Senga Tera condos site
Senga Tera condos site

ዋዜማ ሬዲዮ- እንዴት ናችሁ ግን? እኔ ደህና ነኝ፡፡ ድሮስ ወልዶ የሳመና 40/60 የተመዘገበ ሰው ምን ይሆናል ብላችሁ ነው!! አንድ ቀን መጦራቸው አይቀርም መቼም፡፡

በዛሬው ጦማሬ ከዲቪ ቀጥሎ በሀበሾች የመሻት ዝርዝር ቁልፍ ቦታ እየያዘ ስለመጣው ኮንዶሚንየም በአጭሩ አወጋለሁ፡፡

ለመኾኑ ኮንዶሚንየም ምንድነው? የማን ነው? ለማን ነው? መንፈስ ነው ግዑዝ? እጣ ነው ሥራ? የሚገኘውስ በችሮታ ነው በክፍያ?

እውነት ለመናገር በዚህ ዘመን ለሸገር ሕዝብ ኮንዶሚንየም ማለት ከአብረሃም ቤት ያነሰ ትርጉም የለውም፡፡

“ብጹአን መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ ብዙሀን ለኮንዶሚንየም ይሰለፋሉ፡፡” እንዲል ያዲሳባ ቻርተር፡፡

እድሜ ዘመን ሥጋን በድሎ፣ ላምባገነን ጎንበስ ቀና ብሎ፣ በጾም ጸሎት ተኮማትሮ፣ ለአስርተ ዓመት ጥሪት ቋጥሮ፣ መጠለያን አለማግኘት፣ ነፍስን በድሎ ዓለምን ከማትረፍ በምን ይለያል?

ኮንዶሚንየም ስላልደረሰው ብቻ ትዳር ያልሰመረለትን ከተማ ልማት ይቁጠረው፡፡ ኮንዶሚንየም ስለደረሳት ብቻ ትዳሯ የተቃና፣ ሕይወቷ የጣፈጠ፣ ወልዳ የከበደችን ቤቶች ልማት ይቁጠራት፡፡ በሸገር ኮንዶሚንየም ማለት ባሜሪካ የመኖርያ ፍቃድ ግሪንካርድ እንደማለት ነው፡፡

እኔ እንደውም አንዳንድ ጓደኞቼን ሳስባቸው የሕይወት ግባቸው 40/60 ቤት ዉስጥ ገብቶ በክብር መሞት ይመስለኛል፡፡

ምን የሚል ሰሞነኛ አባባል አለ መሰላችሁ….በምንሊክ ዘመን የደነቆረና ለ40/60 ሙሉ የከፈለ አንድ ናቸው፡፡ ያኛው ዛሬም ‹‹ጎበና ይሙት!›› ብሎ ይምላል…ይሄኛው ዛሬም ኮንዶምንየም ገብቼ፣ ቲቪ ገዝቼ፣ ሚስቴ አግብቼ Happy ever after ብሎ ይቃዣል፡፡ የሁለቱም ነፍስ ዛሬ ላይ የለም፡፡ በነገ ላይ የተንጠለጠለች ነፍስ ምንኛ የተኮነነች ናት!

አንድ ጥያቄ መልሱልኝማ፡፡

ከአፍሪካ ቅኝ ያልተገዛች፣ ኾኖም ግን የገዛ ሕዝቦቿን በቅኝ ገዢዎች ስልት ዘወትር እያታለለች የምታስተዳድር ብልጥ ከተማ ማን ትባላለች?

አዲሳባ ካላችሁ መልሱን አግኝታችሁታል፡፡ ኢህአዴግ መራሹ የልማት ሠራዊት ለ12 ዓመታት ሕዝብ አታሏል፡፡ በተዛባ መረጃ፣ በተንሸዋረረ ዜና፣ በመሰሪ ፕሮፓጋንዳ፣ በእዳ ነዋሪውን ሁሉ ፍዳ አብልቷል፡፡ ማን? ኢህአዴግ!!

ጣሊያን የመርካቶ ዲጂኖ ሕዝብ ሲያስቸግረው ቤት፣ መሬትና ሊሬ አድላለሁ እያለ አታሎ ለመግዛት ይሞክር ነበር፡፡ የቅኝ ገዢዎችን የፕሮፓጋንዳ ስልት የሚከተለው ኢህአዴግ መራሹ የድሪባ ሠራዊት የእምቧይ ካብ መረጃው የሚገነባው በሚከተለው ሁኔታ ነው፡፡

“በ2 ዓመት ዉስጥ ለሚጠናቀቀው የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤት የመሠረት ድንጋይ ተጣለ፡፡”

“በቅርብ ወራት ዉስጥ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤት የመሠረት ሥራው ተጠናቀቀ፡፡”

የ40/60 የሠንጋ ተራ አካባቢ የጋራ መኖርያ ቤት ግንባታ 20 በመቶ ተጠናቀቀ፡፡”

30 በመቶ፣40፣50፣ 70፣80፣ በመቶ ተጠናቀቀ… እየተባለ ይቆይና…99 ላይ ሲደረስ ቀጥ፡፡ ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም፡፡

ዓለም አቀፉ የሒሳብ ቀመር ከ99 በኋላ ተከታዩ ቁጥር 100 እንደሆነ ይነግረናል፡፡ በኢህአዴግ ቀመር ግን መቶ የለችም፡፡ መቶ በየዓምስት ዓመቱ የምክር ቤት መቀመጫ ለመውሰድ ሲሆን ብቻ ነው፡፡

ሁልጊዜም 99 ከመቶ ተጠናቀቀ ከተባለ የጋራ መኖርያ ቤት ፕሮጀክት በኋላ 99 ሰበቦች ይግተለተላሉ፡፡ ምሳሌ፡-

“የፋይናንስ እጥረትና የግንባታ ግብአቶች ዋጋ መናር ለቤቶች ልማት እድገት ማነቆ መሆኑ ተገለጸ፡፡

“የ40/60 ቤቶች ለባለ እድለኞች ለማስረከብ ጥቃቅን የማጠናቀቂያ ሥራዎች ብቻ ቀሩ፡፡”

“የተጠናቀቁ የጋራ መኖርያ ቤቶችን ከንግድ ባንክ ጋር ለመረካከብ እየተሠራ ነው ተባለ፡፡” 

“የ40/60 ቤቶች ርክክብ ሊፈጸም ቀን ተቆረጠ፡፡” 

“የ40/60 ቤቶች ርክክብ ተፈጸመ፡፡” 

“40/60 የጋራ መኖርያ ቤቶች የመመረቂያ ቀን ተቆረጠ፡፡” 

“የ40/60 ቤቶች መጋቢት 2 ሊመረቁ ነው፡፡”

“የከንቲባው በአዲስ አበባ በክራውን እና ሠንጋ ተራ የሚገኙ የጋራ መኖርያ ቤቶችን መረቁ…፡፡

(ረገሙ ቢባል ነው የሚሻል) ለምን ማለት ጥሩ ነው…

ተመረቀ ማለት እጣ ወጣ ማለት ነው እንዴ? አይደለም፡፡ እጣ ወጣ ማለት ግን ነዋሪዎች ቁልፍ ተረከቡ ማለት ነው እንዴ? አይደለም፡፡ ቁልፍ ተረከቡ ማለት ግን ቤታቸውን ተረከቡ ማለት ነው እንዴ? አይደለም፤ ቤታቸውን ተረከቡ ማለት ግን መኖር ጀመሩ ማለት ነው እንዴ? አይደለም…

በኢህአዴግ መዝገበ ቃላት ዉስጥ 100 ፐርሰንትን ላገኘ መቶ ብር እሸልማለሁ የምለው እኮ ወድጄ አይደለም፡፡ መቶ does not exist in the EPRDF Dictionary, Period. እንዳያሳኩ የተረገሙ ናቸው፡፡ Doomed to Fail! ይላቸዋል ፈረንጅ፡፡

ዉድ የጦማሬ ታዳሚዎች!

በዘመናዊት የኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ኢህአዴግ በሕዝብ ደካማ ጎን፣ በሕዝብ ድህነት የተዘባበተ የለም ባይ ነኝ፡፡ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፡፡ ያለማስረጃ አልናገርማ፡፡

ሰሞኑን ለምሳሌ በኢቢሲ አንዲት እናት አንጀት በሚበላ መልኩ ሲያነቡ ይታያሉ፡፡ ለዚያም መሐረብ ይዘው፡፡ ለዚያውም በተደጋጋሚ፡፡ በዜና መሐል ሁሉ ነው የሚታዩት፡፡ ሴትዮዋ ለምን እንደሚያነቡ ለማወቅ በቅርብ ጠብቁ ተባልን፡፡

ለካንስ እንደዚያ እንባ እያነቡ የሚታዩት እናት በኢህአዴግ ችሮታ ቤት በማግኘታቸው ሕይወታቸው ምንኛ መቀየሩን ለማስረዳት ነው፡፡ ካሜራ ደቅኖ የገዛ ዜጎቹን እንባ የሚያራጭ መንግሥት ከኢህአዴግ ሌላ ከየት ይገኛል? እንዲህ በሰው ድህነት ያለልክ መዘባበት በሰማይ ቤት አያስየጥቅም ይሆን? ለነገሩ ገዢዎቻችን ለኮንዶሚንየም ቤት እንጂ ለሰማይ ቤት ብዙም ግድም የላቸው!

ዉድ የአገሬ ሰዎች!

መንግሥቴ ቤት ሰጥቶ ሞርጌጁን በ12 ዓመታት ተሟሙተህ ክፈል ቢለኝ አከብረዋለሁ፡፡ እየኖርኩበት ነዋ!! ነግ ግን የኮንዶሚንየም ፎቶ በቲቪ እያሳየኝ ለ12 ዓመታት እንቁልልጭ እያለኝ፣ ሲደርሰኝ ደግሞ ካሜራ ደቅኖ በደስታ አልቅስ የሚለኝን መንግሥት እንዴት ላከብረው ይቻለኛል?

የእውነት!! ኢህአዴግ ግን ነፍሱ አይማርም፡፡ ይሄን ሚስኪን ድሀ ሕዝብ አግኝቶ ይዘባበትበታል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች  የተሠራ አንድ ጥናት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ 4445 ጊዜ ስለ ኮንዶሚንየም በመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ላይ ዜና ተሠርቷል ይላል፡፡ ከነዚህ ዜናዎች ዉስጥ የ357ቱ ይዘት የጋራ መኖርያ ቤቶቹ በቅርቡ ለባለዕድለኞች እንደሚተላለፉ የሚገልጽ ነው፡፡ ይህ ማለት መንግሥት ሕዝብን በትንሹ 357 ጊዜ አታሏል ማለት ነው፡፡

ሰሞኑን ደግሞ የመንግሥት አዲስ ነጠላ ፌዝ ወደ 40/60 ተመዝጋቢዎች ተሸጋግሯል፡፡ መንግሥት 40 ጊዜ ቤታችሁን ሠርቼ ላስረክባችሁ ተቃርቤያለሁ ሲል የሸገር ሕዝብ 60 ጊዜ እውነት መስሎት ተታሏል፡፡ በሌላ ቋንቋ 40% መንግሥት ያብላል፣ 60% ሕዝብ አውቆም ቢኾን ይሞኛል፡፡  ይህ ነው የአገሬ ነባራዊ እውነት፡፡

ዉድ የአገሬ ሰዎች!

“ከምጽአትና ከ40/60 ኮንዶሚንየም ማን ቀድሞ ይደርሳል?” ያልኩት ወድጄኮ አይደለም፡፡

ሰምታችኋል ግን? አንዳንድ ለ40/60 የጋራ መኖርያ ቤት መቶ እጅ የከፈሉ ምስኪን ሲቪል ሰርቫንቶች ሠንጋ ተራ እየሄዱ ፎቶ መነሳት መጀመራቸውን? አንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ሸሪኬ ከፎቶው ሥር እንዲህ የሚል ካፕሽን ጽፎ አነበብኩ፤

‹‹ግንባታው ቢጠናቀቅ ልኖርበት እችል የነበረው ቤት የወደፊት ገጽታ››፡፡

አንጀቴን ነው የበላው፡፡

እንዴት ታጋሽ ሕዝብ ላይ ይቀለዳል ግን!!? መንግሥት ግፍ አይፈራም ማለት ነው?!

አንዱ ደግሞ ሰሞኑን በሁዳዴ ጾም ቤተክርስቲያን ሄዶ እንዲህ ተሳለ አሉ፤ ለፈረሰኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ…

ከሁለት ዓመት በፊት የተመዘገቡኩት 40/60 ኮንዶሚንየም ቤት ከደረሰኝ ላንተ ወርቃማውን ጥላ…”

መልዓኩ ቅዱስ ገብርኤል አቋረጠው…”አንተ አህዛብ ሆይ! ስለምን ትፈታተነኛለህ…!”

ብሶት ወለድ አሪፍ ቀልድ አይደለች!?

ዉድ የጦማሬ አንባቢዎች!

መቼ ለታ የፈረንጆቹ ታይም መጽሔት ላይ የሰው ልጅ ከ40 ዓመት በኋላ ጨረቃ ላይ መኖር እንዲችል የአሜሪካ ሳይንቲስቶች እየተጉ መኾኑን ባነበብኩ ጊዜ እንዴት ባለ አንድ መኝታ ስቱዲዮ ዉስጥ ለመግባት 40 ዓመት ይፈጅብኛል? ስል ተብሰለሰልኩ፡፡

ይሄ የ40/60 ነገር እኮ፣ ወላ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ሳይቀር ነው እኮ ያስቆጣው፡፡  ካላመናችሁኝ የረቡዕ የካቲት 22 የፊት ገጽ ላይ የወጣውን አንብቡት፡፡

‹‹የቤት ልማቱ አሠራር ካልተፈተሸ ለተመዘገቡት ብቻ ቤት ለማድረስ 55 ዓመት ይፈጃል›› ሲል ተቃውሞውን በደማቁ ጽፎታል፡፡ ለያውም የአዲስ ዘመን በማይመስል ጀግንነት፡፡ ብራቮ አዲስ ዘመን፡፡ እንዲህ ነው እንጂ በባከነ ሰዓትም ቢኾን በሀቅ መንገድ መንገታገት፡፡

በነገራችሁ ላይ! አዲስ ዘመን ተሻሽሏል፡፡  ፈራ ተባ እያለም ቢኾን መንግሥትን ለመተቸት እየሞከረ ነው፡፡ የምሬን ነው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አዲስ ዘመን ጋዜጣን በስም ማጥፋት ወንጀል ፍርድ ቤት እንደገተረው ሰምታችኋል? ይልቅ እሱን ዜና ያነበብኩ ዕለት ምን ትዝ ቢለኝ ጥሩ ነው? ኢትዮጲካሊንክ፡፡

ኢትዮጲካሊንክ ቆንጆ የሬዲዮ ፕሮግራም ነው፡፡ የሥርዓቱ ለዘብተኛ ቲፎዞም እንደሆነ ይታማል፡፡ አውርቶ የማይጠግብ ፕሮግራም…፡፡ እናም በፋና ጣቢያ ለዓመታት ሲያወራ ሲያወራ ከዕለታት አንድ ቀን የማይነካ ባልቦላ ነካና ከሚሰራጭበት ሬዲዮ ፋና ተባረረ፡፡  አንድ አሽሙረኛ አድማጭ ከኳስ ሜዳ አካባቢ ወደ ጣቢያው ደወለና እንዲህ አለ አሉ፡-“አብዮትም ልጆቿን ትበላለች”

ኮንዶሚንየም ሳይደርሳችሁ በአብዮት ከመበላት ይሰውራችሁ!

ሙሴ ሀዘን ጨርቆስ

ለዋዜማ ሬዲዮ