ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፋይናንስ ዘርፍ ታሪክ ብዙም ተሰምተው የማያውቁ የአሰራር ግድፈቶች ሲታዩበት ፣ያበደረውን ገንዘብ በብዛት ማስመለስ ሲያቅተውና ኪሳራ ሲያስመዘግብ ለአመታት የቆየው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፣ አሁን ላይ ከችግሩ እንዲወጣ ያስችለዋል የተባለ የካፒታል ማሳደጊያ ገንዘብን ከመንግስት እንዲያገኝ ተወስኖለታል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትላንት ሀሙስ ባደረገው 20ኛው አስቸኳይ ስብሰባም ልማት ባንኩ ካፒታሉን ለማሻሻል የሚያስችለውን የተሻሻለው የባንኩ ማቋቋሚያ ደንብን አጽድቆ በነጋሪት ጋዜጣም ታትሞ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ መረዳት እንደቻለችውም ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ካፒታል ማሳደጊያነት እንዲውል ከመንግስት የተወሰነለት ገንዘብ 21 ቢሊየን ብር ነው። ይህም የባንኩን ካፒታል አሁን ካለበት 8 ቢሊየን ብር አካባቢ ወደ 29 ቢሊየን ብር ያሳድገዋል። በዚህም በካፒታል መጠን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ ባንክ ይሆናል ። መንግስት ከጥቂት አመታት በፊትም የንግድ ባንክን ካፒታል ለማሳደግ በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።


ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ አሁን ላይ እንዲሰጠው የተወሰነለት 21 ቢሊየን ብር ባንኩ ባለፉት አሰራሮቹ ምክንያት አጋጥሞት ከነበረው የካፒታል ችግር ወጥቶ ወደ ተስተካከለ ስራ እንዲገባ ያግዘዋል ተብሏል። ከዚህ ጎን ለጎንም ልማት ባንኩ የተሻሻለ የብድር አሰራርን ስርአትን አጠናቆ በቅርቡ ተግባራዊ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ከአሰራሩ ጋርም ተቋማዊ የመዋቅር ለውጥን ይተገብራል ። ይህን አጠቃላይ ማሻሻያን በማስጥናት ሂደት ውስጥ የአለም ባንክን ጨምሮ በተለያዩ አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሰሩ ሙያተኞችም ተሳትፈውበታል።ይህ የልማት ባንኩን ሁለንተናዊ አሰራር ይለውጣል የተባለው ሰነድም በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን በቅርቡም በመንግስት ለመጽደቅ ለውሳኔ እንደሚቀርብም ሰምተናል።


የመንግስት የፖሊሲ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በነበሩት የአሰራር ግድፈት የሰጣቸው ብድሮች በእጅጉ አደጋ ውስጥ ገብተው ለባንኩም ችግር ሆነዋል።በቅርብ ጊዜ እንኳ ልማት ባንኩ በጥቅሉ ሰጥቶት ከነበረው 46 ቢሊየን ብር ውስጥ 40 በመቶው የተበላሸ ብድር ሆኖ ቆይቷል። ቁጥሩ ልማት ባንኩ ይፋ ያደረገው ነው። የውስጥ ምንጮች የተበላሸውን የብድር ምጣኔ 50 በመቶን እንደተሻገረም ገልጸውልን ነበር። በብር ሲተመንም እስከ 20 ቢሊየን የሚሆነው ልማት ባንኩ የሰጠው ብድር መመለስ የማይችል ሆኖ ቆይቷል ። የልማት ባንኩ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ከሰጠው ብድር ከ15 በመቶ እንዳይበልጥ ገደብ ያለ እንደመሆኑ በሁለቱም ቀጥሮች ቢወሰድ ባንኩ አደጋ ውስጥ እንደቆየ የሚያሳይ ነው።


ልማት ባንኩ የተበላሸበት ብድር የተቀረጹ ፖሊሲዎች ውጤት እንዳላመጡም ያሳየ ነው። ባንኩ የተበላሸ ብድር በስፋት የታየው ግዙፍ ናቸው ለተባሉ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች የተሰጠ ነው።ብዙዎቹም የቱርክ ኩባንያዎች ናቸው። አይካ አዲስና ኤልሲ አዲስ የተባሉ የቱርክ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች እያንዳንዳቸው ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ ተበድረው መመለስ አቅቷቸው ፣ የኤልሲ አዲስ ኩባንያ ባለቤቶች ሲጠፉ ባንኩ ፋብሪካውን ተረክቦ ማስተዳደር ጀምሯል። አይካ አዲስም ብድሩን መመለስ ስላቃተው ባንኩ ኩባንያውን እያስተዳደረ ነው። ሆኖም ሁለቱንም ፋብሪካዎች በሀራጅ ለመሸጥ የሄደበት መንገድም ስኬታማ አልነበረም ። ኩባንያዎቹ ቢሸጡም እንኳ ያለባቸውን ብድር መመለሳቸው አጠራጣሪ ነው። ይህ አይነት ብድርም የካፒታል ማሸሻ መንገድ እንደነበርም በስፋት ይታመናል። ኢ ቱር የተባለ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካና ቢ ኤም ኢ ቲ የተሰኘ የኬብል ማምረቻም በቢሊየን የሚቆጠር ብድር ወስደው መመለስ ካልቻሉት ውስጥ ናቸው።


ለሰፊፋ እርሻ አልሚዎች በተለይም በጋምቤላ ክልል የተሰጠው ብድርም ሰፊ ችግር ውስጥ የገባ ነው። ለሰፋፊ እርሻ አልሚዎች ከ6 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን ፣ በነበረ ሰፊ የአሰራር ብልሽት ምክንያት ብድሩ አልተመለሰም። አንድ መሬት ለሁለት ባለሀብቶች ተሰጥቶ ለሁለቱ ባለሀብቶች አንድን መሬት ለማልማት ብድር የመስጠት ተደጋጋሚ ተግባራት ፣ የሰፋፊ እርሻ ልምድ ለሌላቸውና በበሬ ጭምር ለሚያርሱ ብድር በመቅረቡ ፣ ከችሎታ ይልቅ ለአካባቢያዊነት ቅድሚያ መሰጠቱ ፣ በቂ ተያዥ እንኳ ላላቀረቡ ግለሰቦችም ብድር መቅረቡ በዚህ ዘርፍ ለተበላሸው ብድር ምክንያት ሆኗል።

ከውጭ ስለመጡ ብቻ በመቶ ሚሊየን የሚቆጠር ብድርን ለእርሻ ወስደው የጠፉ አሉ።ጎርፍን በመሰለ ተፈጥሯዊ አደጋ የዘሩት ተበላሽቶባቸው ብድር መመለስ ያልቻሉ ጥቂት ታማኝ ተበዳሪዎች መኖራቸው ግን የማይረሳ ነው።


የልማት ባንኩም የባንክ ስራን ሰርቶ ከሚያገኘው ትርፍ ይልቅ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የግል ባንኮች ካበደሩት ገንዘብ 27 በመቶውን በቦንድ መልክ እንዲገዙት አርጎ የሚያቀርብለትን ገንዘብ መልሶ የግምጃ ቤት ሰነድ ገዝቶ የሚያገኘው ትርፍ ይበልጥ ነበር። ብሄራዊ ባንኩ አሁን ለልማት ባንኩ ገንዘብ የሚያቀርብበትን የ27 በመቶ የቦንድ አሰራር ማቆሙ የሚታወስ ነው።


የሆነው ሆኖ የፖሊሲ ባንክ ነው በተባለው ተቋም በኩል በሚለቀቅ ብድርም መፈጠር ያለበትን ያክል ስራ አልተፈጠረም፣ ሀገሪቱም በወጪ ንግድ ማግኘት ያለባትን ያህል የውጭ ምንዛሬ አላገኘችም። በባንኩም የስራ አመራሮች መለዋወጥ ተደጋግሞም ነበር።


እርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልማት ባንኩ አቋሙ መስተካከልን እንዳሳየ ይገልጻል።በዚህ በጀት አመት የመጀመርያ ስድስት ወራት ካልተመለሰለት ብድር ውስጥ 4 ቢሊየን ብሩን ማስመለስ እንደቻለ ገልጿል። በዚህም የተበላሸ ብድር ምጣኔውን ዝቅ ማድረግ እንደቻለ ፣ ይህንንም ብድር ማስመለስ ላይና ለዚህ የሚያግዘኝን ንብረቶች መውረስ ላይ አትኩሬ በመስራቴ ነው ያሳካሁት ብሏል።

በተመሳሳይ በበጀት አመቱ ስድስት ወራትም 951 ሚሊየን ብር ማትረፉንም ልማት ባንኩ አሳውቋል። ልማት ባንኩ በቀደሙት አመታት በቢሊየን ብሮች ኪሳራን ሲያስመዘግብ የቆየ እንደመሆኑ ይህ ቁጥር ለብዙዎች አልተዋጠም ነበር።ሆኖም ልማት ባንኩ የትርፍ መጠኑ በዚህ መጠን የመጣው አዲስ የሂሳብ አሰራር ስለጀመርኩ ነው ፣ በአዲሱ የሂሳብ አሰራሬ ከዚህ ቀደም ያስመዘገብኩት ኪሳራም የተጋነነና ትክክል ያልሆነ መሆኑን ተረድቻለሁ ብሏል።አሁን ላይ ባንኩ እንዲሰጠው የተወሰነው 21 ቢሊየን ብር በተሻሻለ አሰራር ከታገዘ ባንኩን ወደ መልካም ጎዳና ሊወስደው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። [ዋዜማ ራዲዮ]