ዋዜማ ራዲዮ- ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውህድ (unified) ሳይሆን ጥምር (coalition/front) ግንባር በመሆኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ውስጣዊ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው፡፡ የመፈረካከስ አደጋም ያንዣበበት ይመስላል፡፡ ከአወቃቀሩ ስናየው ኢሕአዴግ በግንባርነቱ መቀጠሉ ዘግይቶ የሚፈነዳ ቦንብ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በመሠረቱ ለ26 ዐመታት በግንባር ደረጃ መቆየት ውስጣዊ ቅራኔዎችን ከማፈን እና ከማስታመም እንጂ ከመግባባት ይመነጫል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው ፡፡ ይህ ዘገባ ፓርቲው አሁን የደረሰበትን የውድቀት አፋፍ ይዳስሳል። አድምጡትየዚህ ዘገባ ጥቅል መረጃ ከስር በፅሁፍ ያገኙታል።

https://youtu.be/bu_vR8cdRx8

 

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውህድ (unified) ሳይሆን ጥምር (coalition/front) ግንባር በመሆኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው፡፡ የመፈረካከስ አደጋም ያንዣበበት ይመስላል፡፡ ከአወቃቀሩ ስናየው ኢሕአዴግ በግንባርነቱ መቀጠሉ ዘግይቶ የሚፈነዳ ቦንብ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በመሠረቱ ለ25 ዐመታት በግንባር ደረጃ መቆየት ውስጣዊ ቅራኔዎችን ከማፈን እና ከማስታመም እንጂ ከመግባባት ይመነጫል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው የሚሆነው፡፡ በቅርቡ እንኳ ድርጅቱ ሊከፋፈል እንደሚችል አንጋፋው የግንባሩ ድርጅት ጉዳይ እና ፕሮፓጋንዳ ሃላፊ በረከት ስምዖን መናገራቸው እየሰማን ነው፡፡ የኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ እና ውስጣዊ ዲሞክራሲው እየላላ መጥቷል፡፡ ያለ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ደሞ አንድነቱን ጠብቆ መቀጠል ይከብደዋል፡፡

ግንባሩ ሊገጥሙት የሚችሉት የቅራኔ መስኮች አንጻር ስናየው በአባል ድርጅቶች መካከል የሚፈጠረው የአግድሞሽ ቅራኔ፣ በማዕከላዊው ግንባር እና በአባል ድርጅቶች መካከል የሚፈጠር ተዋረዳዊ ቅራኔ እና በአባል ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጠር ውስጣዊ ቅራኔ ብሎ መክፈል ይቻላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ መስኮች ማለትም በአባል ድርጅቶች መካከል እና በአባል ድርጅቶች ውስጥ ቅራኔዎች ማጎንቆል ጀምረዋል፡፡ በተለይ ሕዝባዊ አመጽ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የኦሕዴድ እና ብአዴን የበታች እና መካከለኛ ካድሬዎች ከድርጅቶቻቸው የበላይ አመራር ጋር ብልጭ ድርግም የሚል ቅራኔ እንዳላቸው መታዘብ ይቻላል፡፡ በብአዴን እና በሕወሃት መካከልም ቅራኔዎች ታይተዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን አሁን እየጎላ የመጣው ህዝቡ የክልል ፓርቲዎችን ፈንቅሎ የማመጹ ነገር ነው፡፡ ይሄ ደሞ ለድርጅቱ ምንም እድል የማይሰጥ ማዕበል ነው የሚሆነው፡፡

ግንባሩ ፍትሃዊ የስልጣን እና ሃብት ክፍፍል እጦት፣ የርዕዮተ ዐለም መዘበራረቅ፣ ጠባብነት፣ ብሄርን መጋረጃው ያደረገ ኪራይ ሰብሳቢነት የመሳሰሉ ችግሮች ቢኖሩበትም እስካሁን ጉልህ ቅራኔ ያላስተናገደው አባል ድርጅቶች “ቅድሚያ ለኢሕአዴግ” ለሚለው ህገ ደንብ ጥቅማቸውን ስላስገዙ እና የብዙዎቹ ድርጅታዊ ጥንካሬ የማያወላዳ በመሆኑ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ግን ግንባሩ አባል ድርጅቶቹን ማማለል የሚችልባቸውን ዕድሎች እያጣ ይመስላል፡፡ መዋቅሩ ከመጠን በላይ በመለጠጡ የካድሬዎቹን ፍላጎት ማሟላት የማይችልበት ደረጃ ላይ ሁሉ ስለደረሰ ውስጣዊ ቅራኔው እንደሚባባስ ነው የሚጠበቀው፡፡

እዚህ ላይ ታዲያ አደጋው ከታየው የተዋሃደ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ መሆንን ለምንድን ነው የሚያጓትተው? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ኢሕአዴግ የአራት ብሄር-ተኮር ድርጅቶች ግንባር የሆነው የኢትዮጵያ መሰረታዊ ጥያቄ የብሄር ቅራኔ ነው ብሎ በማመኑ ቢሆንም የብሄር ጥያቄ ግን በህገ መንግስቱ ተፈትቷል፡፡

በህወሃት ክፍፍል ማግስት ግንባሩን ወደ ውህድ ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ ለመቀየር እንቅስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣ ላይ ሳይቀር ተዘግቦ ነበር፡፡ እንዲያውም የኢሠፓን ድርጅታዊ መዋቅር ጥርሳቸውን የነቀሉትን ጓድ ሽመልስ ማዘንጊያን ከእስር ፈትቶ በአማካሪነት ቀጥሮ ማስጠናት ጀምሮ እንደነበር መረጃዎች ነበሩ፡፡ ስራው ግን ገና እንጭጭ ላይ እያለ የ1997ቱ ምርጫ በመድረሱና በተለይ ሕወሃት የምርጫውን ውጤት ያነበበበት መንገድ ውህደትን አንቅሮ እንዲተፋ ስላደረገው በዚያው ተዳፍኖ እንደቀረ ነው የሚታመነው፡፡ ዛሬም የኢሕአዴግ ሃላፊዎች ስለ ውህደት ሲጠየቁ በደፈናው እየተጠና መሆኑን ከመናገር ውጭ ራሱን የቻለ አጥኝ አካል ተቋቁሞለት እና የጋራ ስምምነት ተደርሶበት እየተሰራበት ስለመሆኑ ምንም ፍንጭ መስጠት አይችሉም፡፡

ግንባሩ ባሁኑ ጊዜ ያሉት ውስጣዊ እና ውጫዊ ሁኔታዎች በቀዳሚዎቹ ጊዚያት ከነበሩት በበለጠ የተወሳሰቡ ናቸው፡፡ እናም ወደ ውህድ ፓርቲነት መሸጋገር የሚችልበት ጊዜ ከእጁ እያመለጠው ይመስላል፡፡ ከአቶ መለስ መሞት በተጨማሪ ባሁኑ ሰዓት የድርጅቱን አወቃቀር ከሀገሪቱ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ገምግሞ ወሳኙን መዋቅራዊ ለውጥ ለመለኮስ የሚችል እና ሀገር ዐቀፍ ራዕይ ያነገበ ማዕከላዊ አመራር ያለው አይመስልም፡፡

በርግጥ አራቱ አባል ድርጅቶች ፕሮግራሞቻቸው እና ህገ-ደንቦቻቸው ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ ስለሆኑ ለመዋሃድ ምንም ችግር እንደማይኖርበት የሚገልጹ ወገኖች አሉ፡፡ ድርጅቶቹ በየክልሎቻቸው የሚገጥማቸው ነባራዊ ተግዳሮቶች ግን ይለያያሉ፡፡ በሌላ በኩል ግንባሩ በተግባር ባልተመጣጠነ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነባራዊ ሁኔታው አንዴ መደፍረስ ከጀመረ እንደ ስልጣን እና ሃብት ክፍፍል የመሳሰሉ የተዳፈኑ ቅሬታዎች እና ፍላጎቶች አጎንቁለው ሊወጡ ይችላሉ፡፡ ውህደት በፓርቲ ሃብት፣ ስልጣን እና ፌደራላዊ ሥርዓቱ ከቆመበት የብሄሮች ሉዓላዊነት መርህ ላይ ጉልህ አንድምታ ያለው ነገር ነው፡፡

ባጠቃላይ ውህደትን ናፋቂ የሆኑ ቢያንስ ሁለት አባል ድርጅቶች ጠንክረው በመውጣት ነባራዊ ሁኔታውን ካልተገዳደሩ ውህደትን ማምጣት አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ አሁን የትኛው ውህደት ፈላጊ የትኛው ደሞ ነባራዊ ሁኔታውን አስጠባቂ እንደሆነ በርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል፡፡

በርግጥ ኢህአዴግ ቢዋሃድ ህገ መንግስቱ ተቀዳሚ አላማው ያደረገውን የአንድ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ምስረታ አስተዋጽዖ ለማድረግ ያስችለዋል፡፡ ከአንገት ይሁን ከአንጀት በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደሞ አንድነትን እና የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን መስበክ መጀመሩ ከውህድ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ አወቃቀር ጋር አብሮ ይሄድለታል፡፡ በአራቱም ክልሎች አንጻራዊ ተቀባይነት ያለው መዋቅር መዘረጋት እና ርዕዮተ ዐለም ማስረጽ ይችላል፡፡ ህብረ ብሄራዊነቱ እየገዘገዙት ያሉትን አፍራሽ ብሄርተኝነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት እና ጠባብነት የመሳሰሉ ችግሮችንም ለመግታት ይጠቅሙታል፡፡ ባጠቃላይ ውህደት አሁን የገባበትን የቅቡልነት ቀውስ እንዲያቃልልለት መገመት አይከብድም፡፡

ከህጋዊ ማዕቀፍ አንጻር ስናየው በ2000 ዓ.ም የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ “ውህደት”ን የሚፈቅድለት ቢሆንም ወደ ኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ ስንመጣ ግን የተለየ ነገር ነው የምናገኘው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ግን ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ራሱን ስለሚያፈርስበት ወይም ስለሚበትንበት አግባብ በመተዳደሪያ ደንቡ መግለጽ እንዳለበት ያስገድዳል፡፡ የኢህአዴግ መተዳደሪያ ደንብ ግን ከሌሎች ፓርቲዎች በተለየ በውሀደት ወይም በሌላ መነገድ ስለሚፈርስበት ሁኔታ አንድም አንቀጽ አልተካተተም፡፡ ውህደት የረዥም ጊዜ ግቡ ስለመሆኑ እንኳ በቀጭን መስመር በመተዳደሪያ ደንቡ አልጠቀሰም፡፡ ይሄ ሁሉ እንግዲህ ግንባሩ ከመነሻውም ሆነ በሂደት ውህደትን የመጨረሻ ግብ አድርጎ እንዳልያዘው አመላካች ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡