የለገሀሩ የ 50 ቢሊየን ብር ፕሮጀክት እንዲከለስ ተወስኗል

የወንዝ ዳር ፕሮጀክቱን ማን ይገንባው በሚለው ዙሪያ መግባባት የለም

Legahare sample design (Not actual design)

ዋዜማ ራዲዮ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዲስ አበባ ላይ በድምሩ 79 ቢሊየን ብር የሚያወጡ የመዝናኛ እና የቤት ልማት ፕሮጀክቶችን ይፋ አድርገዋል። አንዱ 50 ቢሊየን ብር ወጭ የሚደረግበት ለገሃር የተቀናጀ የመኖሪያ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ስፍራ ልማት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ 29 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻዎች ማልማት ፕሮጀክት ነው።

የለገሃር የተቀናጀ የመኖሪያ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ስፍራ ልማት ህዳር 10 ቀን 2011 አ.ም በይፋ የማስጀመርያ ስነ ስርአት ላይም ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። በወቅቱ ለገሀርን አጠቃሎ 36 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው ይህ ፕሮጀክት አራት ሺ የመኖሪያ ቤቶች፣ ባለ አራትና አምስት ኮከብ ሆቴሎችና ሌሎች መዝናኛዎች እንደሚገነቡለት ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ የሚያርፍበት ቦታ አሁን እየኖሩ ያሉ 1,600 አባወራዎች እዛው ቤት ተሰርቶላቸው ይኖራሉ ተብሏል። ፕሮጀክቱ ለአዲስ አበቤዎች መልካም ስጦታ እንደሆነም የአዲስ አበባ አስተዳደርና ጠቅላይ ሚንስትሩ ያሰምሩበታል። ፕሮጀክቱም በአቡዳቢው ኤግል ሂልስ ኩባንያ ነው የሚሰራው : መንግስትም በ50 ቢሊየን ብር ፕሮጀክቱ ውስጥ ከሀያ በመቶ በላይ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል።

ኤግል ሂልስ የተባለው የአቡዳቢ ኩባንያ ከዚህ ቀደም ለህዝብ ከተነገረው የፕሮጀክት ይዘትና አላማ የተለየ የራሱን ንድፍ አዘጋጅቶ ስራ ለመጀመር ተሰናድቶ ነበር። ኩባንያው ያቀረበው እቅድ የከተማዋንም ሆነ የህዝብን ፍላጎት ከግምት ያላስገባ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ይናገራሉ።

በተለይ የቀረበው ንድፍ ለገሀር ላይ ያሉ በርካታ አመታት ያስቆጠሩትን እና በቅርስነት ሊመዘገቡ የሚገባቸውን የምድር ባቡር ጣብያንና ጣልያን በወረራ ጊዜ ወስዶ የመለሰውን የአንበሳውን ሀውልት ከግምት ውስጥ ያላስገባ እና ከእይታ ውጭ ያደረጋቸው ሆኗል። ባለሙያዎች እንደሚሉት ኤግል ሂልስ ፕሮጀክቱን ሲቀርጽ እነዚህን ቅርሶች አጉልቶ ማውጣት ይችል ነበር። ስለዚህም የፕሮጀክቱን ይዘትና ዲዛይን የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እንዲያዩና እንዲከልሱት ተወስኗል። ኤግል ሂልስ ግን በዚህ ውሳኔ ደስተኛ አይደለም።

በፕሮጀክቱ ዲዛይንና አተገባበር ዙሪያ የተነሱ ትችቶችን ተከትሎ ኤግል ሂልስ የለገሀሩ ፕሮጀክት ላይ ዲዛይኑ በሀገር ውስጥ አርክቴክቶች እስኪከለስ ድረስ እንቅስቃሴዎችን እንዲያቆም መደረጉን ሰምተናል።

ኤግል ሂልስ በሰርቢያ ቤል ግሬድ ወደ ስራ ሲገባ በህዝብ ከፍተኛ ተቃውሞም ተነስቶበት ነበር።ኩባንያው ዱባይ ውስጥ ከሰራቸው ህንጻዎችና ግብጽም አዲስ ልታስገነባው ካሰበችው ፕሮጀክት ላይ እየተሳተፈ ያለና ልምድ ያለው ነው።

29 ቢሊየን ብር ወጪ ይጠይቃል የተባለው የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማትም እንዲሁ ከጅምሩ እክል ገጥሞታል። በፕሮጀክቱ ሳቢያ አስር ሺህ ያህል አባወራዎችን ከፕሮጀክቱ አካባቢ ማንሳት ታቅዷል። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ዝግጅት አልተደረገም። ስለዚህ በልማቱ ሳቢያ የሚነሱትን ወገኖች የት ለማስፈር እንደታቀደ ወጪውን ማን እንደሚሸፍን የታወቀ ነገር የለም።

በሌላ በኩል ፕሮጀክቱን የሚሰራው ኩባንያ ማነው? የሚለው ውዝግብን ፈጥሯል።
የጣልያኑ ቫርኔሮ የልማት ስራው በምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ይፋ የተደረገ ሰሞን መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር። ዘግየት ብሎ ግን የማን ኩባንያ እንደሆኑ ያልታወቁ የቻይና ዜጎች ስራው በእኛ ነው የሚሰራው በማለታቸው በተፈጠረ የጥቅም ግጭት መስተጓጎል ተፈጥሯል። መንግስትም ቫርኔሮ ፕሮጀክቱን እንዲሰራ ትእዛዝ ከሰጠው በሁዋላ እንዲያቆም አድርጓል። የጣልያኑ ኩባንያም አቤቱታ ማሰማቱን ሰምተናል።

ምናልባት በዚህ ፕሮጀክት ላይ ቻይኖች ብቅ ያሉት ገንዘብን ለፕሮጀክቱ ያመጣሉ ተብሎ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። ለዚህ የወንዞች ልማት ፕሮጀክት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የአምስት ሚሊየን ብር ራትን የመቀመጥ ቅስቀሳ ተጀምሮ እንደነበር የሚታወቅ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]