(በሙሔ ሐዘን ጨርቆስ-ለዋዜማ ራዲዮ ብቻ)

ውድ የዋዜማ ሬዲዮ ታዳሚዎች! እንዴት ሰነበታችሁ!?

እኔ ደኅና ነኝ፡፡ የመሃል አገር ሰው ምን ይሆናል ብላችሁ ነው! ምን ቢከፋ ጦሙን አያድር!

ከሁለት ኩማዎች፣ ከአንድ አሊ፣ ከአንድ አርከበ፣ ከአንድ ይልማ ወዘተ በኋላ በአዲሳባ ሦስት ነገሮች ጠፍተዋል፡፡ የሚንጫጩ ወፎች፣ የሚፈስሱ ወንዞች እና ገላጣ መጫወቻ ሜዳዎች፡፡  ለነገሩ…ድሮም የሚያዳምጥ በጠፋበት ከተማ ወፎች አይዘምሩም፣ ቢዘምሩም “ሌባ ሌባ…” እያሉ ነው። ድሮም  ሙሰኛ በበዘበት ከተማ ወንዞች አይፈስሱም፡፡ ቢፈሱም በሽንት ቤት ፍሳሽ ደፍርሰው ነው፡፡ ድሮም ሕጻናትን የምትበድል ከተማ ገላጣ ሜዳዎች አይኖሯትም፡፡ ቢኖሯትም የታጠሩ ናቸው፡፡

(ይህ ጦማር በድምፅ ተሰናድቶ እንዲህ ቀርቧል፣አድምጡት)

ውድ የዋዜማ ሬዲዮ ታዳሚዎች!

እውነት እውነት እላችኋለሁ….! ባለፉት ሁለት አስር ዓመታት ውስጥ ከበርማዋ አን ሳን ሱ ኪይ ቀጥሎ እድሜውን በቁም እስር ያሳለፈ የዓለም ዜጋ ቢኖር በኮንዶሚንየም ውስጥ የተወለዱና ያደጉ የአዲሳባ ታዳጊዎች ብቻ ይመስሉኛል፡፡ ሱ ኪይ እንኳን አሳሪዎቿ ፈተዋት ሰሞኑን በምርጫ ዘረረቻቸው አሉ። ይብላኝ ላልተፈቱት የኮንዶሚኒየም ልጆች።

እርግጥ ነው በሐበሻ ምድር ንጹሐን በገፍና በግፍ ይታሰራሉ! በምክንያትም ያለምክንያትም፡፡ ሆኖም እስክንድር ነጋ ቢታሰር ዙርባ የፖለቲካ ጥያቄ አንስቶ ነው፤ ተመስገን ቢታሰር ልክ ልካቸውን ተናግሮ ነው። ኦልባና ቢታሰር፣ አንዷለም ቢታሰር፣ አቡበከር ቢታሰር የመብት ጥያቄ አንስተው ነው፡፡ ያዲሳባ ሕጻናት መታሰራቸው ስለምን ይሆን?

===============

ከዋናው ፖስታ ቤት ማዶ፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጀርባ፣ በኢትዮ-ኩባ አደባባይ አስፋልት ላይ ኳስ ለሚያንከባልሉ የኮንዶምንየም ነዋሪ ታዳጊዎች የፀሐዩ ንዳዱ ምንም ማለት አይደለም፡፡ በማንኛውም ደቂቃ ይህ በስስት የሚያዩት የአስፋልት ሜዳቸው በ“ፐብሊክ ባሶች” ሊወሰድባቸው ስለሚችል ጊዜ አያባክኑም፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ፐብሊክ የሚለውን ቃል ወደ አገርኛ ቋንቋ የሚመልስ አልተገኘምና አውቶብሶቹን በዚያው ስም እንጥራቸው። ፐብሊክ ባሶቹም ሌላ መቆምያ የላቸውም፤ ልጆቹም ሌላ መጫወቻ ሜዳ የላቸውም፡፡ ይሄኔ የግዙፍ አውቶቡሶችና የደቃቃ ሕጻናት ፍጥጫ ይጀምራል፡፡

Public Buses at Mesqel Square
Public Buses at Mesqel Square

አዲሳባ ባዶ ስፍራ የላትም፡፡ ሽጣ በልታዋለች፡፡ ከዛሬ ነገ ሁለቱን የቀሯትን ባዶ ስፍራዎች በሊዝ እንዳትሸጣቸው እየተፈራ ነው፤ ኩባ አደባባይና መስቀል አደባባይን! ሁለቱም አደባባዮች በቀድሞ ሥርዓቶች የተሠሩ ናቸው። ልጆቹ ግን ሜዳ እንጂ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች አይደሉም። “ፐብሊክ ባሶቹ” አደባባዮቹን “ለሕዝብ ጥቅም” በቁጥጥር ስር ሲያውሏቸው ምስኪኖቹ ልጆች በብልግና እየተሳደቡ ወደየኮንዶምንየሞቻቸው ይበተናሉ፡፡ ልጆቹ በብልግና የሚሰድቡት የባስ ሾፌሮቹን እንጂ ከተማዋን ባለማወቅ ማርሽ ሾፍረው፣ በሙስና ፈረስ ጋልበው፣ ሜዳ አልባ ያረጓቸውን አስተዳዳሪዎች አይደለም፡፡ ይህን ለመረዳት አእምሯቸው ገና አልጠናም፡፡

አዲሳባ በፎቅ ፎንቃ ወድቃለች፡፡ ክፍት ቦታ ካየች ለነገ አትልም፡፡ ቁጥራቸው ከሦስት መቶ ሺህ ለሚዘሉ ታዳጊ ዜጎቿ አንድም የመጫወቻ ሜዳ አልተወችላቸውም፡፡ በመሐል ከተማ ለልጆች ብሎ ባዶ ቦታ መተው በገዢዎቿ የተንሸዋረረ የከተማ ፕላን መሠረት ቅንጦት ብቻም ሳይሆን ጸረ-ልማታዊነት ነው፡፡ በመሆኑም ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ አዲሳባ ሜዳዎቿን በባትሪ እየፈለገች አጥራቸዋለች፣ ሸንሽናቸዋለች፣ ቸብችባቸዋለች፣ አምክናቸዋለች፡፡ “የማዘጋጃ” ሜዳ አንዱ ነው፡፡ 35ሺህ ካሬ ታጥሮና መክኖ ከተቀመጠ እነሆ በመጪው ግንቦት ድፍን 18ኛ ዓመቱን ያከብራል፡፡

===================

ከኮብልስቶን የተሠሩ የእግር ኳስ ሜዳዎች

ምስጋና ለገዢው ፓርቲና ለታጋሹ 4 መቶ ሺ ተመዝጋቢ ይሁንና፣ ከ97 ምርጫ ወዲህ 105 ሺህ የጋራ መኖርያ ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች ተላልፈዋል፡፡ በነዚህ ቤቶች ዉስጥ በአማካይ ግማሽ ሕጻን/ታዳጊ ይኖራል ብለን ብናስብ እንኳ በአዲሳባ 52 ሺ ሕጻናት/ታዳጊዎች በኮንዶሚንየም ውስጥ ታጉረዋል ማለት ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ተጨማሪ 200ሺ ቤቶች ለነዋሪዎች ይተላለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ያን ጊዜ በድምሩ 150 ሺ ሕጻናትና ታዳጊዎች ማጎርያውን ይቀላቀላሉ ማለት ነው፡፡ ኮንዶሚንየሞቻችንን ስለምን “የሕጻናት ማጎርያ ካምፖች” ብዬ እንደጠራኋቸው አብራራለሁ፡፡

የትምህርት ቢሮ በቅርቡ ባወጣው አንድ አሐዝ አዲሳባ ዉስጥ 980 የሚሆኑ መዋእለ ሕጻናት ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ ታዲያ ለልጆች የሚሆን ምቹ ግቢ የላቸውም፡፡ እቤታቸውም ትምህርት ቤታቸውም መጫወቻ የሌላቸው ልጆች። ደፋር ታዳጊዎች ብቻ በየኮንዶሚንየሙ ግቢ ለመኪና ማቆምያ በተሠሩ “የኮብልስቶን ሜዳዎች” እየተሸሎኮሎኩ በአደገኛ ሁኔታ ይጫወታሉ፡፡ ለሕጻናቱ ተብሎ የተዘጋጀ ስፍራ ያላቸው የጋራ መኖርያ ቤቶች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ “የሰሚት አንድ” ኮንዶሚንየም ምናልባትም ብቸኛው ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡ የሚገርመው አሁን በሚገነቡት የ40-60 የጋራ መኖርያ ቤቶች ውስጥም ለሕጻናቱ በቂ ትኩረት የተሰጠ አይመስልም፡፡

በፎቅ ርዝመት ክፉኛ የሚነሆልለው ገዢው ፓርቲ በሚያካሄዳቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ እስከነመፈጠራቸው ከሚረሳቸው ዜጎች ዉስጥ አካል ጉዳተኞችና ሕጻናት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ለማኅበራዊ እሴቶች ዋጋ ሰጥቶ ምህንድስናን ማካሄድ እምብዛምም ትዝ የሚለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው የመከኑ ግንባታዎችን በየወረዳው የምናየው፡፡

Condos near to Balderasu
Condos near to Balderasu

###

ውድ የዋዜማ ሬዲዮ ታዳሚዎች!

በኢህአዴግ ዘመን የመንግስት ሠራተኛ ልጅ ከመሆን የወታደር ባለሥልጣን ልጅ መሆን በተሻለ ሁኔታ ለማደግ ተስፋ ይሰጣል ልበል? “ሲግናል” የሚገኙ የጋራ መኖርያ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ የወታደራዊ መኮንኖች ልጆች ባየሁ ጊዜ ተገረምኩ፤ እንዴት እንደሚያስቀኑ፡፡ ይቦርቃሉ፣ ኳስ ያንከባልላሉ፣ አባሮሽ፣ ሌባና ፖሊስ፣ “ቅድምድሞሽ” ይጫወታሉ፡፡ ለምን ቢባል ግቢያቸው ለመኪና ማቆምያ፣ ለአትክልት ቦታና ለሕጻናት መጫወቻ የተመቸ ኾኖ በመቀየሱ ብቻ፡፡ ታዲያ ይህንኑ መድገም እንዴት አቃተን?

በሲግናል የጋራ መኖርያ ጀርባ የባልደራሱ ኮንዶሚንየም ይገኛል፣ ከሲግናል ማዶ ደግሞ የአድዋ ድልድይ ኮንዶምንየም በሁለት ጭርንቁስ ቀበሌዎች ውስጥ ተሰንጓል፡፡ በሁለቱም ኮንዶምንየሞች ዉስጥ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ሦስት ሕጻናት ከፎቅ ወድቀው መሞታቸው ተነግሯል፡፡ ከደረጃ ሾልከው አካል ጉዳተኛ የሆኑትን የየኮንዶሚንየሙ ስቱዲዮ ይቁጠራቸው፡፡ በእነዚህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዉስጥ ከ2ኛ ፎቅ በላይ በተደራራቢ አልጋ የሚተኙ ሕጻናት በተለይ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በአልጋው ከፍታ ምክንያት ከመኝታ ቤታቸው መስኮት ሾልከው ሕይወታቸው ስላለፉ ሕጻናት ሰምተናል፡፡ ለዚህም ነው ልጆች ያሏቸው የኮንዶሚንየም ተከራዮች ገና ዕቃ ማጓጓዝ ከመጀመራቸው አስቀድመው የመስኮት ፍርግርግ ብረት ማስበየድ የሚጀምሩት፡፡

የሕጻናት ከፎቅ ላይ ተፈጥፍጦ መሞት በየትኛውም የአዲሳባ ኮንዶሚንየም ውስጥ ብርቅ ዜና አለመሆኑ ብዙ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ ጀሞ፣ ጎተራ፣ ገርጂ፣ አቃቂ፣ አድዋ፣ እንደራሴ፣ መገናኛ፣ ባልደራሱ፣ ባሻወልዴ፣ ሰሚት-1-2-3፣ አያት፣ ልደታ፣ ተክለሐይማኖት…ሁሉም ኮንዶሚንየሞች ቢያንስ አንድ ሕጻን ገብረዋል፡፡ እነዚህ ሕጻናት ለምን ሞቱ ብሎ መጠየቅ ቅንጦት ነው? እድገትን ማንኳሰስ ነው? ጨለምተኝነት ነው?

ለመሆኑ እነዚህን ስንኩል የጋራ መኖርያ ቤቶች የቀየሱ የጥቃቅንና አነስተኛ መሐንዲሶች፣ በኃላፊነት ያስገነቡ ባለስልጣናት፣ ተቆጣጣሪ ኾነው ያሠሩ ሆዳደር አማካሪዎች፣ በሕጻናቱ ከንቱ ሞት ምን ይሰማቸው ይሆን? ለመሆኑ የሟች ሕጻናት ቤተሰቦች ካሳ አግኝተዋል?

መቶ ሺ የጎዳና ልጆች ቱቦ ዉስጥ በሚያድሩበት አገር ስለ መጫወቻ ሜዳ ጉዳይ ጦማር ማርቀቄ ስሜት የማይሰጣቸው እንዳሉም እገነዘባለሁ፡፡ ለሕጻናት መጫወቻ ቦታ ማዘጋጀት ሀብታም አገር ከመሆን ጋር የሚያያይዙትም አይጠፉም። ለእኔ ግን የዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ምንጭ የአስተሳሰብ ድህነት እንጂ የሀብት እጦት አይመስለኝም፡፡ ይህን ደግሞ የሚመሰክርልኝ ብዙም ባልተራራቀ የግንባታ ወጪና የቦታ ስፋት የተገነባው የወታደሮቹ ቤት ነው፡፡ ሲግናል!!!!

Signal military officers condo
Signal military officers condo

አገሬ ለጋራ መኖርያ ቤቶች ግንባታ በድምሩ 17 ቢሊዮን ብር ከስክሳለች፡፡ በዚህ ገንዘብ መሠራት የቻለው የጋራ መኖርያ ቤት ስለምን ልጆችን የሚያገል ኾኖ እንደተቀየሰ ማብራሪያ የሚሰጥ አካል እስካሁን አልተገኘም፡፡ ሳሎን ቤታቸው ዉስጥ ዥዋዥዌ ለመጫወት የተገደዱ ልጆች አያሳዝኑም? ነፍስ በቅጡ እንኳ ያላወቁ ሕጻናት ከታች የሚኖሩ ተከራዮችን ላለመረበሽ ተጨንቀው ሲራመዱ ማስተዋል አያምም? በመጫወቻ ሜዳ እጦት ከወላጆቹ ጋር ካርታ ለመጫወት የተገደደች የሕጻን ነፍስ አልተበደለችም? ልጅን የቁም እስረኛ አድርጎ ማሳደግስ ግፍ አይደለም? በምድር ባያስቀስፍ በሰማይ ቤት አያስኮንንም? ሕጻን እንዴት አትጫወት ይባላል? ሕጻናት እንዴት እንደ አዋቂ ወግ እያወጉ ስቱዲዮ ቤት ተከርችሞባቸው ይዉላሉ? ከዚህ በላይ በሕጻናት ላይ ሊፈጸም የሚችል ምን ወንጀልስ ይኖራል?

ውድ የዋዜማ ሬዲዮ እድምተኞች!

በኮንዶሚንየም ዉስጥ በሙሉ ጤንነት የተወለዱ ሕጻናት አካል ጉዳተኛ ያደረጋቸው በተማረ ሰው እምነት የማይጥለው የኢህአዴግ አስተዳደርና ሰንካላ አስተሳሰቡ እንደሆነ በጽኑ አምናለሁ፡፡ እንጂማ በተመሳሳይ ወጪ ሕጻናትን ያማከለ የጋራ መኖርያ አቅዶ መገንባት የማይቻልና ውስብስብ ሊሆን ባልተገባ ነበር፡፡

በእኔ በኩል ኢህአዴግ ከተሜን ለማስተዳደር በስነልቦናም ኾነ በአስተሳሰብ እንደማይመጥን ከሚመሰክሩልኝ ሁነኛ ነገሮች አንዱ የኮንዶምንየሞቻችን አሠራር ነው፡፡ ኢህአዴግ የቀጫጫ አስተሳሰብ ባለቤት በሆኑና በአመዛኙ የትምህርት ፀበል ባልተረጩ ካድሬዎች የሚዘወር ፓርቲ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ከኮንዶምንየሞች በላይ የሚመሰክር የቁም ሐውልት የለም፡፡ ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ያለው ሰው ለቤት ጠባቂ ዉሻው ቤት ሲሠራ መስኮት ያበጃል፣ አፍኖ አይገድልም፡፡ ሕጻናት ተወልደው በሚያድጉበት የጋራ መኖርያ ስለምን የልጆች መጫወቻ ሥፍራ ተዘነጋ? ለመሆኑ ለዚህ የምህንድስና ቀይ ስህተት ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ አመክንዮ ይኖረው ይሆን?

=======================

ወደ ኢትዮ- ኩባ አደባባይ ልመልሳችሁ!unsafe condos

በአደባባዩ የሚገናኙትን ከኮንዶሚኒየም የሚሰባሰቡ የሜዳ ስደተኞች የሚያሰለጥናቸው ታዲዮስ የተባለ ወጣት አለ። ልጆቹ ‹‹ሞሪንሆ›› እያሉ ያሞካሹታል፡፡

“ፀሐዩ ነው መሰለኝ አንዳንዴ ራሳቸውን ይስታሉ..በየ20 ደቂቃው በግድ አሳርፋቸዋለሁ” ይላል አሰልጣኝ “ሞሪንሆ” ዐይኑን ለአፍታም ከልጆቹ ሳይነቅል፡፡

“የሳር ሜዳ አጥተህ ነው ግን ልጆቹን እዚህ የምታመጣቸው?” የትንኮሳ ያህል የሚሸነቁጥ ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡

“ኸረ ጀለስ! የክፍለሃገር ልጅ ነሽ እንዴ?!” ከት ብሎ ሳቀብኝ፡፡ ሳቁ ሜዳ አልባዋን ከተማ በቅጡ እንደማላውቃት ለማመላከት የታለመ ስላቅ እንደሆነ ተረድቻለው፡፡

ሌላው የሜዳ አማራጭ “አብዮት” ነው፡፡ እዛም ቦታ ማግኘት የማይሞክር ነው፡፡ ከማለዳው 11፡30 ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ ምንም ቦታ አይገኝም፡፡ “ጀለስ…የአብዮት ሜዳን ትልልቆች ከያዙት ቀኑን ሙሉ አይለቁልህም፡፡” ይላል ታዲዮስ በልዩ ጥበብ ኳስ የሚያንከባልሉትን ታዳጊዎች በርቀት እየተቆጣጠረ፡፡

በዚህ የኢትዮ-ኩባ አደባባይ አስፋልት ላይ የሚታዩት ልጆች በአመዛኙ እድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች ነው፡፡ ደማቅ አረንጓዴ የስልጠና ሻማ ማሊያቸው ላይ ደርበዋል፡፡ ከዚያ ውጭ ቢወድቁ ሰውነታቸውን ከጉዳት የሚከላከልላቸው ነገር የለም። የጥቂቶቹ ቅልጥም ጅብ ጀምሮ እንደተወው አጥንት ተጋግጧል፡፡ በፍጹም ወኔ፣ በፍጹም ስሜት ነው የሚጫወቱት፡፡ ተንሸራተው ኳሷን ለማግኘት ሲረባረቡ ስፖንጅ ፍራሽ ላይ እንጂ አስፋልት ላይ የሚጫወቱ አይመስሉም፡፡

የእነርሱን መጨረስ የሚጠባበቁ ሌሎች ሦስት የታዳጊ ቡድኖች ፈንጠር ብለው ‹‹መሐል ባልገባ›› ይጫወታሉ፣ ተራቸው ደርሶ ሜዳው እስኪለቀቅላቸው ልባቸው ተንጠልጥሏል፡፡ በልጆቹ ከፍተኛ የግል የኳስ ጥበብ የተማረኩ መንገደኞች ከአጣዳፊ ጉዳያቸው ተናጥበው ፈዘው ልጆቹን ይመለከቷቸዋል፡፡ ጎል ሲቆጠር በአድናቆት አፋቸውን ከፍተው ያጨበጭባሉ፡፡

ከአሰልጣኝ ታዲዮስ (ሞሪንሆ) ጋር ለሩብ ሰዓት በስፍራው ተቀመጥኩ፡፡ ስለሕይወቱ እያወጋኝ በየመሐሉ ይቁነጠነጣል፡፡ ልጆቹ ላይ ያለማቋረጥ ይጮኽባቸዋል፡፡ ጆሮውን ለኔ ሰጥቶኝ ዓይኑ ከኳሷና ከልጆቹ ጋር ይንከራተታል፡፡ ለአፍታም ወደኔ አይዞርም፡፡ ግን ቶሎ ቶሎ ይቆጣል፡፡

“አንቺ ሳንቾ! የዛች የእንትን ልጅ! ኳስ ልቀቂ ማለት አማርኛ አይደለም እንዴ! ጅብ!”

ለልጆቹ የማይመጥኑ ቃላትን ጭምር እየተጠቀመ ይወቅሳቸዋል፡፡ “ጅብ!” የሚለው ስድቡ ከአፉ ሲወጣ የምርቃት ያህል ቀሎት ነው፡፡

“አስፋልቱ አይጎዳቸውም ግን? ማለቴ ልጆች ስለሆኑ…” አልኩት ተለሳልሼ፡፡

“ትቀልዳለህ?” በሚል አይነት ገልመጥ አድርጎ አይቶኝ ምልከታውን ወደ ልጆቹ አዞረ፡፡ ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ እንደሰነዘርኩ ተሰማኝ፡፡

‹‹አንቺ…ጉቶ…ኸረ ተይ ሰው የሚልሽን ስሚ….ኳስ አትብይ አላልኩሽም…ጅብ!” በድጋሚ ጮኸ!

“ምን ነበር የጠየቅሽኝ ቀዮ?” ኳስ ፎሪ ስትወጣ ፊቱን በከፊል ወደኔ መልሶ ጠየቀኝ፡፡

“አ…ይ ልጆቹ አስፋልት ላይ ሲጫወቱ አይጎዱም ወይ…ማለቴ…”

“ቀላል ይጎዳሉ እንዴ! ፋብሪን አታውቂያትም እንዴ? የኔ ልጅ ነበረች፡፡ ምን ዋጋ አለው እግሯ ተሰበረ፡፡ በሷ ነበር ያልፍልኛል ያልኩት፡፡ ቬንገር ቋጣሪ ነው አይደል? እናቴ ትሙት ቬንገር ፋብሪን ቢያያት ባልኩት ዋጋ ይገዛኝ ነበር፡፡ ብታያት እኮ ቅመም ልጅ ናት፡፡ እሷን ለማየት እዛ ጋ ብዙ መንገደኛ ይቆም ነበር፡፡ መኪናቸውን አዙረው መጥተው የሚያይዋት ሞጃዎች ሁሉ ነበሩ፡፡ እናቴ ትሙት ነው ምልሽ እሷ ለብሔራዊ ቡድን አይደለም ለባርሳ ታዳጊ ብትሰለፍ እልል ያለ አጥቂ ነበር የሚወጣት፡፡ ገብርኤልን እያጋነንኩ አይደለም፡፡ ካላመንክ ማንንም ጠይቅ…”

“ስንት ዓመቱ ነበር?”

“ማን ፋብሪ?”

“አዎ!”

“እሷ 14 ነው የምትልህ፡፡ “እኔ ግን ማንም ቢጠይቅሽ አስር ዓመትሽ ነው በይ” ብያታለሁ፤ አትሰማኝም፡፡ ተጫዋች እድሜዉን ካልቋጠረ በኋላ ሃርድ ነው፡፡”

“ፋብሪ እውነተኛ ስሙ ነው ግን?”

“አይደለም፡፡ የኳስ ስሟ ነው፡፡ ሙሉ ስሟ ፋሪስ ሐሰን ነው፡፡ እኛ ግን ፋብሪ-ፋብሪጋዝ ነበር የምንላት፡፡ እዚህ የጎላ ሚካኤል ልጅ እኮ ናት፡፡ እንዴት አታውቃትም? ተክለሃይማኖት ኮንዶምንየም ነው የምትኖረው”

“የፕሮጀክት አሰልጣኞች አይተዋት ያውቃሉ?”

“እንዴ! ሰውነትን ሁሉ ይዤው መጥቼ አሳይቼዋለሁ፡፡ ቀላል አደነቃት እንዴ? እንዳይሰብሯት በጣም ነበር የምሳሳላት፡፡ የዛሬ 2 ወር እኮ ነው ከዛኛው ብረት ጋር የተላተመችው፡፡ ታምነኛለህ?! እግሯ እንደዚህ ዞረ፡፡ ገብርኤልን እውነቴን ነው! እዚህ የሚቆሙት እኛውልህ እነዛ ላዳዎች ናቸው ሆስፒታል ያደረሷት፡፡ አሁንም ብር አዋጥተው የሚያሳክሟት እነሱ ናቸው፡፡ በጣም ነው የሚወዷት፡፡ እንዴት አታቂያትም ግን ፋብሪን፤ በመስተዳደር ቲቪ ሁሉ ቀርባለች እኮ፣ እኔ ራሱ ኢንተርቪ ሰጥቻለው፡፡”

የማላውቀው ታዳጊ ፋሪስ ሐሰን አሳዘነኝ፡፡ ገላጣው የኩባ አደባባይ አስፋልትን ከዋናው የፖስታ ቤት የመኪና አስፋልት የሚለየው ቀይና ነጩ ፍርግርግ ብረት ነው የፋብሪን እግር ከጥቅም ዉጭ ያደረገው፡፡ እዛው ተቀምጬ ልጆቹ ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ከዚሁ ብረት ጋር ሲላተሙ አስተውያለሁ፡፡ ምንም አልሆኑም ግን፡፡ ኳሷ ነጥራ ብረቱን ስትሻገርባቸው ደግሞ ዋናው አስፋልት ላይ ዘለው ይገባሉ፡፡ ኳሷን ከመኪና ጎማ ለማዳን ነው ልጆቹ ዘለው ወደ ዋናው አስፋልት የሚገቡት፡፡ በዚህን ጊዜ ሌሎች ጣታቸውን አፋቸው ዉስጥ በመክተት ደማቅ ፉጨት ያሰማሉ፡፡ ኳሷን የተሸከርካሪ ጎማ እንዳያፈነዳት ለአሽከርካሪው የፉጨት ቅድመ ማስጠንቀቂያ እየሰጡት ነው፡፡ ከቸርችል የፖስታ ቤት መብራት ለቋቸው ቁልቁል የሚንደረደሩት መኪኖች ፍጥነታቸው ያስፈራል፡፡ ታዳጊዎቹ ግን ከነፍሳቸው ይልቅ ለኳሷ ስለሚሳሱ ስለምንም ግድ ያላቸው አይመስልም፡፡

ኩባ አደባባይን ጥዬ ወደ “ክቡ” ባንክ መራመድ ጀመርኩ፡፡ ታዲዮስ (ሞሪንሆ) ከሩቅ ሲጮኽ ይሰማኛል! ‹‹ ‹‹አቺ…ጉቶ…ኸረ ተይ ሰው የሚልሽን ስሚ….ኳስ አትብይ አላልኩሽም…የሆንሽ ጅብ!” ያዲሳባን ክፍት ሜዳዎች ሁሉ በሊዝ ቸብችቦና ለዘመዶቹ አከፋፍሎ፣ የነጉቶን፣ የነሳንቾን፣ የነፋብሪን ሕልም የበላውን ትልቁን “ጅብ”  ምን ብሎ እንደሚጠራው እንጃ፡፡

አንድ ቀን ለእነዚህ ልጆች ሲባል #ያዲሳባልጆችይፈቱ #FreeAddischildren #የኮንዶሚኒየምልጆችይፈቱ #የሸገርሕጻናትይፈቱ #FreeShegerChildren!  እየተባለ ሰልፍ ይወጣ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ይካሄድ ይሆናል። ማን ያውቃል