Home Current Affairs የኦሮሞ የተማሪዎች ተቃውሞ "የመሪ ያለህ" ይላል! ኢህአዴግስ ከተቃውሞው ምን ያተርፋል?

የኦሮሞ የተማሪዎች ተቃውሞ “የመሪ ያለህ” ይላል! ኢህአዴግስ ከተቃውሞው ምን ያተርፋል?

December 11, 2015 4
Share!
Oromo protestors

Oromo protestors

ለመሆኑ መንግስት የማስተር ፕላን እቅዱን ቢሰርዝ እየተካሄደ ያለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ይቆማል? በኢትዮዽያ የተለያዩ አካባቢዎች የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን የተቃወሙ ሰልፈኞች ከፀጥታ ሀይሎች ጋር እየተጋጩ ነው። ተቃውሞው ለበርካቶች እስርና መቁሰል እንዲሁም መገደል ምክንያት ሆኗል። ይህን ዘገባ እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው። እየተስፋፋ የመጣው ተቃውሞ የተለያዩና የሚቃረን የፖለቲካ አቋም ባላቸው ቡድኖች መካከል ትብብር የሚጋብዝ ሆኗል። ጥያቄው ከማስተር ፕላኑ ባሻገር በሀገሪቱ ያለውን አፋኝ ስርዓት ወደ መለወጥ ሊዞር ይችላል። አርጋው አሽኔ ዝርዝር ዘገባ አለው


የኢትዮዽያ መንግስት የአዲስ አበባ ከተማን ከአጎራባች የኦሮሚያ ከተሞች ጋር በልማት አሰተሳስራለሁ ሲል ያቀረበው ዕቅድ ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲገጥመው ያሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ተቃውሞው ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ሰፊውን የኦሮሚያ አካባቢ ያንቀሳቀሰ ሆኗል። ተቃውሞው በት/ት ተቋማትና በወጣት ተማሪዎች የሚካሄድ ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪዎችም ከሰልፉ ለመቀላቀል እየሞከሩ መሆኑን የዓይን እማኞች ይናገራሉ።

በመንግስት በኩል ይህ አይነቱ ተቃውሞ እንደሚከሰት አስቀድሞ የተገነዘበና የተዘጋጀበት ይመስላል። በሁሉም አካባቢዎች የፀጥታ ሀይሎችን በማሰማራትየሀይል እርምጃ እየወሰደ ነው። በዚህም በርካቶች ቆስለዋል የተገደሉ ተማሪዎችም አሉ (ቁጥራቸውን ከገለልተኛ አካል ማጣራት ባይቻልም)።

እንደ ኢህአዴግ ባለ አፋኝ አገዛዝ፣ የአዲስ አባባ ማስተር ፕላን “የኦሮሚያ ገበሬዎችን ያፈናቅላል፣ የመሬት ቅርምት ስለሆነ እንቃወመዋለን” እያሉ ያሉት ሰልፈኞቹ ጥያቄያቸው ከማስተር ፕላኑ ባሻገር “መስረታዊ መብቶቻችን ይከበሩ” “ኢህአዴግን አንፈልገውም”  የሚል እንድምታ እንደሚኖረው መገመት ከባድ አይደለም።

የኦሮሚያው ስልፍ ከመጧጧፉ አስቀድሞ በጎንደር አካባቢ ብሔርን መሰረት ያደረጉና ሌሎች የመብት ጥያቄዎችን ያነገቡ ተቃውሞዎች መደረጋቸውን፣ ይህን ተከትሎም በጎንደር በእስር ቤት ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ እስረኞች መሞታቸውንና ማምለጣቸውን፣ ይህም በአካባቢው ውጥረት መቀስቀሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኦሮሚያ ባሉ በርካታ የት/ት ተቋማትና በሀገሪቱ ባሉ ሌሎች ከፍተኛ የት/ት ተቋማት እያገነገነ ያለው ተቃውሞ በአማራ ክልል ካለው ጋር ተዳምሮ ሀገሪቱ በጂኣኦግራፊያዊ ስፋቷ ሰፊ ሊባል የሚችል ተቃውሞ እያስተናገደች ትገኛለች።

ተማሪ መር አሆነው ይህ ተቃውሞ በማህበራዊ ሚዲያ እያገኘ ካለው ድጋፍና የሰደተኛ የፖለቲካ ተዋንያን   አይዞህ ባይነት ባሻገር ግብታዊ እንቅስቃሴ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ ቀደም በኢትዮዽያ በተደጋጋሚ እንደተደረጉት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ይህም መሪ አልባ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በገዢው ፓርቲ ላይ ጫና አሳድሮ ውጤታማ ለመሆን ብዙ መንገድ ይቀረዋል።

ገዢው ፓርቲ ተቃውሞው ብዙም እንዳላሳሰበው ለማስመሰል ይሞክር እንጂ የተቃውሞ እንቅስቃሴውን  በዐይነ ቁራኛ እየተመለከተው መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።

ተቃውሞው መሪ አልባና የተደራጀ አለመሆኑን የተገነዘቡ የፖለቲካ ቡድኖች የህዝቡን መነቃቃት ወደተደራጀ እንቅስቃሴ ለመምራት ድንገተኛ የሆነ ስራ ውስጥ እንዲገቡ አስገድዷቸዋል።

በሀገር ቤት ስውር አባላት እንዳሉት የሚገልፀው አርበኞች ግንቦት ሰባትም ሆነ ተበታተነው ያሉት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ከህዝቡ ለመጣው ጥያቄ የሚጠበቀባቸውን የአመራርነት ምላሽ ለመሰጠት ጉድ ጉድ እያሉ መሆኑን ገልፀዋል። እስካሁን በመግለጫ መልክ እየተሰጡ ባሉ አስተያየቶች የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው የኢትዮዽያ ህዝብ ጋር መተባበር ካልቻለ ትግሉ ውጤት አያመጣም ፣ በስልጣን ላይ ያለውን አፋኝ ስርዓትም ለመለወጥ አቅም አይኖረውም የሚለውን አቋማቸውን ብሄር ተኮር ያልሆኑት የፖለቲካ ቡድኖች ለኦሮሞ ልሂቃን አቅርበዋል።

የኦሮም የፖለቲካ ቡድኖችም በኦሮሞ ላይ የሚደርስ በደል የኦሮሞ ብቻ አይደለም፣ ሁሉም ኢትዮዽያዊ አብሮን መቆም አለበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።  እነዚህ የፖለቲካ ዲስኩሮች እስካሁን ይፋዊ በሆነ መንገድ ለፖለቲካ መደራደሪያ ባይቀርቡም በመግለጫ መልክ ተሰምተዋል።

አሁን የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ አመታትን በተለያዩ መንገዶች ሲታገሉ ለቆዩት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መስሏል። ፓርቲዎቹ ህዝባዊ ተቃውሞን መንደርደሪያ ማድረግ ከብልህ የፖለቲካ መሪ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን የተገነዘቡም ይመስላል። አንድ ትልቅ የቤት ስራ ግን ከፊት አለ። ብሄር ተኮር የሆኑና ከመገንጠል እስካ ራስ ገዝ መብት በሚጠይቁና፣ በተለምዶ የአንድነት ሀይል በሚባሉት ቡድኖች መካከል ፣ የግራና ቀኝ የፖለቲካ ሀይሎቹን ወደጋራ መግባባት የሚያመጣ ይህ ነው የሚባል ዝቅተኛ የመግባቢያ ስምምነት በሌለበት እንዴት በጋራ ወደፊት መራማድ ይቻላል? የሚል።

ጥያቄውን የቅንጦት አድርገው የሚመለከቱት አሉ። “አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው በስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት ማስወገድ ነው” የሚሉት ወገኖች በግራና ቀኝ በክንፍ ፖለቲከኞች መካከል ለአምስት አስርተ ዓመታት በኢትዮዽያ ፖለቲካ ውስጥ የነበረውን እውነታ መለስ ብለው ለማየት የደፈሩ አይመስልም።

ማዕካላዊ መንግስት አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ ዘመናትን ባስቆጠረበት የኢትዮዽያ የፖለቲካ ታሪክ የፌደራል ስርዓቱና የብሄር ጥያቄ  አዲስ መልክ በያዙበት ባለፉት አመታት፣ ሁሉን ሊያስማማ የሚችል የፖለቲካ ፕሮግራም ይዞ የፖለቲካ ሀይሎችን ወደ አንድ ማምጣት የሚችል የፖለቲካ መሪና ድርጀት ገና አልተፈጠረም።

ከወራት በፊት ባለመተማመንና በመወነጃጀል ተጠምደው የነበሩት የሁለት ጎራ የፖለቲካ ህይሎች በጋራ መስራት አስፈላጊነት ላይ ያሳዩትን በጎ ፈቃድ ጥሩ መንደርደሪያ ቢሆንም ሩቅ መንገድ ለመጓዝ የሰከነ ውይይትና ስጥቶ የመቀበል እርምጃን ይጠይቃል።

ያልተደራጀ አልያም መሪ የሌለው ተቃውሞ ውጤታማ ሊሆንም ሆነ በገዢው ፓርቲ ላይ ግፊት አሳድሮ አንድም ለድርድር ሲሆን ደግሞ ለስርዓት ለውጥ አቅም ሊኖረው አይችልም።

የፖለቲካ ተቃውሞ ከአደባባይ ስልፍ አልፎ ውጤት የሚያመጣው እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ጥያቄ ይመስላል። በፀጥታና ደህንነት ተንታኞች ምክር መሰረት ህዝባዊ ተቃውሞውን የሚደግፉ ወታደራዊም ሆነ ሲቪል ባለስልጣናት ዋና ኢላማ መሆን አለባቸው። አሁን በኢትዮዽያ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ብሎም ሁሉን አድራጊው ህወሀት በዘረጉት መዋቅር አፈንግጦ ወደ ተቃውሞ ጎራ የሚቀላቀል ተፅዕኖ ፈጣሪ የፖለቲካ መሪ ይኖራል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ይሆናል።

የመከላለያና የደህንነት ተቋማቱም ቢሆን ሌላውን እንደጠላት የሚያዩ እንጂ ለህዝባዊ ተቃውሞ ምላሽ የሚሰጥ ስነልቦናዊ ዝግጅት ያላቸው አይደሉም። ወትሮ ተቃዋሚዎች የገዢውን ፓርቲ ወገኖች ለመሳብ ሙከራ ከማድረግ ይልቅ በማራቅና በማሸማቀቅ ስለሚያርቋቸው እንዲህ ባለው የተቃውሞ ወቅት አይናቸውን የሚጥሉበት የውስጥ አርበኛ ለማግኘት አዳጋች ይሆናል። ከገዢው ፓርቲ አንዱ አባል ከሆነው ኦህዴድ ጋር ይፋዊ ያልሆነ ግንኙነት ያላቸው የኣኦሮሞ ልሂቃን ይነስም ይብዛ ይህን ሙከራ የማድረግ ዕድል አላቸው።

ሌላው አብይ ጉዳይ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲበረታ ከገዢው ፓርቲ ጋር በጓሮ በር የሚደረጉ ድርድርና          ንግግሮች ውጤት ላለው ፖለቲካ አስፈላጊ ናቸው። የፈረንጅ ዲፕሎማቶች ከሚጫወቱት ሚና በበለጠ ገለልተኛና ተሰሚ የሀገር ልጆችን ማሰናዳት አንዱ የቤት ስራ ነው። አመፅና ህዝባዊ ተቃውሞ በራሱ ግብ አይደለም፣ ግቡ የፖለቲካ ለውጥ ሲሆን አመፅና እምቢተኝነት የፖለቲካ አላማን ማስፈፀሚያ መሳሪያዎች ናቸው።

ይልቁንም በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው የሚታወቀው ኢህአዴግ ሰልፉን በተሳካ መልኩ ለራሱ አላማ ማስፈፀሚያ ይጠቀምበታል፣ በህዝቦች መካከል መፈራራት እንዲሰፍንና ኢህአዴግ ብቸኛ የኢትዮዽያ መድህን ሆኖ እንዲታይ ይረዳዋል።

የከሸፉ ስልፎችና ተቃውሞዎችም ቢሆኑ የኢህአዴግን አይነኬነትና አይደፈሬነት እንዲያሳዩ አድርጎ በመቃኘት በህዝቡ ላይ የስነ ልቦና ሽንፈት ለማስረፅ መጠቀሚያ መሆኑ አይቀሬ ነው።

 

4 Comments

 1. ኢስማኤል December 14, 2015 at 11:08 pm

  ራድዮችሁን ድንገት ነው ያገኘሁት ሳዳምጠው ደግሞ በኢትዮጵያዊያን ሚድያ ተደጋግሞ የምንሰማው የተንሻፈፈ የመረጃ ኣቅርቦት ያለው ይዘት ኣላየሁበትም ሚዛናዊነታችሁ ወድጀዋሎህ በደንበኝነት ለቀጣይ ጊዜ ኣብሬያችሁ አሆናሎህ ኢንሻኣላህ ምን ልርዳ ብዮ መዳፈሩን ልተወውና ሌሎችች ጝዶቼም አንዲያደምጣችሁ የተቻለኝን ያክል ኣደርጋሎህ በርቱ በርቱ
  ኢስማኤል ነኝ ከ ኣምስተርዳም ኔዜርላንድ

  Reply
  • wazemaradio December 15, 2015 at 7:11 pm

   Thank you for the compliment and stay tuned with Wazema!

   Reply
 2. Asnake Belay February 1, 2016 at 11:47 am

  Comment
  የአሮሞ ሕዝብ ተቃውሞ መሪና ውጤት አልባ አይደለም።የመሬት ቅርመታን መነሻው ያደረገው ተቃውሞ ከህፃን እስከ አረጋዊያንን ከምሁር እስከ አፈር ገፊ ገበሬ የተሳተፈበት ነው።ጌታው፣በቦታው ስላልነበሩ ሁኔታውን አላዩትም።ሁኔታው ግን እርሶ ለማጣጣል እንደፈለጉት አይደለም።የትግሉም ግለት ወያኔን አስጨንቆት ለመሬት ቅርምት ያወጣውንና በግድም በውድም አስፈጽመዋለሁ ያለውን እንድቀለብሰው ተገዷል።ይህ ውጤት አይደለም?ወያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ እጅ የሰጠበት ነው።ለመሆኑ በ1997ዓም እናንተ ያደራጃችሁትና የመራችሁት አመፅ ለተቃውሞ መነሻ የነበረውን ጉዳይ የመቀልበስ ውጤት ነበረው?ለኦሮሞ ሕዝብና ትግል ያላችሁን የተንሸዋረረ እይታ እናውቀዋለንና አንገረምም።የኦሮሞን ሕዝብ ትግል ለማንካሰስ ብቻ የዘመኑን ቴክኖሎጅ ውጤት የሆኑትን የሙባይል ሰልክና የማሕበራዊ ድረ ገጹን አቅምና ሚና እንኳን ለማየት አልቻሉም።ድሮ ወያኔ ለመግደል ጠመንጃ፣ለመዋሽት ሚድያ ነበረው።በተለይ የሚዲያው አለመኖር የኦሮሞን ሕዝብ ትግሉን ያለአንደበት እንዲያደርግ አስገድዶቷል። እውነቱም ለአለም ጆሮ ሳይደርስ ቆይታል።ዛሬ ሁኔታው ተለውጧል።ቴክኖለጂው እርስበርስ ከማቆራኘት አልፎ እያንዳንዳን የወያኔን ወንጀል በኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክና በግል ለማጋለጥ ችለናል።የአውሮፓ ህብረትን መግለጫ ይመልከቱት።ይህን የዲፕሎማሲ ድል ያለአመራር አላገኘነውም።ወያኔን በፕሮፓጋንዳ አሸንፈነዋል።የመሬት ቅርመታው ተጋልጣል።ወያኔ ሕጻናት ጨፍጫፊ ስርዐት መሆኑ ተጋልጧል።የኦሮሞ ሕዝብ የተበደለ የተገለለ ሕዝብ መሆኑ ተረጋግጣል።ይህ ለእኛ ድል ነው። ያለትግልና መሰዋትነት የተገኘ አይደለም።ጌታው፣የእኛ እዝህ ደርሳል።የእናንተም ፈተና ተቃርቧል።የነገ ሰው ይበለንና አብረን እናየዋለን።

  Reply

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Tweets by @Wazemaradio