ዋዜማ ራዲዮ- ያለፉትን ዓመታት በተበላሸ ብድር ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2013 ዓ ም በጀት ዓመት ከታክስ በፊት የተጣራ 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን ዋዜማ ራዲዮ ከድርጅቱ ሁነኛ ምንጮች ስምታለች።
ልማት ባንክ ይህንን ትርፍ ያስመዘገበው እስካለፈው ሰኔ ወር በነበረው የበጀት ዓመት መዝጊያ ነው።


የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከዚህ ቀደም በዓመት ያስመዘግብ የነበረው ትርፍ ከ300 ሚሊየን ብር ብዙም ፈቀቅ ያላለ ከመሆኑ ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮ ትርፍ ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበ ሆኗል።

ይህ ዓመት በኮሮና ወረርሽኝና በትግራዩ ጦርነት ሳቢያ በኢኮኖሚው ላይ ጥላ ያጠላበት ቢሆንም ባንኩ ከሚጠበቀው በላይ ትርፍ በማግኘት ስኬት ተጎናፅፏል።


የባንኩ የዘንድሮ ትርፍ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ምክንያት የሆነው ከዚህ ቀደም እስከ 51በመቶ ይደርስ የነበረውን የባንኩ የተበላሸ (የማይመለስ) የብድር መጠን በከፍተኛ ደረጃ ለማውረድ በመቻሉና በባንኩ አመራር በተወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎች ነው


በተለይ ባንኩ በአዲስ አበባ ከዚህ ቀደም ይሰጥ በነበረው ብድር የተባለሸ የባንኩ የብድር መጠን ከአጠቃላይ የብድር መጠን አንፃር እስከ 20 በመቶ ሆኖ ይመዘገብ ነበር። በዘንድሮ አመት ግን ይህንን የተባለሸ የብድር መጠን ከ3 በመቶ በታች ማውረድ በመቻሉ አንዱ የትርፋማነቱ ምክንያት መሆኑን የባንኩ ምንጮች ለዋዜማ አስረድተዋል።


ከልማት ባንክ ብድር ወስደው ሳይመልሱ የቆዩ ድርጅቶችም ብድራቸውን እንዲመለሱ መደረጉ እና የባንኩ ብድር የመሰብሰብ አቅም ማደጉ ለተገኘው ከፍተኛ የትርፍ መጠን አስተዋፅኦ አበርክቷል።


ከዚህ በተጨማሪም ባንኩ ማምረት ለሚፈልጉና የፋይናንስ እጥረት ላለባቸው ዜጎች የማምረቻ ማሽኖችን ደንበኞቹ በሚፈልጉት መልኩ ገዝቶ በሚያስተላለፍበት የሊዝ ፋይናንሲንግ የብድር አገልግሎቱ በተለይ በአዲስ አበባ የብድር አሰባሰቡ ከፍተኛ ለውጥ መታየቱንም ስምተናል።


በዚህ የብድር አገልግሎት ዘርፍ ተጠቅመው እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ እና ብድራቸውን ያልመለሱ አምራቾች ከ2 በመቶ እንደማይበልጡ የባንኩ ምንጮቻችን ነግረውናል። ይህም ከፍተኛ የሆነ የአፈፃፀም ስኬት የተያበት ነው።
ባንኩ በትግራይ ክልል ቅርንጫፉ በኩል የሰጠውን ብድር መሰብሰብ ቢችል ደግሞ የትርፉ መጠን ይበልጥ ሊያድግ ይችል እንደነበርም የባንኩ ባለሙያዎች ያምናሉ።


የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከዚህ ቀደም የቱርክ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ዝርፊያ ሊባል በሚችል ደረጃ እየተበደሩ መጥፋት ፣ በጋምቤላ ክልል ለተደራረቡ የሰፋፊ እርሻ መሬቶች ብድርን መስጠት፣ በርካታ የሰፋፊ እርሻ አልሚዎችም ተበድረው መጥፋታቸው ፣ እና በሌሎች ተያያዥ የአሰራር ክፍተቶች የተበላሸ ብድሩ ምጣኔ 51.6 በመቶ (20ቢሊያን ብር) ደርሶ እንደነበር ዋዜማ በተከታታይ ዘገባዎቿ ማስነበቧ አይዘነጋም። [ዋዜማ ራዲዮ]