Kenya President Uhuru Kenyatta
Kenya President Uhuru Kenyatta

ዋዜማ ራዲዮ- በምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር ኬንያ እኤአ በ2008ቱ ምርጫ ሳቢያ በተቀሰቀሰው መጠነ-ሰፊ ግጭት የአሁኑ ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው እጃቸው እንዳለበት ተጠርጥረው ጉዳያቸው ለዓለም ዓቀፉ ፍርድ ቤት ከተመራ ወዲህ የሀገሪቱ ምርጫ ዓለም ዓቀፍ ትኩረት የሚስብ ሆኗል፡፡ ሀገሪቱ በሚቀጥለው ነሐሴ የምታካሂደው ብሄራዊ ምርጫም ከወዲሁ ውጥረት የተሞላበት ሆኗል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት የምርጫ ህጉ እንዲሻሻል እና የምርጫ ኮሚሽኑ ሃላፊዎች ከስልጣናቸው እንዲነሱ የጠየቁት ተቃዋሚዎች አደባባይ ወጥተው ተከታታይ ተቃውሞ ሲያሰሙ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ግጭት ተፈጥሮ ሕይወት ጠፍቷል፡፡

ወዲያው ግን ምዕራባዊያን ዲፕሎማቶች እና የሐይማኖት አባቶች ጣልቃ ገብተው መንግስትን እና ተቃዋሚዎችን በማደራደራቸው ውጥረቱ ሊለዝብ ችሏል፡፡ በድርድሩ ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጣ ኮሚቴ ነባሩን የምርጫ ህግ በጋራ ስምምነት ለማሻሻል ችሎ ነበር፡፡ ሰሞኑን ግን ስልጣን ላይ ያለው የፕሬዝዳንት ኡሁሩ መንግስት ከስምምነቱ ውጭ በረቂቅ ህጉ ላይ አዳዲስ አንቀጾችን ጨምሮ ስላጸደቀው ውዝግቡ እንደገና አገርሽቷል፡፡ የትላልቅ ብሄሮች የሃይል አሰላለፍ ከፍተኛ ሚና ያለባቸውን ምርጫዎችን በማካሄድ በምትታወቀው ኬንያ ፉክክሩ ከወዲሁ በውጥረት ታጅቦ ተጧጡፏል፡፡

ለመሆኑ መንግስትን እና ተቃዋሚዎችን የሚወዛገቡት የምርጫ ህጉ ምን ይዘት ቢኖረው ነው? ኬንያ በምርጫ ውዝግብ ሳቢያ ለዳግም የብሄር ግጭት እና አለመረጋጋት ትዳረግ ይሆን? በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ቢከሰት በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሰላም ላይ ምን አንድምታ ይኖረዋል? የሚሉትን ጥያቄዎች ከወዲሁ መነሳት ያለባቸው ናቸው፡፡ ቻላቸው ታደሰ ያዘጋጀው ዝርዝር እነሆ

 

በኬንያ ከወራት በፊት ኮርድ የተሰኘው የተቃዋሚዎች ኅብረት የ2013ቱን ምርጫ እንዲጭበረበር ያደረጉት የምርጫ ኮሚሽኑ ሃላፊዎች ከሃላፊነታቸው ካልተነሱ እና የምርጫ ህጉ ካልተሻሻለ በመጭው ነሐሴ በሚደረገው ምርጫ ድጋሚ እንደሚጭበረበር በማስጠንቀቅ ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ ጊዜ ጸጥታ ሃይሎች ሃይል በመጠቀማቸው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ተቃዋሚዎች የኡሁሩ ኬንያታን መንግስት በከባድ ሙስና እና ጎሰኝነትን መንግስታዊ መርሁ በማድረግ ይከሱታል፡፡

ያሁኑ ውጥረት እንደገና የተቀሰቀሰው መንግስት ከተቃዋሚዎች ጋር በጋራ ስምምነት የተደረሰበትን ረቂቅ የምርጫ ህግ ባለፈው ታህሳስ መጨረሻ ለፓርላማው ሲያቀርብ አዳዲስ አንቀፆችን አካትቶ በማቅረቡ ነው፡፡ የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መንግስት ዕረፍት ላይ የነበረውን የታችኛውን ፓርላማ ባስቸኳይ አስጠርቶ ነበር አዳዲሶቹን አንቀፆች ያካተተውን ረቂቅ ህግ በጥድፊያ ያጸደቀቀው፡፡ ህጉ ለፓርላማው ሲቀርብ ተቃዋሚዎች ምክር ቤቱን ረግጠው ቢወጡም ገዥው የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ፓርቲ የመቀመጫ ብልጫ ስላለው ረቂቅ ህጉን ከመጽደቅ ሊያስቀሩት አልቻሉም፡፡ ህጉን በፍርድ ቤት ለማስቀየር ከመሟገት ባሻገር የአደባባይ ተቃውሞ በያዝነው ሳምንት እንደሚጠሩም ሲዝቱ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ ግን ከተለያዩ አካላት በረቂቅ ህጉ ላይ እንዳይፈርሙ የተደረገባቸውን ግፊት ገሸሽ አድርገው በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ፈርመውበት ህግ ሆኗል፡፡

አንደኛው አዲስ ማሻሻያ በምርጫው ወቅት የድምጽ መስጫ ኤሌክትሮኒክ ማሽኑ ቢበላሽ መራጮችን የመመዝገብ እና ድምጽ ሰጭዎችን የመለየት ስራ በሰዎች አማካኝነት ሊከናወን የሚችልበትን ዕድል ይከፍታል፡፡ ሌላኛው አወዛጋቢ ማሻሻያ ደሞ ኤልክትሮኒክ ዘዴው ችግር ካጋጠመው የምርጫ ውጤት ከምርጫ ጣቢያዎች ወደ ማዕከል በሰዎች የእጅ ምዝገባ ሊተላለፍ እንደሚችል የሚፈቅድ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ ሁለቱ ማሻሻያዎች የተጨመሩት የምርጫ ኮሚሽኑ ለአሰራር አመቺነት በሚል እንዲካተቱ ሃሳብ ስላቀረበ መሆኑን ሲከራከር ተቃዋሚዎች ግን ገዥው ፓርቲ ምርጫውን ለማጭበርበር እንዲመቸው ከምርጫ ኮሚሽኑ ጋር በማሴር ያካተታቸው ማሻሻያዎች ናቸው ሲል ይሟገታል፡፡ ፕሬዝዳንቱ በበኩላቸው ኤሌክትሮኒክ ዘዴ ለውጭ ሳይበር ጥቃት ሊጋለጥ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ይሰማል፡፡ ገዥው ፓርቲም ሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ሽፋን ስለሌላቸው በኤሌክትሮኒክ መሳሪያ ላይ ብቻ መተማመን አስቸጋሪ ነው በሚለው መከራከሪያው ገፍቶበታል፡፡

ተቃዋሚዎቹ ግን “ኤምፔሳ” የተሰኘውን በኢንተርኔት በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚሰራውን የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴ በመላ ሀገሪቱ እየሰራ አይደለም ወይ? በማለት የማሽን ብልሽት እንደ ምክንያት መቅረቡን አይቀበሉትም፡፡ ኮሚሽኑ የተመዘገቡ ድምጽ ሰጭዎችን ማንነት አጣርቶ ለገዥው ድርጅት መረጃ እንደሰጠ ስለሚጠራጠሩ የህጉ ማሻሻያ ሀገሪቱን ለከፋ ብጥብጥ ይዳርጋታል በማለት እያስጠነቀቁ ነው፡፡ የጋራ ኅብረት የፈጠሩ ስድስት ያህል ተቃዋሚ መሪዎች እና አባሎቻቸው ረቡዕ ዕለት ባደረጉት ስብሰባ ግን የአደባባይ ተቃውሞውን ከጥቂት ቀናት በኋላ ለሚጀመረው የመራጮች ምዝገባ መጠነ-ሰፊ ቅስቀሳ በማድረግ ተክተውታል፡፡

ሁለቱም ወገኖች የብሄር ውጥረትን ሊቀሰቅሱ ወይም ሊያባብሱ የሚችሉ ከረር ያሉ ቃላትን መለዋወጥ ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ ታዛቢዎች እንደሚሉት የ2013ቱ ምርጫ እንደተጭበረበረ የሚቆጥሩት ተቃዋሚዎች የዘንድሮውን ምርጫ በዋዛ የሚያልፉት አይመስሉም፡፡ በተለይ አንጋፋው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ዕድሚያቸው በመግፋቱ ሳቢያ በሌላ ምርጫ የማይወዳደሩ መሆናቸው የነሐሴውን ምርጫ የሞት ሽረት ትግል አድርጎታል፡፡ ከወዲሁ ደጋግመው ምርጫው ካልተጭበረበረ በስተቀር የኬንያዊያንን ይሁንታ እንደማገኝ አንዳች ጥርጥር የለኝም ማለታቸው ደሞ የፖለቲካውን ሙቀት ያጋለው ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ፓርቲ ከአጋር ፓርቲዎች ጋር በቅርቡ ውህደት ስለፈጸመ ምርጫውን ለማሸነፍ ቆርጧል፡፡ በዚያ ላይ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ሀገሪቱን የመሩት ገና ላንድ የምርጫ ዘመን ብቻ ነው፡፡

የምርጫው ረቂቅ ህግ ተቃዋሚዎችን እንደዚህ ያሳሰባቸው በቀጠናው የዴሞክራሲ፣ የመረጋጋት እና የዳበረ ኢኮኖሚ ማዕከል ተደርጋ የምትወሰደው ኬንያ ካሁን በፊት በምርጫ ውዝግብ ሳቢያ መጥፎ ትዝታ ያላት መሆኗ ነው፡፡ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ወደ ስልጣን ያመጣው የ2013ቱ ምርጫ ደም አፋሳሽ ከነበረው የ2008ቱ ምርጫ በተቃራኒ ሰላማዊ ሆኖ ቢያልፍም የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር እና የአሁኑ የዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ግን ምርጫው ተጭበርብሯል ከሚለው ክሳቸው ፍንክች አላሉም፡፡ አሁን የግጭት ስጋት ያንዣበበውም በዚሁ ያልደረቀ ቁስል ሳቢያ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡

የኬንያ፣ የኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱማሊያ ምጣኔ ሰላም እና ሐብት ከሞላ ጎደል የተሳሰረ ስለሆነ የኬንያ ውስጣዊ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በቀጠናው ሀገራት ላይ አሉታዊ አንድምታዎች ይኖሩታል፡፡ ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ኢኮኖሚያዊ ትስስር ቀስ በቀስ ጠንክሯል፡፡ በቅርቡ ከተጠናቀቀው የኢትዮጵያው ጊቤ ሦስት ሃይል ማመንጫ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመግዛት የማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ላይ ናት፡፡ ሁለቱ ሀገሮች በመሰረተ ልማት ዕጦት እና ድህነት የተራቆተውን የጋራ ድንበራቸውን ለማልማት የጋራ የልማት መርሃ ግብር ነድፈው ለመተግበር ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ኬንያ ደህና የነዳጅ ዘይት ክምችት ካገኘች ወዲህ ደሞ በሰፊው አምርታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተሟሟቀ ዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡ በተለይ ላሙ የተሰኘውን ገና በጅምር ግንባታ ላይ ያለውን አዲሱን ወደቧን ማጠናቀቅ ከፈለገች የፕሬዝዳንት ኡሁሩ መንግስት ከፍተኛ ሙዓለ ንዋይ ማፍሰስ ግድ ይለዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደሞ ግዙፉ ፕሮጄክት የማያወላዳ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ይፈልጋል፡፡ ጎረቤት ሀገሮችም ወደቡን ለመጠቀም ትብብር ሊያሳዩ የሚችሉት የተራጋጋች ኬንያን ማየት ከቻሉ ብቻ ነው፡፡

በምርጫ ውዝግብ ሳቢያ ብሄርን መሰረት ያደረገ ግጭት ወይም የተራዘመ ፖለቲካዊ ቀውስ እና አለመረጋጋት ከተፈጠረ በእነዚህ ሁሉ ሰፋፊ ውጥኖች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡

ኬንያ በቀጠናው ድርጅት ኢጋድም ሆነ በምዕራባዊያን አጋሮቿ ለቀጠናው ሰላም ባላት አይተኬ አስተዋጽኦ እና በደቡብ ሱዳን ባደረገችው የአሸማጋይነት ሚና አመኔታ የሚሰጣት ሀገር መሆኗ አይካድም፡፡ በተለይ አንዳንድ የፓርላማ አባላት በሱማሊያ ከአልሸባብ ጋር እየተፋለሙ ያሉት የሀገሪቱ ወታደሮች እንዲወጡ እና ኬንያ ድንበሯን ዘግታ የአልሸባብን ጥቃት እንድትመክት ፖለቲካዊ ግፊት ሲያደርጉ ስለኖሩ በምርጫ ሰበብ ፖለቲካዊ ቀውስ ቢከሰት ሃሳቡ ሰፊ ድጋፍ እንዲያገኝ ሰበብ እንዳይሆን ስጋት አሳድሯል፡፡ ኬንያ ከሱማሊያ ወታደሮቿን ካስወጣች ደሞ በአሚሶም ሰላም ጥበቃ እና በሱማሊያ እጣ ፋንታ ላይ ከባድ ጫና የሚፈጥር መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በተናጥል ያዘመተችውን ጦሯን ከሱማሊያ ካስወጣች ወዲህ በአሚሶም ላይ ጫና እንደበዛበት ወታደራዊ ታዛቢዎች ይስማሙበታል፡፡

በሌላ በኩል ግን በምርጫ ሰበብ ግጭት እንዳይቀሰቀስ ወይም ቢቀሰቀስም ኬንያ ከሌሎቹ የቀጠናው ሀገራት በተለየ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሲቪል ማህበራት እና የሐይማኖት ተቋማት ስላሏት በጎ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ የሚለው ተስፋ ጠንከር ያለ ነው፡፡ ምዕራባዊያን ዲፕሎማቶችም ካሁን ቀደም እንዳደረጉት  መጠነ-ሰፊ ግጭትን በማርገብ ረገድ እገዛ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ ተቃዋሚዎች የ2013ቱን ምርጫ የመሩት የምርጫ ኮሚሽኑ ሃላፊዎች እንዲነሱ በጠየቁት መሰረት በፓርላማው ውሳኔ በቅርቡ የስራ ጊዚያቸው ተቋርጦ የአዲስ ሃላፊዎች ቅጥር በመካሄድ ላይ መሆኑ ውጥረቱን ለማለዘብ እንደረዳ ተቃዋሚዎች ሳይቀሩ ሲገልጹ ይሰማል፡፡ የምርጫ ኮሚሽኑ ሰሞኑን በጋና ምርጫ እንደተደረገው የድምጽ ሰጭዎችን አሻራ መያዝን እንደ መጠባበቂያ ለመጠቀም መወሰኑን ማስታወቁ ደሞ የተቃዋሚዎችን ቅሬታ ሊያለዝብ እንደሚችል ታዛቢዎች ዕምነት ጥለዋል፡፡ ተቃዋሚዎችም ይህንን በመረዳት ይመስላል በያዝነው ሳምንት አስበውት የነበረውን መጠነ-ሰፊ የአደባባይ ተቃውሞ ላልተወሰነ ጊዜ አዘግይተውታል፡፡

አሁን ስድስት ወራት ብቻ የቀሩት ምርጫ ብሄርን መሰረት ያደረገ የሥልጣን እና ሃብት ክፍፍል የተንሰራፋባትን ሀገር የወደፊት ዴሞክራሲ፣ ሰላም እና የምጣኔ ሐብት ዕድገት እንደሚወስን አያጠያይቅም፡፡ ኬንያ በተለይ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ምትክ አልባ ሚና ያላት ከመሆኑ አንጻር የአፍሪካ ኅብረት፣ ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ እና መገናኛ ብዙሃንም ለምርጫው የሚያደርሰውን ሂደት በአንክሮ እየተከታተሉት እንደሆነ ይታመናል፡፡ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች እና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ከፊታቸው የተጋረተውን ፈተና በማለፍ ኬንያ ዴሞክራሲ፣ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ብርቅ ለሆነበት አፍረካ ቀንድ የተስፋ ምልክት ሆና እንድትዘልቅ ያስችሏት ይሆን? በመጭዎቹ ጥቂት ወራት የሚታይ ይሆናል፡፡