Home Talking points Benegerachin Lay-Discussion የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈተና (Part 1)

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈተና (Part 1)

September 30, 2015 1
Share!
Addis Ababa University

Addis Ababa University

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች) ዛሬ ዛሬ የገዥው ፓርቲ ዋነኛ የምልመላ ማዕከላት ሆነዋል። በሀገሪቱ የስፈነው አፈና ምሁሩን ክፍል አፍ ከማዘጋት አልፎ ገለልተኛ የሚባሉትን ሳይቀር ለአገዛዙ እንዲንበረከኩ በረቀቀ መንገድ እየተተገበረ ነው ይሉናል ተወያዮቻችን። ገዢው ፓርቲ በምሁራኑ ደጃፍ እየተከለ ያለው መርዝ መድሀኒቱ በቅርብ ያለ አይመስልም። መምህራኑ ራሳቸው ያጫውቱናል አድምጡዋቸው

 One Comment

 1. ጃሊኒ በረከት October 1, 2015 at 1:14 am

  ሰላም ዋዜማዎች፣
  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉዳይ ከተነሣ ዘንድ እንዳልካቸውና አብርሃም ያላነሡዋቸውን ነጥቦች ላክል፡-

  1. ተማሪዎቻቸውን የመምረጥ ዕድል የሌላቸው ዩኒቨርሲቲዎች
  ዩኒቨርሲቲዎቻችን መሪዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ተማሪዎቻቸውንም በራሳቸው መመዘኛዎች የመምረጥ ዕድል የላቸውም፡፡ በቅድመ ምረቃ መርሐ ግብሮች ትምህርት ሚኒስቴር ይመድብልሃል፤ ታስተምራለህ፡፡ አለቀ፡፡ ተማሪውም ዩኒቨርሲቲውን ወደደው ወይም ጠላው መማር እስከ ፈለገ ድረስ የተሰጠውን ከመቀበል ውጪ አማራጭ የለውም፡፡ እንዲህ ያለ ጨቋኝ የትምህርት ሥርዓት በመካከለኛው ዘመን አውሮፓ እንኳ መገኘቱን እንጃ!

  2. ፖለቲካዊ ታማኝነት ላይ የሚያተኩረው ሥርዓት የፈጠረው አካዳሚያዊ ግልሙትና
  መምህራን ፖለቲካዊ ታማኝነታቸው ወይም አስተዳደራዊ ወገንተኝነታቸው ጥያቄ ውስጥ እስካልገባ ድረስ ያሻቸውን ቢያደርጉ ሀይ ባይ የለባቸውም፡፡ ለምሳሌ፣ የሕዝብ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ክፍል ባለመግባት፣ ተማሪዎችን በቅጡ ሳያስተምሩ ከባድ ፈተና በመፈተንና ዝቅተኛ ነጥብ በመስጠት የሚታወቁ እጅግ ብዙ መምህራን በግል ኮሌጆችና በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንድም ክፍል ሳይቀሩ፣ ተማሪዎችን ተንከባክበው በጥሩ ሁኔታ ሲያስተምሩ ይታያሉ፡፡ በዚህ አካዳሚያዊ ግልሙትና (academic prostitution) የተነሣ መደበኛ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ካለቻቸው ገቢ ላይ ቆጥበው፣ በሥራ የደከመ ሰውነታቸውን እንደምንም ታግሠው፣ ገንዘባቸውን ከፍለው የሚማሩ የማታ የሕዝብ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ በአስተማሪዎችና በአስተዳደሮች የሚፈጸመው ግፍ ይህ ነው አይባልም፡፡ (ለነገሩ የቀን ተማሪዎችም በወጪ መጋራት ሥርዓት ገንዘባቸውን ከፍለው ነው የሚማሩት፡፡) ይህ በተለይ እንደኮምፒውተር ሳይንስ ዓይነት ትምህርቶች ላይ እጅግ ገዝፎ የሚታይ ችግር ነው፡፡ ተጨማሪ ምሳሌ፣ በክረምት መርሐ ግብር የሚማሩ ተማሪዎች (ከየክልሎቹ የሚመጡ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን) በስምንት ሳምንት ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በምዝገባ ቢያንስ አንድ ሳምንት ይቃጠላል፤ በጋ ላይ “በርቀት ለተማሯቸው” ከአራት የማያንሱ ኮርሶች ማጠናከሪያ ለመስጠትና ፈተና ለመፈተን ተብሎ ተጨማሪ ቢያንስ ሁለት ሳምንታት ይቃጠላሉ (ይህ ሁሉ በጋ ላይ መጠናቀቅ የነበረበት ነገር ነው)፡፡ ሦስቱ ሳምንት ሄደ፤ አምስት ሳምንት ቀረን፡፡ ከቀሪ አምስት ሳምንቶች ውስጥ ሁለቱ ሳምንቶች የፈተና ናቸው፡፡ ሦስት ሳምንት ቀረ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ በእነዚህ ሦስት ሳምንቶች ውስጥ ነው በመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር 16 ሳምንት የሚወስዱ ኮርሶችን ተማሪ ተኮር በሆነ መልኩ አስተምሮ ማስመረቅ ይጠበቅበታል፡፡ የመደበኛ መርሐ ግብሩ ጉዳይም ከዚህ ብዙም የሚለይ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው፣ የዩኒቨርሲዎቹን የግማሽ ዓመት ወይም የሩብ ዓመት ሪፖርት ስንመለከት በሴሚስተሩ የመጀመሪያ ቀን ትምህርት እንደተጀመረ ይናገራል- “day one class one” ይሉታል በሪፖርት ቋንቋ፡፡ ይህ ግን ነጭ ውሸት ነው፡፡ አስተማሪዎቹ ቢገኙ እንኳ ተማሪዎቹ አይገኙም፤ ምክንያቱም ለምደዋል፡፡ በመጀመሪያው ቀን ትምህርት ተጀመረ ቢባል እንኳ ከዚያ በኋላ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው አስተማሪዎች ስሜስተሩን በአግባቡ ተጠቅመው ሥራቸውን አይሠሩም፡፡ ለምን ተብለው ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ “ዩኒቨርሲቲ በሚከፍለኝ ደሞዝ ብቻ ቤተሰብ ላስተዳድር አልችልም፡፡ ተጨማሪ ሥራ መሥራት አለብኝ” የሚል ነው፡፡ እርግጥ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ደመወዝ በከተማ ለመኖር ያስችላል ብሎ መናገር ቀልድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የአስተዳደሩና የመምህራኑ ንዝኅላልነት በተማሪዎች ላይ የሚያደርሰውን በደል ተገቢ አያደርገውም፡፡ እነዚህ አስተማሪዎች ጥቅማ ጥቅም ነክ የሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም “ልማታዊ ስብሰባ” ሲጠራ ግንባር ቀደም ተሰላፊዎች ናቸው፤ በቀላል ቁጥር ቁጥር የማይገመቱትም የፖርቲው አባላት ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም የአካዳሚ ሥራውን እርግፍ አድርገው ትተውት ዋና ሥራቸውን ፓርቲያዊ ሥራ አድርገውታል፡፡ ሥራቸውን በአግባቡ የሚሠሩ፣ የኑሮ ችግር ሳይረታቸው፣ ፖለቲካዊ መገፋቱ ሳይበግራቸው አካዳሚያዊ አስተዋጽዖ ለማድረግ ደፋ ቀና የሚሉ መምህራን ደግሞ ልማታዊ ስብሰባው ላይ ባለመገኘታቸው ብቻ ማስጠንቀቂያ ይላክላቸዋል፤ ማሳሰቢያ ይነገራቸዋል፡፡ (በነገራችን ላይ፣ ስብሰባ ሲጠራ መምህራን ቀሪ መቆጣጠሪያ (አቴንዳንስ) ላይ እንዲፈርሙ ይደረጋል፡፡ የኮሌጅ ዲኖችና ዳይሬክተሮች ያን ጊዜ የሚኖራቸው ዋና ሥራ ይህን የቀሪ መቆጣጠሪያ ወረቀት ማዞር ነው፡፡ የአንድ ኮሌጅ ዲን (ዶ/ር እገሌ) የአቴንዳንስ ወረቀት ይዞ ታች ላይ ሲል ይታያችሁ!)

  3. የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለልማታዊ መምህራን ብቻ
  ፖለቲካዊ አመለካከታቸው “ልማታዊ” ያልሆኑት መምህራን ላይ የሚደርሰው ውስጥ ውስጡን የሚካሄድ የማግለልና የመበደል ስልት ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ልዩ ልዩ ሰበብ በመፍጠር ፖለቲካዊ አመለካከታቸው ልማታዊ ያልሆኑ ሰዎች እንዳይቀጠሩ ይደረጋል፡፡ ይህ በተለይ በረዳት ምሩቃን ቅጥር ላይ ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው፡፡ በልዩ ልዩ መንገዶች ዕድገትና ጥቅማ ጥቅም ይነፈጋቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ የኢሕአዴግ አባል ነገር ግን አካዳሚያዊ ዐቅሙ ዝቅተኛ የሆነ መምህር በአካዳሚያዊ ዐቅማቸውና አስተዋጽዖዋቸው የሚበልጡትን ቀድሞ ቤት ያገኛል፡፡ (ቤት በከተማ- በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ- ምን ማለት እንደሆነ ከግለሰብ ቤት ተከራይቶ መኖር የሚፈጥረውን ሥነ ልቡናዊና አካላዊ ሥቃይና ቀውስ የቀመሰ ይገባዋል፡፡) ፖለቲካዊ አመለካከታቸው ያልተወደደላቸው ሰዎች የእነርሱን ሙያ በሚጠይቅ ነገር ላይ እንኳ እንዳይሳተፉ ይደረጋል፡፡

  4. የሥርዓተ ትምህርት ወጥነት
  ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች በሙሉ የቅድመ ምረቃ መርሐ ግብሮቻቸው በአንድ ዓይነት ሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) እንዲያስተምሩ ተደርጓል፡፡ የዚህ ሥርዓተ ትምህርት ምንጩ ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ከማዕከል ወደ ታች በእዝ ሰንሰለት የሚወርድ የሥርዓተ ትምህርት “ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት” መሆኑ ነው፡፡ ይህም የተሻለ ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ ረገድ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይፎካከሩ በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶታል፡፡ መምህራንንም አስንፏል፡፡ አንድ ዲፓርትመንት የሚያስተምርበትን ሥርዓተ ትምህርት የመቀየር ሥልጣን የለውም፡፡ ለማሻሻል የሚችልበት እድል ራሱ በጣም ጠባብ ነው፡፡

  ይህ ሥርዓተ ትምህርት ሞጁላራይዜሽን የሚባል አቀራረብን ይከተላል፡፡ በዚህ አቀራረብ መሠረት ደግሞ አብዛኛውን ሥራ የሚያከናውኑት ተማሪዎች ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ በራሱ ክፉ አልነበረም፡፡ ነገር ግን አቀራረቡ ሌሎች በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ ለምሳሌ፣ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ባለው አሰቃቂ የማስተማሪያ መጻሕፍት እጥረትና የተማሪዎች ያልዳበረ የንባብ ልምድ የአንድን ኮርስ ዐበይት ክፍሎች ተማሪው በራሱ ይወጣቸዋል ብሎ ማሰብ ቅዠት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ ይህ አቀራረብ በውስጡ የተከታታይ ምዘናን (continuous assessment) የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግም መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ዩኒቨርሲቲዎች ወጥ የሆነ የውጤት አሰጣጥን (fixed grading scale) የሚከተሉ ሆኗል፡፡ ተማሪዎች ከ90 በላይ ነጥብ ማምጣት ካልቻሉ A አይሰጣቸውም፡፡ ይሁን እንጂ፣ ተማሪዎቹ 90 እንዲያመጡ አስተማሪው ስንት የክፍል ሥራ ሰጥቷቸው ነበር? ምን ያህል ምዘናስ አካሂዷል? የሚለውን እየተከታተለ የሚመለከት የለም፡፡ በዚህ የተነሣ የተማሪዎች ውጤት አሰጣጥ ፍጹም ኢፍትሐዊ ሆኖ ይታያል፡፡ አንድ አስተማሪ ሁለት የቤት ሥራዎችና አንድ የማጠቃለያ ፈተና ሰጥቶ ለተማሪዎቹ ውጤት ይሰጣል፡፡

  ከሞጁላራይዝድ ሥርዓተ ትምህርት ጋር አብረው ከቀረቡ ነገሮች መካከል ሌላኛው አጠቃላይ ውጤታቸው ዝቅተኛ የሆነባቸውን ተማሪዎች ደጋግሞ በመፈተን እንዲያልፉ ማድረግ ነው፡፡ በሥርዓተ ትምህርቱ መሠረት አጠቃላይ ውጤቱ/ቷ Fx የሆነ ተማሪን አስተማሪዋ የማጠናከሪያ ትምህርት ሰጥታ፣ ድጋሚ ፈተና አውጥታ የመፈተን ግዴታ አለበ/ባት፡፡ በዚህ የድጋሚ ፈተና ጊዜ ተማሪው/ዋ ድጋሚ Fx ውጤት ካመዘገበ/ች አስተማሪዋ እንደገና ፈተና አውጥታ ትፈትናለች፡፡ አሁንም ተማሪዋ ያንኑ ዝቅተኛ ውጤት ካመጣችስ? አስተማሪዋ ለሦስተኛ ጊዜ ፈተና አውጥታ ትፈትናለች፡፡ አስተማሪዎች ይህንን ተደጋጋሚ ፈተና የማውጣት ድካም ለማምለጥ ሲሉ ተማሪዎች የማፊለያ ውጤቶችን እንዲያገኙ ያደርጋሉ፡፡ የዩኒቨርሲቲዎች አስተዳደሮች ይህን አካሄድ “ማብቃት” ይሉታል፡፡ ለምን ይህን አካሄድ እንደመረጡት ሲጠየቁም ተማሪዎች ከግቢ ወጥተው ሪአድሚሽን በመጠየቅ የሚያባክኑትን ጊዜ ለማዳን ነው ይላሉ፡፡ እውነቱ ሲታይ ግን በአንድ በኩል የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለመሸከም ዐቅማቸው የማይፈቅድላቸውን ተማሪዎች እንደምንም ብሎ በማስመረቅ ስታቲስቲክስ ለማሳደግ ይመስላል፡፡ የፓርቲው ሰዎች ይህንን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለጥቂት ምርጦች (elites) ብቻ ሳይሆን ለብዙኃኑ ማዳረስ (massification) ስላለብን ነው ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እጅግ እየወረደ የመጣውን የትምህርት ጥራት ለመሸፈን የሚደረግ ጥረት ሆኖ ይታያል፡፡ ልክ አንደኛ ደረጃ ላይ እንደሚታየው በነጻ የማሳለፍ ዘመቻ መኾኑ ነው፡፡ አንድ ገጽ ጽሑፍ በቅጡ አንብበው መረዳት የማይሆንላቸው፣ ስማቸውንም ሆነ ዜግነታቸውን በትክክለኛ ፊደሎች የማይጽፉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወይም ምሩቃን ቢበረክቱ አይግረማችሁ፡፡

  ይህ አቀራረብ ትምህርት ሚኒስቴር በሀገር ዐቀፍ ደረጃ እንዲተገበር ሲያውጅ የዩኒቨርሲቲ ሹመኞች ለዩኒቨርሲቲ መምህራን በጉዳዩ ሥልጠና እንዲሰጡ ታዝዘው ሥልጠና ተካሂዶ ነበር፡፡ እኔ በነበርሁበት ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚደንት እና አንድ የትምህርት ኤክስፐርት የተባሉ ሰው ነበሩ አሠልጣኞች፡፡ ሥልጠናው ብዙም ሳይገፋ ከመምህራኑ ጉልሕ ተቃውሞ ገጠመው፡፡ አቀራረቡ ለምን እንደማይሠራም ትችቶች መወርወር ጀመሩ፡፡ ይሄኔ፣ የትምህርት ኤክስፐርቱ “You know, I am here because I am paid.” ብለውን አረፉት፡፡ መምህራኑም ወዲያው ጥያቄያቸውን አቆሙ፡፡ በቃ! ከዚህ በኋላ ምን ጥያቄ ያስፈልጋል? ትምህርት ሚኒስቴር ግን ወደድንም ጠላንም ተገበረው- ዕድሜ ለዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት፡፡

  5. የዩኒቨርሲቲ ሥልጣን የዘውጌ ፖለቲካን ለማራመጃነት
  ይህ እጅግ በጣም አስከፊው የኢሕአዴግ ዘመን የተከለብን በሽታ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ አብርሃም ደሞዝ፣ አምሳሉ አክሊሉን፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ ዮናስ አድማሱ፣ ፈቃደ አዘዘ፣ ደበበ ሰይፉ፣ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፣ የመሳሰሉ ምሁራንን ያፈራው ጥንታዊው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ዲፓርትመንት (በውስጡ የአማርኛ፣ የኦሮምኛና የትግርኛ ዩኒቶች ነበሩት) በቢፒአር ስም ተበትኖ የአማርኛ ዲፓርትመንት፣ የኦሮምኛ ዲፓርትመንት እና የትግርኛ ዲፓርትመንት እንዲሆን የተበየነው በዋናነት የዘውግ ፖለቲካን በመጠቀም ሥልጣን ይፈልጉ የነበሩ ዘውጌዎች ተጽዕኖ ነበር፡፡ ድሮ በአንድ የዲፓርትመንት ሊቀመንበር ቢሮ፣ በአንድ ጸሐፊ፣ በአንድ ተላላኪ ይሠሩ የነበሩ ሥራዎች ሦስት የዲፓርትመንት ሊቀመንበሮች፣ ሦስት ጸሐፊዎች ሦስት ተላላኪዎች አስፈለጉት፡፡ በሌሎች ዲፓርትመንቶች ውስጥም እንዲሁ ከፓርቲው ወይም ከፓርቲው ሹማምንት ጋራ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ለራሳቸው ሹመት የሚሆኑ ክፍሎችን ለማመቻቸት ሲሠሩ ነበር፡፡ በዚህ የተነሣ በዩኒቨርሲቲው ተደጋጋሚ የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብሮች በልዩ ልዩ ተቋማት ሥር ሲሰጡ ይታያል፡፡

  ሌላ ምሳሌ፣ ከአንድ የዩኒቨርሲቲው አስተማሪ እንዳገኘሁት መረጃ፣ በ2007 ዓ.ም. በአአዩ ሰላሌ ካምፓስ የአማርኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ትምህርታቸውን ጀምረው የነበሩ የቅዳሜና የእሑድ ክፍል ተከታታይ ትምህርት 42 ተማሪዎች ቁጥራችሁ አነስተኛ ስለሆነ መርሐ ግብሩ አትራፊ አይደለም ተብለው ትምህርት እንዲያቆሙ ተደርጎ ነበር፡፡ ሌሎች የትምህርት መርሐ ግብሮች ከነበራቸው የተማሪ ቁጥር አኳያ ጉዳዩ ሲጣራ ግን ምክንያቱ የተማሪ ቁጥር ማነስ አለመሆኑ ተገለጠ፡፡ ተማሪዎቹ ትምህርት እንዲያቆሙ የተደረገው ቁጥራቸው በማነሡ ሳይሆን “በኦሮሚያ ምድር እንዴት አማርኛ?!” የሚል ከአንዳንድ የዩኒቨርሲቲው ሹመኞች ዘንድ የበቀለ እጅግ ደካማ አመለካከት ነበር፡፡ ተማሪዎቹ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት እስከ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ድረስ ሄደው አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡ ውጤት ማግኘታቸው ግን አልተሰማም፡፡

  6. የማይነር ትምህርት የተከለከሉባቸው ዩኒቨርሲቲዎች
  በዘመነ ኢሕአዴግ በከፍተኛ ትምህርት ላይ ከተፈጸሙ ትልልቅ በደሎች አንዱ የኮመን ኮርሶችና የማይነር ትምህርት እንዲቀር መደረጉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎቻችን እየተማሩ ያሉ ተማሪዎች በሦስት ዓመታት ውስጥ በአንድ ዲሲፒሊን ያሉ ዋና ዋና ነገሮችን ለመዳሰስ ከመሞከር ውጪ ከሌሎች ዲሲፒሊኖች ጋር በመተዋወቅ የዕውቀት አድማሳቸውን የሚያሰፉበት በር ተዘግቶባቸዋል፡፡ ማይነር ትምህርት ገንዘብ አባካኝ ነው በሚል ፈሊጥ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲቀር መደረጉ ተማሪዎችን የአንድ ዲሲፒሊን እሥረኛ አድርጓል፡፡

  ከኮመን ኮርሶች ውስጥ እንደ ታሪክና ፍልስፍና ያሉ ለወጣቶች አእምሮ መዳበር ዐቢይ አበርክቶ የሚኖራቸው ኮርሶች ጠፍተው ሎጂክና እንግሊዘኛ ብቻ ቀርተዋል፡፡ በፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ የፕሬዚደንትነት የመጨረሻ ዓመታት ችግሩን የተገነዘቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጎምቱ መምህራን እነዚህንና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በሙሉ ዲፓርትመንት ሳይለይ ከሒሳዊ አስተሳሰብ፣ ከዓለምና ሀገርኛ ሥነ ጥበብና ሥነ ጽሑፍ፣ ከሀገር ዐቀፍ ታሪክ፣ የሳይንስ ፍልስፍና (the philosophy of science)፣ የሰው ልጅ አናቶሚ፣ የቋንቋ የባህልና የማኅበረሰብ ረቂቅ ትሥሥርን፣ ወዘተ. የሚተዋወቁባቸው የጋራ ትምህርቶች ሥርዓተ ትምህርት አሰናድተው ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ፣ ዕቅዱ ተግባር ላይ መዋል ሳይጀምር እርሳቸው ከቦታው ተነሡ፡፡ ስንት የተለፋበት ዕቅድም ከእርሳቸው መነሣት ጋር አብሮ ኮቴው ተዘነጋና ወሬው ሁሉ ቢፒአር ሆነ፡፡

  7. የወጣት ምሁራን ኩብለላ
  ሀገራዊ የፖለቲካ ጭቆናው እየከፋ መምጣት፣ በክፍል ውስጥ በተማሪ ካድሬዎችና የዘውግ ፖለቲከኞች፣ በግቢ ውስጥ ደግሞ በልማታዊ ሹመኞችና አስተማሪዎች የተነሣ አካዳሚያዊ ነጻነት እንደሰማይ መራቁ፣ የኢኮኖሚያዊ ችጋሩ መባባስ ብዙ ወጣት መምህራንን ተስፋ አስቆርጧል፡፡ ለኮንፈረንስ፣ ለሴሚናር ወይም ለዐጭር ሥልጠና ወይም ለድኅረ ምረቃ ትምህርት በሄዱበት የማይመለሱ እጅግ ብዙ ናቸው- በአንድ ወቅት ከአንድ ወዳጄ ጋር ባደርግነው ቆጠራ ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ብቻ በአንድ ዓመት ከ20 በላይ ወጣት አስተማሪዎችና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ወጥተው ቀርተዋል፡፡ እነዚህ እንግዲህ እኛ የምናውቃቸው ብቻ ናቸው፡፡ የማናውቃቸው ስንት ሄደው ይሆን? በተለይ እነዚህ ዓለም ዐቀፍ የትምህርት ተቋማት እና ጉባኤዎች ላይ የሚሳተፉ ወጣት ምሁራን በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ ካሉት መካከል የተሻሉት በመሆናቸው ሀገራዊ ጉዳቱ ቀላል እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ አሁን አሁንማ ለመድነውና እገሌ እንትን ሀገር ለጉባኤ ሄዷል ከተባለ ያን ሰው ተመልሶ ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት እንግዳ እየሆነብን ነው፡፡ አሁን ባለው አያያዝም ይህ ነገር በቀላሉ የሚቆም አይመስልም፡፡ ፓርቲው እንደሆነ ምሁራን ሲሄዱ “እፎይ ተገላገልን!” እንጂ “ጎደለብን!” አይልም፡፡

  8. የማስትሬትና የዶክትሬት ፋብሪካዎች

  የከፍተኛ ትምህርትን ለማስፋፋት በርካታ ከድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤቶች የወጡ መምህራን ያስፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ሲባል በዋናነት አአዩ ከክልል ዩኒቨርሲቲዎች የሚመጡ መምህራንን በድኅረ ምረቃ መርሐ ግብሮች የማሠልጠን ኃላፊነት ወስዷል፡፡ አንዳንድ የክልል ዩኒቨርሲቲዎችም የማስተርስ ዲግሪ መርሐ ግብሮችን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ከድኅረ ምረቃ መርሐ ግብሮቹ ምሩቃን አብዛኛው ስለዲሲፒሊኖቻቸው ዕውቀት ሳይይዙ የሚወጡ ናቸው፡፡ ሞጁላራይዝድ በሆነው የድኅረ ምረቃ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ኮርሶች የሚሰጡት በተከታታይ ነው- ማለትም አንዱ ሲያልቅ ሌላኛው ይቀጥላል፡፡ አንድ የድኅረ ምረቃ ኮርስ በአንድ ወር ያልቃል፡፡ መስከረም አንድ ኮርስ፣ ጥቅምት አንድ ኮርስ፣ ኅዳር አንድ ኮርስ፣ ታኅሣሥ አንድ ኮርሥ እያለ ይሄዳል፡፡ በአንድ ወር ውስጥ ተማሪዎች ምን ዓይነት ስፔሺያላይዜሽን ሊያዳብሩ እንደሚችሉ ይታያችሁ፡፡ ከዚያ የማተርስ ቴሲስ ወይም የፒኤችዲ ዲሰርቴሽን ይጽፋሉ፡፡ በቃ! ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብንና ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብን ለይታ የማታውቅ የሥነ ጽሑፍ መምህርት፣ አርጀንቲና አፍሪካ ውስጥ ያለች ሀገር ናት ብላ የምትከራከር የታሪክ መምህርት፣ Applied Linguistics ብላ አስተካክላ መጻፍ የማትችል የApplied Linguistics ዶ/ር፣ ሥነ ምግባር የጎደላቸው የሥነ ዜጋ አስተማሪዎች፣ ወዘተ. በየዩኒቨርሲቲው ይሞላሉ፡፡ (በነገራችን ላይ እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው በሙሉ በእውነት የተከሠቱ ነገሮች ናቸው እንጂ እኔ የፈጠርኳቸው ምሳሌዎች አይደሉም፡፡)

  የተማሪዎቹ አማካሪዎች ተብለው ከሚመደቡት ሰዎች መካከልም በቀላል ቁጥር የማይገመቱት ተማሪዎቹን ለማማከር ፈጽሞ ጊዜ የላቸውም፡፡ ወይም ቢሮ የላቸውም፡፡ ቢኖራቸውም ቢሯቸው ውስጥ አይገኙም፡፡ ቢገኙም የተማሪዎችን ወረቀት ቶሎቶሎ አይቶ መመለስ አይሆንላቸውም፡፡

  Reply

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Tweets by @Wazemaradio