CBE Headquarters New building -FILE
  • የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጓል
  • የባንኩ ትልልቅ ደንበኞች የሚስተናገዱበት አዲስ ክፍል ተቋቁሟል

ዋዜማ ራዲዮ- ከ2010 አ.ም ጀምሮ በተለያዩ የማሻሻያ ትግበራዎች ውስጥ ያለፈው ግዙፉ መንግስታዊ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 15 ምክትል ፕሬዝዳንቶችን ምደባ አካሂዷል። ይህም አራት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ የተካሄደ ምደባ ነው።

ምደባው የተካሄደው ባንኩ ባስጠናው አዲሰ መዋቅር አማካኝነት ሲሆን ጥናቱንም ያካሄደውም መሰረቱን አሜሪካ ያደረገው  መካንዚ(Mckinsey) የተባለ የስራ አመራር አማካሪ ድርጅት  ሰለመሆኑ ዋዜማ ራድዮ  ከዚህ ቀደም መዘገቧ ይታወሳል።

በመዋቅሩ የመጀመርያ ትግበራም የ15 የምክትል ፕሬዝዳንቶች ምደባ ባለፈው ሳምንት ተካሂዷል። 

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 24 ምክትል ፕሬዝዳንቶች የነበሩት ሲሆን በተደረገ የክለሳና ማሻሻያ ስራ የምክትል ፕሬዝዳንቶች ቁጥር ወደ 18 ዝቅ ተደርጎ ቆይቷል ፣ በአዲሱ ምደባ ደግሞ ባንኩ በ15 ምክትል ፕሬዝዳንቶች ተዋቅሯል። 

በዚህም አቶ ኀይለኢየሱስ በቀለ የብድር አስተዳደር ዘርፍን በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ተመድበዋል። አቶ ኀይለኢየሱስ የኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ በንግድ ባንክ ከመጠቅለሉ በፊት ባንኩን በስራ አስኪያጅነት የመሩ ፣ ከዚያም የኢትዮጵያ ልማት ባንክን በምክትል ፕሬዝዳንትነትና  እና በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉ እና በተፈጠሩ አለመግባባቶች ከሀላፊነታቸው የተነሱ መሆናቸው ይታወሳል።

ንግድ ባንኩ ትልቅ ለውጥ አመጣበታለሁ ብሎ በምክትል ፕሬዝዳንት እንዲመራ ያቋቋመውን የዎልሴል ባንኪንክ ክፍልን ደግሞ አቶ ሙሉነህ ለማ ይመሩታል።አቶ ሙሉነህ ባንኩን እስካሁንም በምክትል ፕሬዝዳንትነት እያገለገሉ ያሉ ናቸው። አሁን የሚመሩት የዎልሴል ባንኪንግ አገልግሎትም ከግል አካውንት ውጪ የባንኩ ትልልቅ ደንበኞች ተለይተው አገልግሎት የሚሰጥበት ስርአት ነው። በዚህ የምከትል ፕሬዝዳንትነት መደብ ስር ያሉ ሰራተኞችም ዋነኛ ስራቸው ደንበኞች የሚፈልጉትን አገልግሎት ተከታትሎ ማስፈጸም እንደሆነም ዋዜማ ሬዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች።

በሌላ በኩል ደግሞ ወይዘሮ ማክዳ ዑመር የኦዲት ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነዋል። የፋሲሊቲ ማኔጅመት ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ወደ ሰው ሀይል ምክትል ፕሬዝዳንትነት የተሸጋሸጉ ሲሆን የሰው ሀይል ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ጡሪ ከቦታቸው ተነስተዋል። እመቤት መለሰ የስትራቴጂክ ዕቅድና ሽግግር ዘርፍ  እንዲሁም ሙሉነህ አቦየ ሪስክ ማኔጅመኘት ኤንድ ኮምፕሊያንስ ምክትል ፕረዝዳንቶች ሆነው ከተመደቡት መካከል ናቸው። 

በሌላ በኩል የባንኩ የህግ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ሱሪ ፈቀታ እና የቢዝነስ ዴቨሎፕመንች ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ይስሀቅ መንገሻም ተነስተዋል። በቀጣይም የዳይሬክተሮች ምደባ እንደሚከናወን ሰምተናል።

ግዙፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህንን መዋቅር ለተወዳዳሪነትና ለበለጠ ውጤታማነት እንደሚፈልገው ተገልጿል።

በ2012 አ.ም አጋማሽ አካባቢ አቶ አቢ ሳኖ የባንኩን ፕሬዝዳንትነት ከአቶ ባጫ ጊና ከመረከባቸው በፊት ንግድ ባንኩ ከፍተኛ የትርፍ ማሽቆልቆል ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል። የ2012 አ.ም የባንኩ ትርፍ 14 ቢሊየን ብር ሲሆን ይህም በባንኩ ታሪክ ብዙም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከቀደመው አመት አንጻር የ1.4 ቢሊየን ብር ቅናሽ አሳይቶ ነው። 

በዚያው 2012 አ.ም ባንኩ ያሰባሰበው ተቀማጭ ከ2011 አ.ም ከ30 ቢሊየን ብር በላይ ቀንሶ ወደ 54 ቢሊየን ብር ወርዷል። 

ከአቶ ባጫ መነሳት በኋላ በነበረው የአቶ አቤ ሳኖ ፕሬዝዳንትነት ወቅት የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግ ባንኩ ከገባበት አደጋ መውጣት ችሏል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2013 አ.ም ትርፍ ከ20 ቢሊየን ብር በላይ ሆኗል።   እንዲሁም ባንኩ በዚያው አመት ከ140 ቢሊየን ብር በላይ ተቀማጭ በማሰባሰብ አጠቃላይ ተቀማጩን 735 ቢሊየን ብር አድርሷል። ያለፈው አመት ትርፉም በባንኩ ታሪክ ያልታየም ነበር። የባንኩ ሀብትም አንድ ትሪሊየን ብርን ተሻግሯል።

ከበርካታ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ያልተመለሰ ብድር ችግር ውስጥ ገብቶ የቆየው ንግድ ባንኩ መንግስት ያቋቋመው የልማት ድርጅቶች ዕዳ አስተዳደር ኮርፖሬሽን የልማት ድርጅቶችን ዕዳ መውረሱን ተከትሎ ያልተመለ ብድር ምጣኔው ተስተካክሏል። አሁን ባለው መረጃም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበላሸ ብድር ምጣኔ 4.6 በመቶ ሲሆን ይህም ለንግድ ባንኮች ከተቀመጠው የ5 በመቶ የተበላሸ ብድር ምጣኔ አንጻር መልካም የሚባል አፈጻጸም ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]