social iconsዋዜማ ራዲዮ- የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና መቃረብን ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በክልሎች የማህበራዊ ድረ-ገጾች እንዳይታዩ ታገዱ፡፡እገዳው በሞባይል ኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረጉ የማህበራዊ ድረ-ገጾች ጉብኝትን ይጨምራል፡፡

ቅዳሜ ረፋዱን በአዲስ አበባ የሚገኙ ኢንተርኔት ካፌዎች አንዳንዶቹ ደንበኞቻቸውን “ኮኔክሽን የለም” እያሉ ሲመለሱ የተስተዋሉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ “ፌስ ቡክ እንደማይሰራ፣ ኤሚይል እና ኢንተርኔት ግን መጠቀም እንደሚቻል” ለተጠቃሚዎች ሲገልጹ ታይተዋል፡፡ የዋዜማ ዘጋቢዎች በተዘዋወሩባቸው የኢንተርኔት ካፌዎች ፌስ ቡክ ብቻ ሳይሆን ትዊተርም አገልግሎት እንደማይሰጥ ታዝበዋል፡፡

በግንቦት ወር ሊሰጥ ታቅዶ የነበረው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ሾልኮ ወጥቶ በድረ ገጾች በመለቀቅ ምክንያት ፈተናው መሰረዙ የሚታወስ ሲሆን በዚህ ሳምንትም ተመሳሳይ የፈተና መሰረቅ ጭምጭታዎች በተማሪዎች ዘንድ ሲናፈስ ቆይቷል፡፡ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ተፈታኝ ተማሪዎች የፊታችን ሰኞ ይጀመራል ተብሎ ከሚጠበቀው ፈተና መካከል ናቸው የተባሉ የጥያቄ ወረቀቶችን ቫይበር እና ዋትስ አፕ በመሳሰሉ የመገናኛ አፕሊኬሽኖች ሲዘዋወሩ እንደተመለከቱ ገልጸዋል፡፡

አንድ ተፈታኝ ከረቡዕ ጀምሮ በተማሪዎች የ”ዋትስ አፕ ግሩፕ” ላይ የእንግሊዘኛ ጥያቄዎችን የያዘ ፒ.ዲ.ኤፍ ፋይል መመልከቱን ይናገራል፡፡ ተማሪዎች የተመለከቱት ፈተና “ወደ ማተሚያ ቤት ከመላኩ በፊት ተሰርቆ የወጣ ነው” መባሉን ይናገራሉ፡፡ የኬሚስትሪ እና ሂሳብ ፈተናዎች በተመሳሳይ ተሰርቀው መሰራጨታቸው ሲናፈስ ቆይቷል፡፡ ዛሬ ለንባብ የበቃው “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ስለፈተና መሰረቅ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስትሩን አቶ ሽፈራ ሽጉጤን ጠይቆ “ውሸት ነው፤ የራሳቸውን የውሸት የፈተና ወረቀት አዘጋጅተው ነው ወሬውን ያሰራጩት” ብለዋል፡፡