Addis Ababa City Hall, head of the adminstration
Addis Ababa City Hall, head of the adminstration

ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ!

ገረመው እባላለሁ፡፡ እሳት የላስኩ ደላላ እንደሆንኩ እግዜርም ሰይጣንም ያውቃሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ መሆኔን ድሪባ ኩማም ያውቃሉ፡፡ ውሎና አዳሬ ብሔራዊ ቴያትር መሆኑን ገዢም ሻጭም ያውቃል፡፡ ‹‹ላየን ባር›› ቤቴ፤ ‹‹ቴሌ ባር›› ግዛቴ ነው፡፡ አልረጋም፡፡ ካዛንቺስ ነው ሲሉኝ ሳሪስ፣ ቀበና ነው ሲሉኝ ባምቢስ….፡፡ሄሄሄ…ደላላ ምን ቀልብ አለው ብለው ነው!?

ለማንኛውም ጆሮ ያውሱኝ፡፡ ከሰሞኑ የቃረምኩትን በፍጥነት ወደርስዎ አደርሳለሁ፡፡

ይቅርታ ያርጉልኝ! ቅልብልብ የምለው ወድጄ አይደለም፡፡ ጊዜው ነው፡፡ ወቅቱ ለሰከነ አይሆንማ፡፡ እኛ በስክነት ያቀናናትን ከተማ ጩሉሌዎች ባንድ ሌሊት አፍርሰው ሰሯት! ለኛ የነበሩ ትናንት ተላላኪ፣ መሽቶ ሲነጋ ሆኑብን አስመጪና ላኪ…ይላል ዳርጌ፡፡ እውነቱን ነው፡፡ሄሄሄ…ይልቅ አይፍዘዙ ጌታው! መፍጠን ነው የሚያዋጣው!

እጅህ ከምን አሉኝ?

ትናንት ከትናንተ በስቲያ ማዘጋጃ ነበርኩ፡፡ ባህል አዳራሽ፡፡ ከደላላ በስተቀር ዝር ያለ ሐብታም አልነበረም፡፡ እኔና እኔን ከመሰሉ ከፍተኛ የመሬት ደላሎች በቀር በስፍራው እንኳን ሰው ወፍ አልነበረም፡፡ አጫራጮች እንኳን ፖስታ ይከፍቱ የነበረው እያዛጉ ነበር፡፡ አፋቸውን እየከፈቱ ሚሊዮን ዲጂት የተጻፈበትን ፖስታ መክፈት በውነት ክብረ ነክ ነው፡፡ለሦስት ተከታታይ ቀን ጠዋት ሦስት ሰዐት ገብተን ማታ ሦስት ሰዐት ወጣን፡፡

‹‹ለምን›› አሉኝ?

ለ21ኛው የመሬት ችብቻቦ ነዋ፡፡ ሶስት ሰአት ተገብቶ ሶስት ሰአት የሚወጣው ሌላ ለምን ይመስሎታል፡፡ ለፊንፊኔ መሬት ካልሆነ፡፡

እኔ ምለው! ሰው ሚሊዮን ብር ያፈሰሰበትን ጨረታ ባይታደም እንኳ እንዴት ‹‹ማን አሸነፈ›› ብሎ አይጠይቅም፡፡ የኔ ደንበኞች እኔ ደውዬ ማሸነፋቸውን እስክነግራቸው ድረስ መጫረታቸውን እንኳ ዘንግተውት ነበር ብል ማጋነን አይሆንም፡፡

ለማንኛውም የፊንፊኔ አፈር ወርቅ እንደሆነች አስመስክራለች፡፡ በዚህ ዙር ፊንፊኔ ለአንድ ካሬ የ66ሺ ብር ክብረወሰን አስመዝግባለች፡፡

በቅድሚያ የ21ኛው ዙር የመሬት ሊግ ተሳታፊ የነበሩትን ክፍለከተሞች ከዚህ በማስከተል እዘረዝራለሁ፡፡

ቦሌ- ለጨረታ ያቀረባቸው ቦታዎች ብዛት – 6፣   ጉለሌ- ለጨረታ ያቀረባቸው ቦታዎች ብዛት – 4፣ የካ- ለጨረታ ያቀረባቸው ቦታዎች ብዛት -37፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ-ለጨረታ ያቀረባቸው ቦታዎች ብዛት – 24፣ አቃቂ ቃሊቲ- ለጨረታ ያቀረባቸው ቦታዎች ብዛት 41፣ ኮልፌ ለጨረታ ያቀረባቸው ቦታዎች ብዛት 11፣ ልደታ- ለጨረታ ያቀረበው ቦታ ብዛት አንድ፡፡ አራዳና ቂርቆስ ለዚህ ዙር ዉድድር ሚኒማ ባለማሟላታቸው አልተሳተፉም፡፡

ጌታዬ! መሬት ነው ሁሉን የሚዘውር፡፡ ስለመሬት ሲወራ እህ ብለው ይስሙ፡፡

ከተአምረኛው ልደታ እጀምራለሁ፡፡

ልደታ ክፍለከተማ በዚህ ዙር አንድ ቦታ ብቻ ለጨረታ ያቅርብ እንጂ የዙሩን የመሬት ክብረወሰን የሰበረው እርሱ መሆኑን ስነግርዎ በታላቅ አግራሞት ተውጬ ነው፡፡ በወረዳ 8 ልዩ ስሙ ‹‹ሰንጋ ተራ›› አካባቢ 1043 ካሬ ስፋት ያለው ቦታ ድሀ ሰፋሪዎች እንዲነሱ ከተደረገ በኋላ ለጨረታ ቀርቦ 66ሺ ብር በካሬ ተሸጧል፡፡ አዎ የማይታመን ነው አይደል?

ይረጋጉ ጌታዬ! ግለሰብ አይደለም ይህንን ያበደ ዋጋ ለሽራፊ መሬት ያቀረበው፡፡ ቡና ባንክ ነው፡፡ ቡና ባንክ ገና የኤቲኤም ማሽን እንኳ ያልተከለ ባንክ ይኸው ሰማይ የሚቧጥጥ ፎቅ ለመስራት ይሽቀዳደማል፡፡ ለዚህ ቦታ ፀሐይ ኢንሹራንስ 41ሺ ብር በማቅረብ 2ኛ፣ አባይ ባንክ 32ሺ ብር በማቅረብ 3ኛ፣ ደቡብ ግሎባል 10ሺ አንድ መቶ ብር በማቅረብ አራተኛ ሲሆኑ የመጨረሻውን አስቂኝ ዋጋ ያቀረበው እናት ባንክ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ስንት ሰጠ አይበሉኝ ጌታው፡፡ እናት ባንክ የመሬት ሳይሆን የሂል ጫማ ዋጋ ነው ያቀረበው፡፡ የመረጃ እጥረት ያለበት ይመስላል፡፡

ለማንኛውም ቡናዎች ድል ቀንቷቸዋል፡፡ ታዲያ ድሉ ከታላቅ ኃላፊነትና ግዴታ ጋር ነው፡፡ ሰሞኑን በሚፀድቅ ማስተር ፕላን መሠረት በሰንጋ ተራና አካባቢው ቡና ባንክ ሊገነባ የሚችለው ትንሹ የፎቅ ርዝመት G+19 ሲሆን ከዚህ በላይ ልስራ ካለ ግን ሰማዩን ጨርቅ ያርግለት ብለዋል የመስተዳደሩ የመሬት ባለሞያዎች፡፡

እዚህ ጋ ለአፍታ ቆም እንላለን፡፡ ለመሆኑ ቡና ባንክ ይህንን ቦታ በስንት ብር ገዛው ለሚለው ምላሽ ለማግኘት የስልኬን የሂሳብ ማስያ ለመጠቀም እገደዳለሁ፡፡  68, 838, 000 ብር (ስልሳ ስምንት ሚሊየን ስምንት መቶ ስልሳ ስምንት) መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ከነወለዱ አከፍላለሁ ካለ የዚህን ሂሳብ 20 በመቶ በ10 ቀናት ዉስጥ ከፍሎ ቀሪዉን በ30 ዓመት ይገፈግፋል ማለት ነው፡፡ ወለዱ ታዲያ የዋዛ አይምሰልዎ!

ባንክስ ባንክ ነው፡፡ ከባንክ የማይተናነሱ ግለሰቦች መኖራቸውን ሰምተው ይሆን? ይህንን ለመረዳት ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እናመራለን፡፡

የሼክ አላሙዲንም ሆነ የፋጡማ ሮባ፣ የሙለርም ሆነ የአፍሪካ ኅብረቱ ዋና ፀሐፊ መኖርያ ቤት የሚገኘው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እንደሆነ ያውቁ ይሆን? ሳር ቤት ገብሬል ድሮም የሞጃ ክልል ነው፡፡ ካለፈው ዙር የተራረፉ 5 ቦታዎች ለጨረታ ቀርበው ነበር፡፡ ቤቶቹ የሚገኙት ካስማ ሪልስቴት ከሚገነባቸው ቅንጡ አፓርትመንቶች ፊትለፊት ነው፡፡ ቦታዎቹን ያሸነፉት ሰዎች ደግሞ አጋጣሚ ሆኖ ወደፊት የሚጎራበቱት የመን ኤምባሲን ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አጠገቡ የሚገኝ ኪስ ቦታ ለየመን ኤምባሲ ስለተሰጠ ነው፡፡ የመኖቹ አገራቸው ጦርነት ሆነ መሰለኝ ቦታው ላይ እስካሁን ግንባታ አልጀመሩበትም፡፡

ታዲያ እነዚህ 5 ቦታዎች ስንት ብር የቀረበባቸው ይመስልዎታል? ከ41ሺ እስከ 48ሺ ለካሬ፡፡ ደግሞ እኮ የቦታዎቹ ስፋት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ከ350 ካሬ እስከ 450 ካሬ የሚሰፉ አነስተኛ ኪስ ቦታዎች ናቸው፡፡ ከነዚህ ኪስ ቦታዎች ዉስጥ ሁለቱ ወደ አቶ ካሳ ልጆች ገብተዋል፡፡ ለሁለት ቦታዎች ተመሳሳይ ዋጋ ያቀረቡት ወንድማማቾቹ መሳይ ካሳና አሰፋ ካሳ ለካሬ 48110 ብር በማቅረብ የቤተሰብ ታሪክ ሰርተዋል፡፡ ከአቶ ካሳ ቤተሰብ ለቦታዎቹ በትንሹ 40 ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል ማለት ነው፡፡ አቶ ካሳ ማን እንደሆኑ ለማወቅ ያደረኩት የስልክ ጥሪ ዉጤት ሳያስገኝ ካርዴ አልቋል፡፡

በዚህ ዙር ሌላም ታሪክ የሰራ የሞጃ ቤተሰብ አለ፡፡ የዱጉማ ሁንዴ ልጆች ድል ቀንቷቸዋል፡፡ አያት አደባባይ ወደ ጣፎ በሚወስደው አስፋልት መንገድ የሚገኙ ሰፋፊ ይዞታዎችን አሸንፈዋል፡፡ ሚሊዮንና ዘላለም የሚባሉት የሟቹ ባለሀብት የአቶ ዱጉማ ልጆች አንድ በዘሚሊ ቀለም ፋብሪካ ስም፣ ሌላውን ደግሞ በዲኤች ገዳ ብረት ፋብሪካ ስም ያሸነፉ ሲሆን ለሁለቱም ቦታዎች 35ሺ ብር ለካሬ ሜትር ሰጥተው ነው የጠቀለሏቸው፡፡ ልጆቹ የታላቁን የአቶ ዱጉማን ሌጋሲ እያስቀጠሉ ይመስላል፡፡

በዙሩ ከፍተኛ ዋጋ ይሰጠዋል ተብሎ የተገመተው በኮድ ቁጥር 11587 የተመዘገበው ስፍራ ሲሆን አያት አደባባይን ታኮ የሚገኝ አይን ቦታ ነበር፡፡ ለዚህ ቦታ ቶሞር ተሬዲንግ 35680 ብር በመስጠት ጣፋጭ ድል ተቀዳጅቷል፡፡ ቶሞር ያሸነፈው ወይዘሮ ሙና በድሩ የተባሉ ባለሐብት ካቀረቡት ዋጋ የአመስት ብር ጭማሪ ብቻ በመስጠት መሆኑ የዙሩ አስገራሚ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡

የ21ኛው ዙር የመሬት ጨረታ አማካይ ዋጋ 21ሺ ብር ለካሬ ሲሆን ዝቅተኛው ዋጋ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተመዘገበውና የውብዳር ወሰኔ የተባሉ ወይዘሮ ለ750 ካሬ ቅይጥ ቦታ ያቀረቡት 3,777 ብር ነው፡፡ የየካ መሬቶች በአመዛኙ የተሸጡት ከ28ሺ ብር በላይ ሲሆን የንፋስ ስልክ አብዛኛዎቹ ቦታዎች ለካሬ ከ30ሺ ብር በላይ ቀርቦባቸዋል፡፡

ጉለሌ ክፍለከተማ ብዙም በመሬት ሊዝ ጨረታ ተሳትፎ ያልነበረው ሲሆን በዚህ ዙር ያቀረባቸው 4 ቦታዎች ከፍተኛ ዋጋ አስገኝተውለታል፡፡ በመለስ ዜናዊ በተሰየመው ፓርክ አካባቢ የሚገኙት ሁሉም ቦታዎች ከ20ሺ ብር በላይ ለካሬ ቀርቦባቸው ተጠናቀዋል፡፡ ይህ የተጋነነ ዋጋ በፍጹም ለአካባቢው ይቀርባል ያለ አልነበረም፡፡ ብዙዎች ‹‹ጉለሌም እንደቦሌ!›› ብለው እንዲገረሙ ሆነዋል፡፡

የፊንፊኔ መሬት ዋጋው ይረግባል ሲባል ብሶበታል፡፡ እነዚህ 30ና 40ሺ የሚቀርብባቸው ቦታዎች ብዙዎቹ ከሁለት ዓመት በፊት በካሬ 5ሺ ብር የሚያልቁ የነበሩ መሆናቸው አገሪቱ ምን ያህል አለመረጋጋት ዉስጥ እንደሆነች የሚያመላክት ነው፡፡ አሁን ብዙ ሺ ሄክታር መሬት በመሐል ፊንፊኔ ከድሀ እየጸዳ በመሆኑ ባለሀብቶቹ ሳይራኮቱ መሬት ያገኛሉ የሚል ተስፋን አሳድሯል፡፡ የቤቶች ግንባታ ኤጀንሲ በበኩሉ ለ40-60 የሚሆኑ ቦታዎችን መስተዳደሩ ሊያቀርብልኝ ባለመቻሉ ቤት መገንቢያ አጥቻለሁ እያለ ሲያማርር ተሰምቷል፡፡

ጌታው! ለዛሬው ይብቃን፡፡ ለ22ኛው ዙር እመለሳለሁ፡፡

ገረመው ነኝ ከላየን ባር!