Amhara TVዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያው ገዥ ፓርቲ ከገጠመው ህዝባዊ ተቃውሞ ባሻገር የራሱ አባል ድርጅቶችም በከረረ አለመግባባት ላይ መሆናቸውን ድርጅቱ ራሱ አልሸሸገም። ይህ የፖለቲካ ሽኩቻ ጎልቶ ከሚንፀባረቅባቸው መድረኮች አንዱ ፓርቲዎቹ በሚመሯቸው ክልሎች ያሉት የክልል መገናኛ ብዙሀን ተቋማት ናቸው። የአማራና የኦሮሚያ ክልል የቴሌቭዥን ስርጭቶች በሀገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት ሙሉ ቁጥጥርና የበላይነት ያለውን ህወሐት የሚነቅፉና በማዕከላዊነት የሚተላለፈውን ፕሮፓጋንዳ መና ያስቀሩ ሆነዋል። ይህን የክልል መገናኛ ብዙሀን አንፃራዊ ነፃነት መልሶ ለመገደብ ገዥው ፓርቲ አዲስ እቅድ መንደፉ እየተሰማ ነው። [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከግርጌ ያገኛሉ]

የክልል መገናኛ ብዙሀኑ ስርጭታቸውን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አማራጭ ቻናሎችና በሳተላይት ማስተላለፍ ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል። እስከ ቅርብ ጊዜ የብሄራዊው ቴሌቭዥን ተቀፅላ ተደርገው የሚታዩ በአቀራረብም ሆነ በይዘት ማራኪነት የሚጎድላቸው ነበሩ። በሀገሪቱ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመፅ ተከትሎ ግን ቀስ በቀስ ከዓመፁ ጋር የተያያዙ የህዝብ ጥያቄዎችን በማንሳት የተመልካቾቻቸውን ትኩረት መግዛት ችለዋል። አሁን ባሉበት ደረጃ ደግሞ በሀገሪቱ በአንድ ወገን ብቻ ይፈስ የነበረውን የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ላይ ውሀ ቸልሰውበታል።

ይህን ችግር መፍታት ያስችላል የተባለ አዲስ ዕቅድ ውስጥ ውስጡን ውይይት ከተደረገበት በኋላ ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን የዋዜማ ምንጮች ነግረውናል።
የመጀመሪያው እርምጃ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ቀድሞ ወደ ክልሎች አሸጋግሯቸው የነበሩ የተለያዩ የቋንቋ ፕሮግራሞችን ራሱ መልሶ መያዝ ሲሆን፣ ለዚህም እንዲረዳው የትግርኛና የኦሮምኛ አዳዲስ ቻናሎችን በቅርቡ ይከፍታል። በአዳዲሶቹ ቻናሎች የክልሎችን ፕሮግራሞች ተሰሚነት የሚፎካከሩና የመዝናኛ ይዘት የሚያመዝንባቸው ፕሮግራሞች ይኖሩታል። ይህ ዕቅድ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከሌሎች የግል ቻናሎች ተፎካካሪነትና የገጠመውን የተመልካች ማሽቆልቆል ለማካካስም ያለመ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንን ሀገር አቀፍና አለማቀፍ ቻናሎች በመጠቀም ስርጭት የሚያከናውኑት የክልል መገናኛ ብዙሀን ከፍ ያለ ኢንቨስትመንት የሚጠይቀውና የኢትዮ-ቴሌኮምን መሰረተ ልማት ከሚጠቀመው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ስርጭት ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ መታቀዱንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ እርምጃ የክልል መገናኛ ብዙሀን የሀገር ውስጥ ተደራሽነትን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ሲሆን ዋነኛ ስርጭታቸው በሳተላይት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ያላቸውን ተደራሽነት ከማሳነሱ በላይ በማናቸውም ጊዜ የራሱ የመንግስት አፈና (ጃሚንግ) ሰላባ ያደርጋቸዋል።
ይህ እቅድ በቀጣዮቹ ወራት ደረጃ በደረጃ የሚተገበር ሲሆን፣ በሀገሪቱ የብሄር ግጭት መባባሱና የብሄር ፌደራሊዝሙ ላይ ጥያቄዎች መነሳት መጀመራቸው ለእርምጃው መነሻ መሆኑ ተገልጿል።
ገዥው ፓርቲ አንድነቱን ጠብቆ መቆም በተሳነው በዚህ ጊዜ የክልል መገናኛ ብዙሀን ልዩነትን በማስፋትና የትግል መሳሪያ በመሆን ያሳዩት አዝማሚያ፣ በተለይ በህዝቡ ዘንድ እያገኙት ያለው አመኔታ የበላይነቱን ላለማጣት እየተንገታገተ ላለው ህወሐት ትልቅ ራስ ምታት መሆን በቅርቡ በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ በይፋ ሲነሳ ተሰምቷል። [ዝርዝር የድምፅ ዘገባውን ከታች ያድምጡት]

https://youtu.be/AKlAWjvyAiQ