(ዋዜማ)- የኬንያ ፖሊስ ከኢትዮጵያውያን ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዛሬ ጠዋት ፈተና ላይ ወድቆ ነበር። ፖሊስ በናይሮቢ ጫፍ በሚገኘው እና ካህዋ ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ ያመራው በአካባቢው ተደብቀዋል ስለተባሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በደረሳቸው ጥቆማ ነበር። ትላንት ማክሰኞ ምሽት ተገድሎ ከተገኘ የሞተር ሳይክል ታክሲ (ቦዳ ቦዳ) አሽከርካሪ አሟሟት ጀርባ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሉበት ብለው ያመኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የፖሊሶቹን በቦታው መገኘት አልወደዱትም። በመቶዎች የሚቆጠሩት ነዋሪዎች በቁጥር ጥቂት የሆኑትን ፖሊሶች በድንጋይ ከአካባቢው ለማባረር ጊዜ አልወሰደባቸውም። ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን የተረዳው የአካባቢው ፖሊስ አድማ በታኝ ፖሊሶችን ጨምሮ በመምጣት ጥይት ወደ ሰማይ እየተኮሰ የተቆጡትን ነዋሪዎች በመበተን የ23 ኢትዮጵያውያንን ነፍስ አድኗል።

የኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኬንያ ፖሊሶች መያዝ አዲስ ነገር አይደለም። አዲሱ ነገር “እስከ ጥይት መተኮስ የደረሰ ተቃውሞ ከነዋሪዎቹ እንዴት መጣ?” የሚለው ነው። “በኬንያ ፖሊስ ዘንድ ጥይት ወደ ሰማይ በመተኮስ ለህግ አልገዛ ያሉ ሰዎችን መበተን የተለመደ ነው። ይህ ግን የሚሆነው ፖሊስ በኃይል ሲበለጥ ነው” ይላል ጉዳዩን ለመዘገብ በቦታው የተገኘው የዴይሌ ኔሽን ጋዜጠኛ ለዋዜማ ሲናገር። “በዚህ ሁነትም የውጭ ዜጋዎችን ህይወት ለማዳን ወደ ሰማይ መተኮስ ነበረባቸው” ይላል። ነዋሪዎቹ ኢትዮጵያውያኑን እንዲጠረጥሩ ያደረጋቸው ሟች አሽከርካሪ በመጨረሻ የጫነው ተሳፋሪ ኢትዮጵያዊ ነበር መባሉ ነው። የሞቱ እውነተኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ማንም በእርግጠኝነት መናገር እንዳልቻለ ጋዜጠኛው ይገልጻል።

“ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ብዙውን ጊዜ ደቡብ አፍሪካን አልመው ኬንያን በመሸጋገሪያነት የሚጠቀሙባት በመሆኑ እና ብዙም እንቅስቃሴ ስለማያደርጉ ከነዋሪዎች ጋር እምብዛም ችግር ውስጥ አይገቡም” ይላል ጋዜጠኛው። “ነገር ግን እነርሱን ከሶማሌያውያን ጋር የማምታት እና በዚያም ምክንያት ኬንያ ከአልሻባብ ጋር ከገባችበት ውጥንቅጥ ጋር የማያያዝ ነገር አለ።”

በፖሊስ የተያዙትን ኢትዮጵያውያን ለማነጋገር የሞከረው ኬንያዊ ጋዜጠኛ የቋንቋ ችግር እንደገደበው ይገልጻል። ከስደተኞቹ አንዱ ግን ከአንድ ቀን በፊት ወደ አካባቢው መምጣታቸውን ነግሮታል። ጋዜጠኛው በዴይሊ ኔሽን ድረ ገጽ ካተመው ዜና ጋር ተያይዞ የወጣ ፎቶ እንደሚያሳየው ከስደተኞቹ አንዱ ከሀድያ ዞን ጃጁራ ከተማ የመጣ የ26 ዓመት ወጣት ነው። እርሱና ሃያ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ወደ ናይሮቢ ሲደርሱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደሚኖሩባቸው ኢስሊ እና ሀርሊንጋሃም ሳይሆን የተወሰዱት ከኢትዮጵያ ድንበር እስከ ናይሮቢ የሚዘረጋው መንገድ አካል በሆነው የቲካ ሱፐር ሃይዌይን ታክኮ ወደሚገኘው ካህዋ ነው።

“ኢስሊ እና ሀርሊንግሃም በኬንያ ጥገኝነት አግኝተው በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚዘወተር ነው። ካህዋ በአዘዋዋሪዎች አማካኝነት የሚመጡቱ የሚመርጡት ነው” ይላል ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ የሆነ ኬንያዊ ጋዜጠኛ። ከዚህ ቀደም በካህዋ ባለ እስር ቤት በርካታ ኢትዮጵያውያንን መመልከቱንም ይገልጻል።

ካህዋ ብቻ ሳይሆን ዳንዶራ እና ኡሞጃ የተሰኙ በአቅራቢያ የሚገኙ አካባቢዎችም ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ኬንያን በሚያቋርጡ ኢትዮጵያውያን የተወደዱ ናቸው። “አካባቢዎቹ ህዝብ የበዛባቸው ስለሆኑ ስደተኞቹ በቀላሉ እንዳይለዩ ያደርጋቸዋል። በዚያ ላይ ቤት ኪራይ ርካሽ ነው” ይላል የአዲስ አበባው ኬንያዊ ጋዜጠኛ። በካህዋ ብቻ 350 ሺህ ነዋሪዎች እንደሚኖሩ ይገመታል። በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ቁጥር መሰረት እስከ ታህሳስ 2008 ዓ ም ድረስ ብቻ በድርጅቱ የሚታወቁ 28 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በኬንያ ይኖራሉ።