን መዋቅር ለመተግበር መሆኑም ተነግሯል።


ከሶስት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ መንግስት ካሉት ሀምሳ ዘጠኝ ኤምባሲዎች ግማሽ ያህሉን ለመዝጋት ማቀዱን በፓርላማ ባደረጉት ገለፃ ላይ ጠቅሰው ነበር።


አዲሱ የዲፕሎማሲ አደረጃጀት ላይ የሀገሪቱን ጥቅሞች ለማስከበር ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ በሆነ መንገድ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን የሚቻልበትን መንገድ ላይ ያተኮረ መሆኑን በሂደቱ ከተሳተፉ አንድ ዲፕሎማት ስምተናል።በተለይ ሀገሪቱ ካላት ውስን የውጪ ምንዛሪ ከፍተኛ በጀት በማውጣት ያሏትን ኤምባሲዎች ስታንቀሳቅስ መቆየቷንና አሁን ግን በገንዘብም በዲፕሎማሲያዊ ዉጤትም ሌላ አማራጭ መሞከር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል ብለውናል ዲፕሎማቱ።

የሀገሪቱን ግማሽ ያህል ኤምባሲዎች በመዝጋት ሀሳቡ ላይ አንዳንድ ተቃውሞ መኖሩንም ተነግሯል።
አሁን ከተጠሩት የዲፕሎማቲክ ስራተኞች መካከል የመንግስታቱ ድርጅት የኒውዮርክ ሚሲዮን እና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሁም ሎስ አንጀለስና ሜኒሶታ ቆንስላ የሚሰሩ ከአርባ አምስት በላይ ሰራተኞች ይገኙበታል። [ዋዜማ ራዲዮ]