ጨመቅ – ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሀገሪቱ ከውጪና ከውስጥ የገጠሟትን የፀጥታና የደህንነት ችግሮች ለመቀልበስ ከፍተኛ ዋጋ ጭምር በመክፈል እየታገለ ያለ ተቋም ቢሆንም በ 2010 ዓም በሀገሪቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ በተለያየ ሀላፊነት የመደባቸው የራሱ ሰራተኞች ለከፋ ቀውስ ዳርገውት ቆይተዋል። ሁለት መቶ ያህሉ አሁን ታግደዋል። ዝርዝሩን ያንብቡት

[ዋዜማ ራዲዮ] የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ከ2010 አ.ም ማለትም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጦች ከመጡ በኋላ እስከ አሁን ድረስም ፈተና ውስጥ ያለ ተቋም ሆኖ ቀጥሏል። ጥቅምት 24 2013 አ.ም በፌደራል መንግስትና በሕወሓት መካከል ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ተቋሙን በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ ያሉት የቀድሞ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህ በደህንነት መስሪያ ቤቱ ላይ ሰፊ ለውጥን ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ሰምተናል።

ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮቿ መስማት እንደቻለችውም አቶ ተመስገን ወደ ሀላፊነት ከመጡ በኋላ የደህንነት መስሪያ ቤቱ አሁን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር በሆኑት አቶ ደመላሽ ገብረሚካኤል በሚመራበት ጊዜ ከከፍተኛ እስከ በታች አመራር የነበሩ ከ200 በላይ ሰዎች ደሞዝ እየተከፈላቸው በግዳጅ ፍቃድ እንዲወጡ ተደርገዋል።


ፍቃድ እንዲወጡ ከተደረጉት በተጨማሪም በምክትል ዳይሬክተር ደረጃ ያሉት ሀላፊዎች በሌሎች አመራሮች እንዲተኩ የተደረጉም አሉ። ፍቃድ እንዲወጡ የተደረጉትን በመቶ የሚቆጠሩ አመራሮችን ወደነበሩበት ስራ ይመለሱ አይመለሱ ግልጽ የሆነ መረጃን ዋዜማ ራዲዮ ማግኘት አልቻለችም። ሆኖም በተቋሙ አመራሮች ላይ ይህ አይነት ውሳኔ የተወሰነው የደህንነት መስሪያ ቤቱ የሀገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ማስከበር በሚቻልበት ደረጃ ተግባሩን ማከናወን ችሏል ተብሎ ስላልታመነበት መሆኑን መረዳት ችለናል።

በተለይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከመጣበት ከ2010 አ.ም በሁዋላ በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ ከላይ ከላይ የተወሰኑ የአመራር ለውጦች ተደረጉ እንጂ መሰረታዊ የሆኑ ስር ነቀል ለውጦችን ማድረግ ባለመቻሉ ሀገሪቱን ዋጋ በማስከፈል መቀጠሉ በተደጋጋሚ በተደረጉ ግምገማዎች ተነግሯል።

በብሄራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ውስጥ ካሉ አመራሮች ውስጥ ለቀጠራቸው ሀገርና መንግስት ታማኝ ሆኖ ከመስራት ይልቅ ለቡድኖች አገልጋይ መሆን ሲስተዋል መቆየቱን የግምገማ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። በሀገሪቱ በንፁሐን ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እንዲፈፀም፣ ታጣቂ ቡድኖች ላይ እርምጃ እንዳይወሰድ መረጃ የማሾለክና የተሳሳተ መረጃ በመሰጠት የደህንነት መስሪያቤቱ የከፋ ጥልፍልፍ ውስጥ ገብቶ መቆየቱም ተነግሯል።

በደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ በኢትዮጵያ ተከስተው በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ውስጥ ተሳታፊ ናቸው በሚል ጥርጣሬ አሁንም እረፍት ወጥተው ደሞዝ የሚከፈላቸው 27 ሰዎች ስም ዝርዝርም ዋዜማ ራዲዮ ደርሷታል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተለያየ ጊዜ ንጹሀን ዜጎች ላይ ግድያ ሲፈጸም በዚህ ድርጊት ውስጥ እጃቸው አለበት ተብለው ከተጠረጠሩ የክልሉ ባለስልጣናት በተጨማሪ ጌታቸው ብርሀነ (ጌታቸው ታክሲ) የተባለ በብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ደህንነት እንዲመራ ሀላፊነት የተሰጠው ግለሰብ አሁን በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተሳትፏል በሚል ከስራ እንዲታገድ የተደረገ ነው።

ጌታቸው ብርሀነ በ2011 አ.ም በቁጥጥር ስር ውለው እስር ቤት ያሉ የቀድሞ የደህንነት መስሪያ ቤት ሀላፊዎችን ካልተያዙ የቀድሞ የደህንነት ሀላፊዎች መረጃ በማቀባበል የተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራት እንዲፈጸሙ ከፍተኛ ትብብር ሲያደርግ ቆይቷል በሚል ተወንጅሎ ጉዳዩ እየተጣራ ነው። ግለሰቡ ከስራ ቢታገድም ሌሎች እንቅስቃሴዎቹ ባለመታገዳቸው አሁንም በጥፋት ስራ ተሰማርቶ እንደሚገኝ የደህንነት መስሪያቤቱ ባልደረቦች ስጋታቸውን በተደጋጋሚ እየገለፁ ይገኛሉ።

 በተለይ መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ፖለቲከኞችና የቀድሞ የደህንነት መስሪያ ቤት ሰራተኞች እስር ቤት ካልገቡ ተባባሪዎቻቸው ጋር በጸጥታ አስከባሪና የደህንነት ሰራተኞች አማካይነት የስልክና መሰል ግንኙነት እንዲያደርጉ ትብብር እየተደረገላቸው መሆኑ በሀገሪቱ ሌላ የጸጥታ ችግር ሲፈጥር ይታያል።

በእስር ላይ ያሉት የቀድሞ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቀጥሎም የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ያሬድ ዘሪሁንን ጨምሮ የታሰሩ የቀድሞ የደህንነት ሀላፊዎች እንዲሁም ፖለቲከኛ ጃዋር መሀመድ ባሉበት እስር ቤት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ተገኝቶባቸው እንደነበር ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮች ማረጋገጥ ችላለች።

ከሰሞኑ ለጃዋር መሀመድ እስር ቤት ድረስ በመሄድ አራት ሲም ካርዶችን ሊሰጥ ሲል ተይዞ ፍርድ ቤት የቀረበው ግለሰብ ጉዳይም ከዚሁ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ምንጮቻችን ጠቁመውናል።

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አመራርና ሰራተኛ ሆነው በ2010 አ.ም ላይ ሀገራዊ ለውጥ ከመጣ በሁዋላ በተለያየ መንገድ ከሀገር የወጡ ግለሰቦችም ሀገር ውስጥ ካሉ ግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን የተለያዩ ጥፋቶችን ማቀናበር መቻላቸውንም አንድ የተመለከትነው ሰነድ ይጠቁማል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም እነዚህ አደገኛ እንቅስቃሴዎች ከመቆጣጠር ይልቅ ተባባሪ የሆኑ የደህንነት መስሪያ ቤት አመራርና ሰራተኞች መኖራቸውንም ነው የሰማነው።

አዲሱ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ያጋጠሙትን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት በርካታ እንቅስቃሴን ጀምረዋል።ከምክትል ዳይሬክተሮች ጀምሮ የአሰራር ክፍተት የታየባቸውን ከ200 በላይ አመራሮች ከስራ አንስተው መተካካትን ለመስራት በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው ።

የቀድሞው የኢህአዴግ አስተዳደር ኢትዮጵያን በሚመራበት ጊዜ ያለ አግባብ ከስራቸው ተባረው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የደህንነት ባለሙያዎችን የመመለስ ፍላጎት የነበረ ቢሆንም ጀነራል አደም መሀመድም አቶ ደመላሽ ገብረሚካኤልም መስሪያ ቤቱን በመሩባቸው ጊዜያት ያለ አግባብ የተባረሩትን ለመመለስ በቂ ሙከራ አልተደረገም። [ዋዜማ ራዲዮ]