Ermias Amelga
Ermias Amelga

ጌታው እንዴት ሰንብተዋል?

ኤርሚያስን ያውቁታል? ይበሉ ይተዋወቁት! ሁነኛ ወዳጄ ነው፡፡ የአገሬ ሀብታሞች ከብዙ ብር ሌላ ምን አላቸው ይበሉኝ፡፡ ብዙ በሽታ! ብዙ ስኳር፣ ብዙ ደም ግፊት፣ ብዙ ሪህ…ብዙ ጭንቀት፡፡ ኤርመያስ ከብዙ ብር ሌላ ምን አለው ብለው ይጠይቁኝ፡፡ ኤርሜያስ ከብዙ ብር ሌላ ብዙ ዕውቀት፣ ብዙ ሕልም፣ ብዙ እቅድ፣ ብዙ ቅዠት…፡፡

የአገሬ ሐብታም ቁርጥ ካላንቆራጠጠው ሀብታም የሆነ አይመስለውም፡፡ ሆዱ የየካ ተራራን ካለከለ የበለፀገ አይመስለውም፡፡ ኤርሚያስ ስጋ መብላት ከተወ ዘመን የለውም፡፡ ሰውነቱ ላይ ሩብ ኪሎ እንኳ ትርፍ ስጋ አትገኝም፡፡

የኤርሜያስ ጠቅል አመልጋን ችሎት ለመታደም ሰባራ ባቡር ወደሚገኘው አራዳ ችሎት ሄጄ ነበር-መቼ ለታ፡፡ የቀድሞው አሰሪዬን፣ አርአያዬን፣ አልባሽ አጉራሼን አየሁት፡፡ ባይኔ በብረቱ፡፡ ተጎሳቁሏል እንጂ አላረጀም፡፡ ኤርሚና ፍቅር መቼም አያረጁም፡፡ ዋሸሁ?…እውነተኛ እድሜዉን ሰለማውቅ ነው አፌን ሞልቼ ‹‹ኤርሚያስ አያረጅም›› የምለው፡፡ የ50ኛ ዓመት ልደቱን ካከበረ ዘጠኝ አመት አለፈው! እሱ ግን አሁንም 33 ነው የሚመስለው፡፡ ዉሃ ነዋ የሚጠጣው፡፡ ኩልል ያለ ዉሃ! ያውም እራሱ ያመረተውን ዉሃ! ኮንኮርድ እየተዝናና ዉሃ የሚጠጣ ሀብታም ካለሱ አይቼ አላውቅም፡፡

እግዚአብሔር ዉሃን ፈጠረ፤ በጊዮን በኩል ወንዝ ሆነህ ፍሰስም አለው፡፡ ከዝንተ ዓለም በኋላ ያን ዉሃ መለስ ዜናዊ ገደበው፤ ኤርሚ በላስቲክ አሽጎ ቸበቸበው፡፡ ሃ ሃ…ኤርሚ ብልጧ!

ኤርሚያስ በማዕከላዊ

ማዕከላዊ አንገላተውታል፡፡ ዘብጥያ እንደወረደ ሰሞን ታይፎይድ የሚባል የድሀ በሽታ አሞት ቆዳው ሁሉ ተቆጥቶ ግልብጥብጥ ብሎ ነበር፡፡ አሁን መለስ ብሎለታል፡፡ በቀጥታ ከማዕከላዊ ነው ይዘውት የመጡት፡፡ ሰልካካ አፍንጫው ከርሱ ቀድሞት ወደ ችሎት ገባ፡፡ አፍንጫው የአረብ ነው የሚመስለው፡፡ ቢዝነስ የሚያሸተው ከሩቅ ነው ይባልለታል፡፡ ሰው የሄደበትን መንገድ መሄድ ይታክተዋል፡፡ ጥርሱን የነቀለው በነጭ ካፒታሊዝም ነው፡፡ ደንበኛ የዎልስትሪት ቆማሪ፡፡

ነገር ሲሰክን አይወድም፡፡ በትንሹ አይረካም፡፡ ዛሬ ፋብሪካ ከፍቶ ትርፍ እየተንፎለፎለለት ድንገት ተነስቶ ሊዘጋው ይችላል፡፡ ግድ የለውም፡፡ አንድ ጊዜ አስታውሳለሁ ‹‹ገዢ ፈልግ›› ይለኛል፡፡ ‹‹አብደሀል?›› አልኩት፡፡ በዉዳቂ ብር የገዛውን የማዳበሪያ ፋብሪካ ሽጥልኝ ያለኝ ቀን ነው እንደዚያ የደፈርኩት፡፡ አፌን አውጥቼ ‹‹አብደሀል ወይ›› አልኩት፡፡

‹‹ምን ላርግ- ሥራው ትርፍ ብቻ ሆነብኝ!›› አለኝ፡፡ ያን ቀን ሰውዬው የፈረንጅ ቡዳ የለከፈው ንክ ዲያስፖራ እንደሆነ ጠረጠርኩ፡፡ ነጋዴ እንዴት ትርፍ ይጠላል?

ኤርሚያስ ከደላሎች ሁሉ እኔን አብልጦ ያቀርበኝ ነበር፡፡ ‹‹ዋና ጉዳይ ገዳዩ›› ሆኜ ለተወሰኑ ጊዜያት ሰርቻለሁ፡፡ አንዴ 25 የሚሆኑ የማርኬቲን ሠራተኞቹን ሰብስቦ እያወያየን ድንገት ይህን ተናገረ፤ ‹‹ምንም ነገር አትፍሩ፣ እኔ ጋር መስራት ካልወደዳችሁ ጥላችሁኝ ሂዱ፤ ሁለት ጊዜ የመኖር ዕድል የላችሁም፡፡ የራሳችሁን ነገር ሞክሩ! ዘላለም ለኔ አገልጋይ መሆን የለባችሁም እኮ፡፡ ሕይወትን መጋፈጥ ልመዱ፡፡ እኔ በበኩሌ ሺ አመት እንደ አይጥ ከመኖር አንድ ቀን እንደ አንበሳ ሆኖ መሞትን እመርጣለሁ››

ሰውየው ብዙ እንግዳ ባህሪያት አሉት፡፡

የአቶ አስፋውን ክራውን ሆቴል ያፈራረምኩት ለታ ‹‹ኤርሜያስ…ምነው ግዢ አበዛህ! ደፈርከኝ አትበለኝና ገንዘብ አወጣጥህን አልወደድኩትም፡፡ ሰዎቹ ቀዳዳ ካገኙብህ አንድ ቀን አያሳድሩህም-ዘብጥያ ነው የሚወረውሩህ›› አልኩት፡፡ ስስ ከንፈሩን ገለጥ አድሮጎ ሳቀና መልስም ሳይሰጠኝ አለፈኝ፡፡ ቆይቶ ጨዋታውን ከዘነጋነው በኋላ ወደ ጆሮዬ ተጠጋና እንዲህ አለኝ- ‹‹አይገርምህም! ቅድም ያልከኝ ነገር ትንሽ ትንሽ ናፈቀኝኮ…››

‹‹ምኑ?››

‹‹ዘብጥያ መውረዱ፣  ጥሩ እረፍት ይሆነኝ ነበር ብዬ አሰብኩ፡፡ በጊዜ ማጣት ጀምሬ የተውኳቸው መጻሕፍት ነበሩ…›› ብሎኝ ተከዘ፡፡ ሰውየው ያመዋል እንዴ?!

እንደዚያ ብሎኝ ሲያበቃ ከአመታት በኋላ በደቡብ ሱዳን በኩል ወደ ዱባይ ፈረጠጠ ሲሉኝ አዘንኩበት፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን እንደሚመለስ ዉስጤ ይነግረኝ ነበር፡፡ ይቅርታ ባያረጉለት እንኳ ፕላስቲክ ሰርጀሪ ተሰርቶም ቢሆን አሻፈረኝ ብሎ ይመለስ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ኤርሚያስን ድሮም ሳውቀው ብርን የሚያፈቅርበት መንገድ ከሌሎች ሀብታሞች ይለያል፡፡ ከብርና ከክብር ይልቅ በአዲስ መንገድ ሄዶ ስኬት መቀዳጀት ይወዳል፡፡ ከዉጤት ይልቅ ሂደት ያዝናናዋል፡፡

ማልዶ ከእንቅልፉ ይነሳና አስቸኳይ የቦርድ ስብሰባ ጥራልኝ ይለኛል፡፡ አባላቱን ሰብስቦ የሆነ የእብድ ሐሳብ ያቀርብላቸዋል፡፡ ‹‹ ከንግዲህ አሸዋና ሲሚንቶ እያቦካን አንኖርም፡፡ አዲስ ነገር መሞከር ይኖርብናል፡፡›› አዳሜ በድንጋጤ ይቁለጨለጫል፡፡ ለመሆኑ ከናንተ ዉስጥ ማግኒዢየም ቦርድ የሚያውቅ አለ? በስቲል ስትራክቸር ሰርተን በስድስት ወር 150 ቤት እናስረክባለን፡፡›› ሌላ መቁለጭለጭ፡፡

የሆነ ማለዳ መጣና አክሰስ ሪሶርት ሆቴል ከነገ ጀምሮ መገንባት እንጀምራለን አለ፡፡ ደነገጥን፡፡ ምንድነው ደግሞ ‹‹ሪሶርት ሆቴል?›› አልነው፡፡

‹‹ብዙ ዲያስፖራ አገር ቤት ሲመጣ ማደርያ የለውም፡፡ ዘመድ ቤት ማደር ደግሞ ነጻነቱን ይጋፋል፡፡ ሆቴል አልጋ መያዝ ኪሱን ይጎዳዋል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ድያስፖራ 3ሺ ዶላር እናስከፍለዉና ኩፖን እንሰጠዋለን፡፡ ያ ኩፖን የምንገነባው ሪሶርት ሆቴሉ ዉስጥ ለ25 ዓመታት በነጻ እንዲገለገል ያስችለዋል፡፡ እድሜውን ሙሉ በዓመት ለአንድ ሳምንት አዲሳባ ሲመጣ  የሚያርፍበትን ሆቴል እንሰራለታለን፡፡

ተቁለጨለጭን፡፡ ‹‹ሁለት ወር ስጡኝና 200 ሚሊዮን ብር ሰብስቤ እመጣለሁ፡፡››

አመንነው፡፡ እውነት ለመናገር ኤርሚን አለማመን ከባድ ነው፡፡

እሱን ይገዳደሩት የነበሩት ብቸኛ ሰው አንድ ኮሎኔል አብረሃ የሚባሉ ሰው ነበሩ፡፡ ፈተና ሆኑበት፡፡ እርግጥ ነው እሳቸው ጥሩ ደንበኛዬ ነበሩ፡፡ ብዙ መሬት አጋዝቻቸዋለሁ፡፡ ኤርሚያስ ሲታሰር ግን ገነው ወጡ፤ ሪልስቴቱን የሚዘውሩት እሳቸው ሆነው ቁጭ አሉ፡፡ ሪልስቴቱ ችግር ዉስጥ የወደቀ ጊዜ ደሞዛቸው 45ሺ ብር አድርሰውት ነበር ይባላል፡፡ በግላቸው የአንድ የጥበቃና ደኅንነት ካምፓኒ ባለቤት ናቸው፡፡ በዚህ ድርጅት ስም ለአክሰስ ብዙ ሥራ ሰርቻለሁ ብለው ራሱን አክሰስን ከሰሱት፡፡ 22 ሚሊዮን ብር በፍርድ ቤት አስወሰነዋል ብሎ ጓደኛዬ ነገረኝ፡፡ ቆራጥ ሰው ናቸው፡፡

ኤርሚ ከመውጣቱ በፊት ኢምፔሪያል ሆቴልን ለሜቴኮች ያሸጥኩለት እኔ ነበርኩ፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ሳይጨርስላቸው ነበር የሄደለው፡፡ አንቀው ያዙኝ፡፡ ዱባይ እንዳለ ነገርኳቸው፡፡ እዚያው ሄደው አስፈርመውት መጡ፡፡ ኮሎኔሉ በዚህ ረገድ የነበራቸው ሚና ቀላል አልነበረም፡፡

ኤርሚያስ በችሎት

አርብ ዕለት ማለዳ Ermi pic

ቀይ መላጣው የሸፈነለትን ነጭ ኮፍያ ችሎት ሲገባ አወለቀው፡፡ ለብሶት የነበረው ቲሸርት የጎረምሳ ነው፡፡ ነጣ ያለ፣ ተካፋች ያልሆነ፣ የራሱ ጨርቅ ኮፍያ ያለው ዘናጭ ቲሸርት፡፡ አለባበሱ ስለሕይወቱ ጠቆም የሚያደርገው ነገር ያለ ይመስላል፡፡ አገጩን የወረሩት ጢሞቹ አንድም ጥቁር ፀጉር አላጀባቸውም፡፡ እንዲያውም ልክ እንደ እስላም ጀለቢያ ነጥተዋል ብል አላጋነንኩም፡፡ ገና ሲያየኝ የሚያምሩትን አኒያን ብልዝ ጥርሶቹን አሳይቶኝ ያስለመደኝና የጥቅሻ ሰላምታ ሰጠኝ፡፡ አፀፋውን መለስኩለት፡፡ እሱ ወደ ችሎቱ ሲገባ ከኔና ከሁለት የታጠቁ ፖሊሶች ዉጭ ማንም አልነበረም፡፡ ገና አግዳሚ ወንበር ላይ እንደተቀመጠ የታዘዙትን የሚፈጽሙ ፖሊሶች የእጅ ሰንሰለቱን ፈቱለት፡፡ አመሰገናቸው፡፡

ችሎቱ ለመሰየም 20 ደቂቃ ሲቀሩት ምድረ ዉሪ ዱሪዬ እስረኛ ከቂሊንጦ ተግዞ ኤርሚ ወደነበረበት የቀኝ አግዳሚ ተወተፈ፡፡ አቤት የታሳሪ ብዛት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታሳሪ እየበዛ ችሎቶች ሞልተው እየፈሰሱ ነው፡፡ ድፍን አገሩ ነው እንዴ እየተሳረ ያለ? እች እድለቢስ አገር በየዘመኑ አሳሪ አያጣትም፡፡ በታሪኳ የታሳሪ እጥረት ገጥሟትም አያውቅም፡፡ የሽክርክሪቱ ምስጢር ምንድነው ያላችሁኝ እንሆን ታሳሪ የሆኑት ሲፈቱ ዞረው አሳሪ መሆናቸው ነው እላችኋለሁ፡፡

የገረጀፈችው የሰባራ ባቡር ችሎት ብዙ ታናግራለች፡፡ አንዲት ደሳሳ ያለ እቅድ የተሰራች የምትመስል ፎቅ ናት አራዳ ችሎት ተብላ ስም የተሰጣት፡፡ የፎቋ ስሪት የመኪና መለዋወጫ ቸርቻሪ ሱቆች ማደሪያ ለመሆን ነበር፡፡ በድንገት ፍርድ ቤት ተከራያት፡፡ በመጀመርያዋ ፎቅ ላይ ሬጅስትራር፣ የዳኛ ቢሮ፣ ችሎት 1 እና ችሎት 3 አዳራሽ ይገኛል፡፡ ሁሉም ክፍሎች በስስ ችቡድ ነው የተሸነሸኑት፡፡ ያሰማማሉ፡፡ እዚያኛው ክፍል ያለ ዳኛ መዶሻ ሲመታ እዚኛው ችሎት ያለ እስረኛ ይበረግጋል፡፡ ሬጂስትራር ያሉ ፀሐፊዎች ማስቲካ ጧ ባደረጉ ቁጥር ችሎቱ ይታወካል፡፡ በኮሪደር ሂል ጫማ የተጫማች ኮረዳ ባለፈች ቁጥር የዳኛ ብያኔ ይደናቀፋል፡፡ ለሥርአቱ የታመኑ ዳኞቹ ደጋግመው ‹‹ሥነ-ስርዓት›› እያሉ ይጮኻሉ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሚሰማቸው የለም፡፡

የእስረኞችን መብዛት ተከትሎ አንዲት ከቂጥም ከቦርጭም አብዝቶ የሰጣት የዋህ ኮስታራ ፖሊስ ወደ ኤርሚያስ ዞራ ‹‹ አንተ! ማነህ!? አንተን እኮ ነው…ወዲያ ተጠጋ!! ›› ብላ አምባረቀችበት፡፡ ኤርሚ ባልንጀራዬ ፈገግ ብሎ ያዘዘችውን አደረገ፡፡

ከጎኑ ድሮ ቢጫ እንደነበረ የሚገመት የነተበ ከነቴራ በሰማያዊ ጂንስ ሱሪ የለበሰ ወጠምሻ  መጥቶ ተቀመጠ፡፡ ልጁ የኤርሚ ማንነት የተገለጠለት አይመስልም፡፡ ትትትትት ይላል ወደ ጆሮው ተጠግቶ፡፡ ልጁ የችሎቱ መጀመር በፖሊስ እስኪበሰር ድረስ ኤርሚን በወሬ ሰንጎ ይዞት ቆየ፡፡ እየተወራጨ ያወራል፡፡ ኤርሚ ተቆጥቦ ይስቃል፡፡ ሻራና ዛንድራን እየተረከለት ሳይሆን አይቀርም፡፡ አይ አለማወቅ! እኔ እሱን ባረገኝ….ዝም ብሎ የባጥ የቆጡን ከሚዘባርቅ ‹‹ኤርሚዬ እስቲ በነካ እጅህ አንዲት ዳሳሳ ጎጆ ቤት ስራልኝ›› ቢለው ምን ነበረበት፡፡ ኤርሚ ያራዳ ልጅ…ለነገሩ ቤት መች ሰርታ ታውቅና፡፡ እንኳን ለሰው ለራሷም እኮ ቤት የላትም፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ እናቱ ቤት ነበር እኮ የሚያርፈው፡፡ እናቱም በቅርቡ አረፉ፡፡ የድሮ ቤታቸው ሳርቤት ካናዳ ኤምባሲ ጎን ነበር የሚገኘው፡፡ ያ ዉቡ ግቢ…አሁን ባንኮች ክሊኒክ ተብሎ ይጠራል፡፡

የኤርሚ አሳዳጊ የአቶ አመልጋ አባት ቤት ነበር ድሮ፡፡ የኤርሚ አባቶች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ አንድ አሳዳጊና አንድ የገዛ አባቱ፡፡ ኤርሚ ያራዳ ልጅ ታዲያ ይህንን ቤት ከንግድ ባንክ ሞቅ ያለ ብድር ተቀብላበት ቢዝነሷን ስታጧጡፍ በሀራጅ አሸጠችው፡፡ ያኔ ብዙ ሰው ኤርሚ ያሳደጉትን ቤተሰቦች ጉድ አረገ አለ፡፡ እኔና ጥቂት ዉስጥ አዋቂ ዳላሎች ግን ኤርሚ ብልጧ! ብለን ተሳሳቅን፡፡

ችሎት ተጀመረ

1ኛ ችሎት ላይ ዳኛ ወይዘሪት ማስተዋል ሲገቡ አሳሪዎች፣ ታሳሪዎችና የታሳሪ ቤተሰቦች ቆሙ፡፡ ዳኛ ወይዘሪት ማስተዋል ሲቀመጡ አሳሪ፣ ታሳሪና የታሳሪ ቤተሰቦች አብረው ተቀመጡ፡፡

ዳኛ ወይዘሪት ማስተዋል በክላሰር ከፊታቸው ከተቆለላቸውን ፋይል ዉስጥ አንዱን መዘው፣ ‹‹አቶ ኤርሜያስ ቀርበዋል?›› ብለው ጠየቁ፤ ወደ አቶ ኤርመያስ ዞረው እያዩ፡፡ እየተመለከቱም መጠየቅ የፍርድ ቤት ወግ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አቶ ኤርሜያስ ቀልጠፍ ብለው ‹‹እኔ ቀርቤያለሁ፤ ኾኖም ጠበቆቼ ከአራዳ ፍርድቤት የማስፈቻ ወረቀት ለማምጣት ሄደው እዚያው ነው ያሉት…ትንሽ ብንጠብቅ ይደርሳሉ›› ብለው ተናገሩ፡፡

ወይዘሪት ማስተዋል ጥቂት እንደማስተዋል ካሉ በኋላ ወደ ሌላ ፋይል ዞሩ፡፡

‹‹አቶ አሊ አፋር ቀርበዋል?››

አሊ አፋር ያ ኤርሚን በወሬ ሲነተርከው የነበረው ጎረምሳ ነው፡፡ ቢጫ ከነቴራ በጂንስ ለብሷል፡፡ ስሙ ሲጠራ ቆመ፡፡ ዜጎችን ወደ ሳኡዲ በህገወጥ መንገድ ለማስተላለፍ ሞክረሃል፤ የሰው አስተላላፊ ደላላ ነህ ተብሎ ነው የተከሰሰው፡፡ ይሄ መንግሥት እራሱ ደላላ ሆኖ ለምን ደላላ አምርሮ እንደሚጠላ አይገባኝም፡፡ ከሚሌና ከኦሮሚያ አካባቢ ለሱ ሁለት ሺ አምስት መቶ ብር ሰጥተናል ያሉ ‹‹ተላላፊ›› ሰዎች አንድ በአንድ እየመጡ መሰከሩበት፡፡ ጠበቆች መስቀለኛ ጥያቄ ሲጠይቋቸው ግን ‹‹ፖሊስ በሱ ካልመሰከራቹ ወደ አገራቹ አንልካችሁም ብሎ ለአንድ ወር ከአንድ ሳምንት እየገረፈ እንዳሰራቸው›› ጠቆም አደረጉ፡፡ የወጣት አሊ አፋር ምስክሮች ከመብዛታቸው የተነሳ ቢቀጣጠሉ እዚያው ያሰቡበት ሳኡዲ አረቢያ መድረስ የሚችሉ ናቸው፡፡

ምስክር የመስማቱ ሂደት እጅግ የተንዛዛና ለሦስት ተከታታይ ሰአታት የዘለቀ ነበር፡፡ ብዙዎቹ መስካሪዎች አማርኛ መናገር የማይቸሉ ስለነበሩ በአስተርጓሚ መታገዝ ነበረባቸው፡፡ ይህም ሌላ መንዛዛትን ፈጠረ፡፡ በዚህ ሁሉ ሰዓት ኤርሚ ብልጧ የሆነ ትልቅ ዶሴ ከጠበቃ ሞላ ዘገየ ተቀብላ አገላብጣ ታነብ ነበር፡፡ ችሎቱን የታደሙ የኤርሚ እህቶች አንዷ በአንጻሩ ቅንጡ ሞባይሏን ከፍታ ‹‹ካንዲ ክራሽ›› የተሰኘውን አጓጊ ጌም እየተጫወተች ነበር፡፡

የኤርሚ ችሎት መጀመር

ኤርሚ ድንጋይ ያናግራል ይባላል፡፡ እውነት ነው፡፡ እንዲያውም ያንሰዋል፡፡ ድንጋይ ያስለቅሳል፡፡ ከማማሩ፣ አንደበቱ፣ ከአንደበቱ፣ ዕውቀቱ፣ ከዕውቀቱ፣ ቀልጥፍናው፡፡ አእምሮው ስል ነው፡፡ አንድም ትርፍ ስጋ ያልፈጠረበት ሰውነቱን እንዳሻው ማዘዝ ይችላል፡፡ ሰውነቱን ብቻ ሳይሆን ሰውም ይታዘዝለታል፡፡

ኤርሚ ይዞት የመጣውን ሀሳብ ዉድቅ ማድረግ የሚችል ሰው የለም፡፡ ድምጽ መስጠት ብቻ ነው የሚያዋጣው፡፡ አክሰስ ወፋፍራም የቦርድ አባላት ነበሩት፣ አሉት፡፡ ስብሰባም ይቀመጡ ነበር፡፡ ስብሰባቸው የኢህኤደግ ፓርላማን እየመሰለ ሲመጣ ግን ሁሉን ነገር በኤርሚ ላይ ጥለው ጠፉ፡፡ ኤርሚ ፍጹም ነው ብለው ለማመን ተገደዱ፡፡ ፍጹም ሰው ‹‹አማካሪ ምክር ቤት›› ስለምን ያሻዋል ብለው ተበተኑ፡፡

የዛሬው እስረኛ ኤርሚ ርቱእ አንደበቱ ለፍርድ ቤት ባይመጥን ይሆን ሁለት ምን የሚያካክሉ ጠበቆችን ያቆመው? በዕለቱ ሁለቱም ጠበቆቹ ዘግይተው ነበር ችሎት የደረሱት፡፡ አቶ ሞላ ዘገየም ይዘገያሉ እንዴ? ባለፀጋው አቶ ሞላ አዘውትረው የሚቆሙት ለባለፀጎች ነው፡፡ ድምጻቸውና ቁመናቸው ከአበበ ባልቻ የሚስተካከል ነው፡፡ ሆቴል አላቸው፣ ሎጅ አላቸው፣ የአስጎብኚና የጎዙ ወኪል አላቸው፡፡ የሚያዙበት ጋዜጣ ብቻ ነበር ያልነበራቸው እሱንም ሰሞኑን ከፈቱ፡፡ ሚዲያው ጽንፍ እየያዘ ሲያስቸግራቸው ‹‹ዉይይት›› ብለው መጽሔት ከፈቱ፡፡ ይህን መጽሔት ለመክፈት ያወጡት ገንዘብ ግማሽ ሚሊዮን እየደረሰ ነው፡፡

ለባለንጀራዬ ለኤርሚያስ የሚመጥኑ ጠበቃ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ ጠበቃ መኮንን ከጎናቸው አሉ፡፡

በዕለቱ የሞያ ምስክርና አስተያየት እንዲሰጡ የአራት ሰዎችን ቃል ለመስማት ነበር የተቀጠረው፡፡ ሁሉም በአቃቤ ሕግ በኩል የቀረቡ ናቸው፡፡ የዘመን ባንክ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅና የዘመን ባንክ ፕሬዚደንት ይገኙበታል፡፡ ኤርሚ አምጦ የወለደው ባንክ በርሱ ላይ ሊነሳ ይሆን ብለን ሰጋን፡፡  የኤርሚን አገር መልቀቅ ተከትሎ ቼክ የያዙ ደንበኞች ወደ ባንካቸው መጉረፍ እንደጀመሩ፤ አክሰስ ሪልስቴት አካዉነት ዉስጥ በቂ ስንቅ ስላልነበረ አካውንቱ በብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት እንዲዘጋ መደረጉን ለፍርድ ቤቱ አስረዱ፡፡

አቶ ደመላሽ ሮባ የተባሉ ሰው በዕለቱ የቀረቡ ሌላው ምስክር ነበሩ፡፡ እኒህ ዘለግ ያሉና ሽበት የወረራቸው ጥቁር ሰው ለፍርድ ቤት እንዲህ አሉ፡፡

‹‹ ለወንድሜና ባለቤቱ ወይዘሮ ጽጌረዳ አበበ መንገሻ ሕጋዊ ወኪል ነኝ፡፡ ወንድሜ ከዉጭ ደውሎ ከአክሰስ 2 አፓርታማዎችን ግዛ አለኝ፡፡ በ3 ሚሊዮን ብር ሁለት አፓርታማ ገዛሁ፡፡ አንድ ከቦሌ ሜጋ፣ አንድ ከቦሌ ጃፓን አካባቢ፡፡ ምን ዋጋ አለው ታዲያ…ብጠብቅ ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡ ብጠብቅ የለም፡፡ ወደ አቶ ኤርሜስ ዘንድ ሄጄ ቢያንስ የአንዱን አፓርታማ ብር  መልሱልኝ አልኩ፡፡ ወለዱን ከፈለኝና ቼክ ጻፈልኝ፡፡ የ500 ሺ ብር ቼኩን ይዤ በቀኑ ዘመን ባንክ ሄድኩ፡፡ የባንኩ ሰራተኞች ወደ ኤርሜያስ ደወሉና አገናኙኝ፡፡ ‹‹አቶ ደመላሽ…በዚህ ሰዓት ጉሮሮዬ ላይ ለምን ትቆማለህ?›› አለኝ፡፡ አሻፈረኝ አልኩ፡፡ ‹‹እባክህን ትንሽ ታገሰኝና የሚቀጥለው ረቡዕ ወይም አርብ ብር ይገባል፣ ያኔ ትወስዳለህ›› ሲለኝ…፤

‹‹ዝም በል ባክህ…ያንተ አርብና ረቡዕ ማብቂያ የለውም አልኩት›› አሉ፡፡ የተከበረው ፍርድ ቤት ሳቁን መቆጣጠር ተሳነው፡፡

አቶ ንጉሴ የተባሉና የአክሰስ ካፒታል ሰራተኛ የሆኑ፣ ኤርሜያስ አመልጋን ለ17 ዓመታት የሚያውቋቸው ሰው ቃለ መሐላ ፈጽመው የመስካሪ ወንበር ላይ ተቀመጡ፡፡ ሰውየው ለፍርድ ቤት እንዳስረዱት ‹‹በአገር ዉስጥ ገቢ ምክንያት ችግር ላይ ያለ ካምፓኒ አለ፤ ካምፓኒውን ከሞት ካዳነው በኋላ አክሰስ ሊገዛው ይፈልጋል፣ ብር አነሰን ተባልኩ፡፡ ለአክሰስ አምስት መቶ ሺ ብር አበደርኩ፡፡ ከጊዜ በኋላ ገንዘቤ እንዲመለስልኝ ቼኩን ይዤ ብሔድ ደረቅ ቼክ መሆኑ ተነገረኝ››› ሲሉ አስረዱ፡፡

ከነዚህ መስክሮች ባሻገር ፍርድ ቤቱ አቶ ሄኖክ ተስፋዬ የተባሉ የዘመን ባንክ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ የሞያ አስተያየትን ሰምቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የኤርመያስ ጠበቆችን መስቀለኛ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ካደረገና ካከራከረ በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮውን ለሰኔ 5 አደረገ፡፡ በጤና ምክንያት ሚሪንዳ እየጠጡ ችሎት የታደሙት ጠበቃ ሞላ ዘገየ ጎላ ያለ ድምጻቸውን ይበልጥ ጎላ አድርገው ‹‹ክቡር ፍርድ ቤት! የምናገረው አለኝ! ደንበኛዬ የዋስትና መብቱ አሁንም ድረስ ተፈጻሚ አልሆነለትም…›› ብለው አቤቱታ ማሰማት ሲጀምሩ ዳኛ ማስተዋል ጣልቃ ገብተው ‹‹በዚህ መዝገብ ተከሳሽ ዉጭ ሆነው መከላከል እንደሚችሉ ብይን ሰጥቻለሁ፤ ሌላ ክስ ካለባቸው የሚመለከተውን ችሎት ጠይቁ›› በማለት ቁርጥ ያለ ምላሽ ሰጥተው አሰናበቱን፡፡ (ዋዜማ ራዲዮ)