የአገር ሰው ጦማር አይጧ፣ ምጣዱ እና የትግራይ ወጣት

[አሉላ ገብረመስቀል  ለዋዜማ ሬዲዮ]

በድምፅ ሸጋ ሆኖ ተሰናድቷል-እዚሁ አድምጡት

 

 

Mekele
Mekele

 

ሰኔ 20 2007 ዓ.ም፣

ዝግጅት:- ‹‹መሽኪት›› ሽልማት ኪነ-ጥበባት ትግራይ፣

ቦታው:- መቀሌ ሰማዕታት አዳራሽ

ይህ አዳራሽ ሳቅ አያውቅም፡፡ ፖለቲካ ሲቦካበት ነው የኖረው፡፡ ለትግራይ ጥበብና ጥበበኞች እውቅና በሚሰጠውና “የትግራይ ኦስካር” እየተባለ በሚሞካሸው በዚህ ልዩ ምሽት እንኳ የአዳራሹ መንፈስ ያው ነው። የእጩ አርቲስቶች ስም ሲጠራ ብቻ በፉጨት የታጀበ ደማቅ ጭብጨባ ይሰማል፡፡

በትግርኛ የባህል ሙዚቃ  ዘርፍ አሸናፊ… “ሶፊያ አጽበሃ” … ቤቱን የሚያርድ ጭብጨባ ተሰማ…

በሙዚቃ የዓመቱ ምርጥ የትግርኛ አልበም አሸናፊ…. “ሰለሞን ባይረ”…  ሌላ የጭብጨባ ድማሚት ፈነዳ።

ዝግጅቱ እንዲህ ቀጥሎ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን አንድ ያልተለመደ ነገር ታየ፡፡ ለዚህ ታላቅ የጥበብ ድግስ የተገኙት ዋናው ሰው፣ ጥቁሩና ኮስታራው የህወሓት ሊቀመንበር፣ የአውአሎም ታናሽ ወንድም፣ የመለስ ምትክ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር፣ አቶ አባይ ወልዱ ንግግር ሊያደርጉ ከመቀመጫቸው ተነሱ፡፡ ኾኖም የእርሳቸው ስም በመድረክ መሪው መጠራቱን ተከትሎ ታዳሚዎች ወንበራቸውን እያጠፉ አዳራሹን መልቀቅ ጀመሩ፡፡

“ነገሩ አስደንጋጭም አሳፋሪም ነበር” ይላል በዝግጅቱ የታደመ የሙዚቃ አቀናባሪ፡፡ ሁሉም ሰው የተመካከረ ነበር የሚመስለው፡፡ ርዕሰ መስተዳደሩ ገና መነጋገሪያውን ሳይጨብጡ የአዳራሹ ግማሽ ሕዝብ በሚያስደነግጥ ፍጥነት ተነስቶ ወጣ፡፡ በቃ የሆነው ይህ ነው፡፡

በፊተኛው ረድፍ የነበሩት የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ዶክተር ክንደያ ገብረሕይወት፣ የቀድሞው የሕወሓት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቴድሮስ ሃጎስ የሚያደርጉት ጠፍቷቸው አቀርቅረዋል፡፡ አርቲስት ኪሮስ ሀይለስላሴ እና ጥቂት የአቶ አባይ ወልዱ እልፍኝ አስከልካዮች የአዳራሽ በር እንዲዘጋና የቀረው ታዳሚ ተመልሶ እንዲቀመጥ ሙከራ አደረጉ፡፡

መድረክ መሪው ድምጽ ማጉያውን አንስቶ ተማጽንኦ አቀረበ፡፡ “በጃኻትኩም…በጃኻትኩም! (እባካችሁ!)” ፤ ጥቂት ሰዎች እንደነገሩ ተመልሰው ቁጭ አሉ፡፡ ያ ዕለት ኩርፊያ ያደመነው የትግራይ ወጣት በሰውየው አስተዳደር ላይ ያለውን መራር ተቃውሞ ያሳየበት አጋጣሚ ሆኖ ተመዘገበ፡፡

**********************************************************************

ለመሆኑ የትግራይ ወጣት በሕወሓት እና በሚዘውረው የኢሕአዴግ መንግሥት ላይ ጨርሶ ተስፋ ሊቆርጥና ሊያምጽ ይችላል? ይህ ጥያቄ ለብዙዎች ጥያቄ ኾኖ መቅረቡ በራሱ የሚያናድድ ሲሆን ጥቂቶች ግን “ይህን ጥያቄ ለመጠየቅ ትክክለኛ ጊዜ እየመጣ ነው” ብለው ያምናሉ፡፡ “የትግራይ ወጣት በህወሓት ላይ ባያምጽም ፊቱን አዙሯል” ይላሉ።

ሕወሓት በትግራይ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ አይደለም፡፡ የ30 ዓመታት የበረሀ መንፈስ ነው፤ የሩብ ምእተ ዓመት መንግሥት ነው፡፡ ለ54 ዓመታት እንደቤተሰብ የኖረ የጡት አባት ነው፡፡ በዚህ የህወሓት የረዥም ዓመታት ተጋድሎ ከተገኘው ሰላምና መረጋጋት ባሻገር ፓርቲው የሚወክለው ሕዝብ ከኢኮኖሚ እድገቱ ይነስም ይብዛ ተቋድሷል፡፡ የዚህ ሕዝብ የተጠቃሚነት ድርሻ “የበዛ ነው” የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ሌሎች በተቃራኒው ይከራከራሉ፡፡

ህወሓት መራሹ መንግሥት “የትግራይ ተወላጆችን በፖለቲካና በኢኮኖሚው ዘርፍ አንግሷቸዋል” የሚሉ ወገኖች በመንግሥት መዋቅር በየእርከኑ የተሰገሰጉ ኃላፊዎችና ምክትሎቻቸውን ይጠቅሳሉ፣ በሚኒስትር ደረጃ ቁልፍ የመከላከያና የደኅንነት ዘርፎች በትግራይ ተወላጆች እጅ መሆንን ያወሳሉ፤ እንደ ትእምእት (ኤፈርት) ያሉ የፓርቲው የንግድ ኢምፓየሮች እጅ መርዘም፣ በግለሰብ ደረጃ በብርሃን ፍጥነት ወደ ብልጽግና የተሸጋገሩ ከተሜ ትግራዊያን በቁጥር መብዛት እንዲሁም የክልሉ ተወላጆች በኮንስትራክሽን፣ በገቢና ወጪ ንግድ፣ በከተሞች የፎቅ ግንባታ ከዕለት ዕለት ጡንቻቸው መፈርጠሙን እንደማሳያ ይዘረዝራሉ፡፡

በተቃራኒው የቆሙ ተከራካሪዎች ደግሞ ከተሜው ተጋሩ (ትግራውያን) ሰፊውን  ድሃ የገጠር ሕዝብ ጋርደውታል ብለው ያምናሉ፡፡ ሕዝብ ስለ ትግራይ “የተሳሳተ ምስል እንዲኖረው ያደረጉት ጥቂት በከተማ የሚኖሩ የትግራይ ነጋዴዎችና ፖለቲከኞች ናቸው” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ እውነቱን ለመረዳት “ትልቁን ምስል” ማየት እንደሚገባ አበክረው ያሳስባሉ፡፡ እነርሱ “ትልቁ ምስል” የሚሉት ትግራይና ሰፊው የትግራይ ሕዝብ በየትኛውም መመዘኛ ወደኋላ ቀርተዋል የሚለውን ሙግታቸውን ነው፡፡ ይህንኑ እንዲያጠናክሩላቸው በማሰብም የክልሉን የልማት እድሎች ውስንነት ይዘረዝራሉ፤ መሰረታዊ የውሃ፣ የመብራት፣ የትምህርት፣ የሥራ እድል እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የነጻነት ውስንነቶችን ያነሳሉ፡፡ “እነዚህ ከየትኛውም ክልል በላይ በትግራይ የከፋ ደረጃ ላይ ናቸው፤ የክልሉ 10 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ እኮ ዛሬም ድረስ የምግብ ተረጂ ነው” ሲሉ መከራከሪያቸውን ያሳርጋሉ፡፡

እርግጥ ይህ “የአልተጠቀምንም” ትርክት በገዢው ፓርቲ አመራሮች ጭምር በስፋት እንዲራገብ ይፈለጋል፣ ብዙም ተሠርቶበታል፡፡ ከዓመት በፊት የህወሓት ትግል የተጀመረበት 40ኛ ዓመት ሲከበር ፓርቲው አርቲስቶችን በማስተባበርና ወደ ክልሉ በመውሰድ “የሚወራው ሐሰት ነው፣ የትግራይ ተወላጆች አልተጠቀሙም” የሚሉ ምስክርነቶችን እንዲሰጡ ማስደረጉ የሚታወስ ነው፡፡

******************************************************************************

እንካሰላንቲያ በትግሪኛ፣ የስታዲየም ፖለቲካ

“እንካ አዝግነኒ” የትግርኛ “እንካሰላንቲያ”  ነው፡፡

የመቀለ ወጣቶች እንዲህ ይላሉ፡፡

 

– እንካ አዝግነኒ

– ብምንታይ!

– ብለለ!

– እንታይ አለካ ብለለ?

– ደው ኢልኻ ቅረ ኸም ስታዲየም መቀለ”

 

በአማርኛ

– እንካሰላንቲያ

– በምንቲያ!

– በሱሪ

– ምናለ በሱሪ

– እንደስታዲየማችን አንቺም ቆመሽ ቅሪ  እንደማለት ነው።

ያልተጠናቀቀው የመቀሌ ስቴዲየም ለትግራይ ወጣቶች ፖለቲካዊ ትርጉም ይሰጣቸዋል፡፡ ከዛሬ 10 ዓመታት በፊት  ከየትኛውም ክልል ቀድሞ ግንባታው የተጀመረ ቢሆንም ዛሬም ድረስ አለመጠናቀቁ ያንገበግባቸዋል፡፡ ስታዲየም ለከተማዋ ብሎም ለክልሉ ነዋሪዎች የአመራሩ የቅሽምና ሀውልት ተደርጎ በአመዛኙ ይታሰባል፡፡ የስታዲየም ጥያቄ በክልሉ “ወደኋላ ቀርተናል፣ ረስታችሁናል” ለሚለው ኅብረ ራሮት ሁልጊዜም እንደ ዋና ማጠንጠኛ ሆኖ ይቀርባል፡፡ በተለይም ሀዋሳና ባሕርዳር ከተሞች እንደተፎካካሪ ከተማ መታየታቸውና የስቴዲየም ግንባታ በሁለቱም ከተሞች በአጭር ዓመታት ውስጥ ተጀምሮ መጠናቀቁ ለተራው የትግራይ ወጣት “በሌሎች ተበልጠናል” ስሜትን መፍጠሩ አልቀረም፡፡ በዚህ ቁጭት ላይ ደግሞ፣ “ለትግሉ ስንት ዋጋ ከፍለን…” የምትለዋ ስሜት ስትጨመር የመሸታ ቤት ጨዋታን ወደ ፍልሚያ የሚያንደረድር መካረር ሊፈጠር ይችላል።

የስቴዲየም ጉዳይ ተልካሻ የቅንጦት ጥያቄ እንደሆነ የሚያስቡ ነዋሪዎች በአንጻሩ ክልሉ ዛሬም ድረስ ያልተመለሰ ከፍተኛ የውኃ አቅርቦት ችግር እና ሌሎች በፍትህ ዙርያ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይበልጥ ያንገበግቧቸዋል፡፡ የውሃና የፍትሕ ጥያቄዎች ባለፉት 10 ዓመታት ዉስጥ በየስብሰባው ሁሉ በከፍተኛ ብስጭትና ቁጣ ታጅበው በሕዝብ የሚነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ቢሆኑም አንድም ጊዜ ሕዝቡን ከፍ ላለ ተቃውሞ  ጋብዘውት አያውቁም፡፡ አለዚያም አፈናው መተንፈሻ አሳጥቶት ውስጥ ለውስጥ እየተንተከተከ ይሆናል።

ቄስ ገብረገርግስ – አይጧና ምጣዱ

ከህወሓት የመጨረሻው ጉባኤ ወዲህ እንደ አቡነ ጴጥሮስ መታየት የጀመሩ አንድ ሰው አሉ፣  ቄስ ገብረገርግስ ገብረማርያም ይባላሉ፡፡ በ1970 ዓ.ም የወየኑት እኚህ ቄስ የሕዝቡን እሮሮ በህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ያለ ፍርሃት አስተጋብተዋል፡፡ በቅርቡ “ውራይና” ከተባለና በክልሉ ከሚሰራጨው ብቸኛው የትግርኛ የግል መጽሔት ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ መነጋገሪያነቱ እስካሁንም አልበረደም፡፡ “ልጆቻችንን ገብረን ያመጣነው ስርዓት መልሶ ደርግ ሆነብን፤ እንከን የለሽ ምርጫ የምትሉት ውሸት ነው፤ አማራጭ ስለሌለን ነው የመረጥናችሁ፤ ፍትህን ዶሮ ሽጠን እየገዛን ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ከመማረሩ የተነሳ እንደገና መወየን ነው የቀረው” የሚሉ ኮስታራ ኀይለ ቃሎችን ለታሪክ አስመዝግበዋል።

ቄስ ገብረገርግስ “ጌታቸው አሰፋ በጉባኤው ላይ ሕዝብ ቢያምጽ ምን እናደርጋለን? ብሎ የጠየቀው ሊታሰብበት ይገባል፣ በዚሁ ከቀጠላችሁ ሕዝብ ማመፁ አይቀርም” ሲሉ የደኅንነቱን ሹም ስጋት አስተጋብተዋል፡፡ ቄስ ገብረገርግስ የትግራይ ሕዝብ አሁን ለህወሓት ያለውን ስሜት በዚህ መንገድ ይገልፁታል፤ “ምእንቲ እታ መጎጎ ትሕለፍ እታ እንጭዋ”  ፤ “ምጣዱ ከሚሰበር አይጥዋ ትለፍ”  እንደማለት ነው። ከቄሱ አንጋግር አይጧ ህወሓት እንደሆነች መረዳት ይቻላል፤ ምጣዱ ምንድን ነው?

በህወሓት ካድሬዎች እንደ ከሀዲና የእናት ጡት ነካሽ ተደርገው የሚሳሉት የአረና ፓርቲ አመራሮች ይህን የሕዝብ ብሶት ወደ ምርጫ ድምጽ ለመለወጥ የአቅም ማነስ ይታይባቸዋል፡፡ ከየትኛውም አገር ውስጥ ከሚንቀሳቀስ ፓርቲ በከፋ በገዢው ፓርቲ ወከባ ይፈፀምባቸዋል፡፡ ክልሉን ካስተዳደሩ ሰዎች የተሻለ ተወዳጅና ከሙስና የፀዱ ሆነው የሚታሰቡት አቶ ገብሩ አስራት እንኳ እስከዛሬ በተቃዋሚነት ማግኘት የቻሉት ድምጽ ስድስት ሺህ ብቻ ነው፡፡

የክልሉን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉ እንደ አብረሃ እንቋር ያሉ ዜጎች በአረና ወይም ወደፊት በሚወለድ ሌላ ብሔር ተኮር ፓርቲ ላይ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ “አረና በ2002 ምርጫ በመላው ትግራይ ከመቶ ሃያ ሺህ በላይ ድምጽ አግኝቷል፡፡ ገብሩ ባለፈው የምክር ቤት ምርጫ በመቀሌ በተለይም ላጬና አይደር ጣቢያዎች ላይ ሕወሓትን አሸንፏል፡፡ የክልሉን የአፈና ደረጃ ለሚያውቅ ይህ ቁጥር ተስፋ ብቻም ሳይሆን ከተስፋም በላይ ነው” ይላል አብረሃ፡፡

እርሱ እንደሚለው በትግራይ የሕወሓት ሕልውና የሚያከትመው ከራሱ ከሕዝቡ በወጡ የትግራይ ልጆች በሚቋቋም የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ብቻ የሚያቀነቅን ኅብረብሔራዊ ፓርቲ በትግራይ ቦታ የለውም ብሎ በጽኑ ያምናል፡፡ “ትግራይ ውስጥ ላለፉት 10 ዓመታት ቅንጅትን የመሰሉ ፓርቲዎች ሕዝቡን ወደ ደርግ ዘመን እንደሚመልሱት የሚያሳምን ፕሮፓጋንዳ በገዢው ፓርቲ ተነዝቷል፡፡ ይህን መቀልበስ ከባድ ነው፡፡ ለዘብተኛ የትግራይ ወጣቶች እንኳ ‘ቅንጅት’ የሚል ስም ስትጠራባቸው ይበረግጋሉ፡፡ ይህ መሰበር የሚችለው ደግሞ ከአብራኩ የወጡ ተቃዋሚዎችን በመፍጠር ብቻ ነው፡፡” ይላል፡፡

ትግራይ ውስጥ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊኖር ይችላል?

በትግራይ በሚገኙ ሦስት ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ከ50 ሺህ ይልቃል፡፡ የተማሪዎቻቸው ሕብረ ብሔራዊ ስብጥር ከተቀሩት የአገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ጋራ ተመሳሳይ ቢሆንም አንድም የአመጽ ድምጽ አሰምተው አያውቁም፡፡ “ይህ በራሱ የሚናገረው ታሪክ አለ” ይላሉ ክልሉን በቅርብ የሚያውቁ እንደ አብረሃ ያሉ ወጣቶች፡፡ ለመጀመርያና ለመጨረሻ ጊዜ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ጠንከር ያለ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው በ1996 ዓ.ም ሲሆን መነሻውም የካፌ ምግብ መጓደልና ሙስና ነበር፡፡ ከዚያ ዘመን በኋላ ኮሽ ያለ ነገር የለም፡፡ በ1993 በመላው የአገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች አመጽ ሲቀጣጠል በትግራይ ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሂደት ቀጥሎ ነበር፡፡ የክልሉ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ በትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ክሌሎች ክልሎች የሚመጡ ተማሪዎች ክልሉን “ከተቃውሞ የጸዳ” አድርገው ሳይቀበሉት አልቀሩም።

ከዩኒቨርስቲ ውጭም ቢሆን በክልሉ አደባባይ የሚያስወጣ የሕዝብ ተቃውሞ ተሰምቶ የሚያውቅበት አጋጣሚ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ከዓመታት በፊት የቀድሞ የሕወሓት አካል ጉዳተኛ ታጋዮች “ተዘንግተናል” በሚል በጋራ መጠለያቸው መጠነኛ አመጽ ቀስቅሰው ነበር፣ በአባዲ ዘሙ አወያይነት ቶሎ መዳፈን ችሏል።  ከዚያ በኋላ ‘ሠራዊት’ በተባለ ቦታ  የጨረቃ ቤት የሠሩ ግለሰቦች ቤታቸውን በግብረ ኃይል ለማፍረስ ሲሞከር በተነሳ ግርግር መጠነኛ ተቃውሞ ተከስቶ አድማ በታኝ ኃይል ተሰማርቶ ያውቃል፡፡ ባለፉት 24 ዓመታት ትግራይ ላይ ከነዚህ ውጭ ሊጠቀስ የሚችል ሕዝባዊ ተቃውሞ ይቅርና ኮሽታ እንኳን አልተሰማም፡፡

አብረሃ እንደሚለው “ትግራይ ውስጥ እያንዳንዱ ቤተሰብ የሩቅና የቅርብ ዘመዱን በጦርነት ከማጣቱ ጋር ተያይዞ ከልጅነት እስከ እውቀት በሚሰማቸው የበረሃ ተረቶች ለፓርቲው የየኔነት ስሜት አዳብሮ እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ በክልሉ በሚቀርቡ የቴሌቭዥን ድራማዎች፣ ሙዚቃዎች፣ ዲስኩሮች፣ ውይይቶች፣ ስፖርት ፌስቲቫሎች፣ የበዓል ፕሮግራሞች ላይ ሳይቀር ስለተሰው ሰማዕታት ይሰበካል፡፡ የመዋዕለ ሕጻናት መዝሙሮች  በአመዛኙ ሰማዕታቱን የሚዘክሩ ናቸው፡፡ ድል ያለ ሠርግ ላይ እንኳ ከሚዜሙ ዜማዎች ሲሶው ስለተሰውት ወያኔዎች ነው፡፡ ይህም ከጎረቤት ኤርትራ የሚዲያ ባሕል ጋር ተመሳሳይ ያደርገዋል፡፡” በዚህ ሁኔታ የተቃኘ ማኅበረሰብ ለፓርቲው ከልክ ያለፈ ታማኝነትን ቢያሳይ ምኑ ይገርማል?

አይጧንና ምጣዱ ምንና ምን ናቸው?

በትግራይ የሕዝብ አፈና፣ የመናገር ነጻነት እጦትና የዲሞክሪያሳዊ መብቶች መሸራረፍ ጥልቀቱ የሌሎችን ክልል የሚያስንቅ ሆኖ ሳለ “መሠረታዊ የፖለቲካ ጥያቄን የሚያነሳ ብዙ የትግራይ ወጣት አታገኝም” ይላል በክልሉ በሚንቀሳቀስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ዉስጥ ከ10 ዓመት በላይ ያገለገለ  ባለሙያ፡፡ የመጻፍ መብት፣ ሐሳብን የመግለጽና የመሰብሰብ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በትግራይ እንደ ወንጀል መታየት ከጀመረ ዘመን አልፎታል፡፡ እነዚህን መብቶች ባለፉት ረዥም አመታት ውስጥ የጠየቀ ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ከዚያ ይልቅ ትንንሽ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ምሬቶችን ትሰማለህ፡፡ ያ ደግሞ በአጭር ዓመታት ውስጥ ሁሉን አቀፍ ወደሆነ ተቃውሞ ይሻገራል ብዬ አላስብም” ሲል ይከራከራል፡፡

አንድ የአክሱም ዩኒቨርስቲ ባልደረባ “የትግራይ ወጣት በመጀመርያ ህወሓት የፖለቲካ ፓርቲ እንጂ ሃይማኖት እንዳልሆነ የሚነግረው ይፈልጋል” ብሎኛል፡፡ “ለምን መሰለህ? ብዙ ጓደኞቼ ህወሓትን ከተቹ በኋላ የመፀፀት ነገር አይባቸዋለሁ፡፡ ልክ አማኝ ሃይማኖቱን ወይም ፈጣሪውን ጨክኖ ሲተች የሚሰማው ዓይነት ስሜት…፡፡ ”

“አንድን ታዳጊ ለረጅም ጊዜ ያለማቋረጥ የ ‹‹ቫዮለንስ›› ፊልሞችን ብታሳየው ባህሪውን ሙሉ በሙሉ ትለውጠዋለህ፡፡ ይህ ተረት ሳይሆን በጥናት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡” ይላል የሚዲያ አማራጭ ማጣት አሁን መሬት ላይ ላለው እውነት ምክንያት መሆኑን ሲያስረዳ፡፡ “በርግጥ ሕወሓትን ጨክኖ መተቸት ከማኅበራዊ ሚዲያዎች መበራከት ጋር ተያይዞ አሁን አሁን እየተለመደ ይመስላል፡፡ የክልሉን አንኳር ችግሮች ፈልፍለው ለሕዝቡ በራሱ ቋንቋ የሚያደርሱ ወጣት የማኅበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች እየተፈጠሩ መሆኑ ተስፋ ነው፡፡”

ይኸው የዩኒቨርስቲ ባለሙያ እንደሚለው በትግራይ ሕወሓት ከፖርቲም በላይ የመመለክ ቁመናን እንዲያገኝ ያስቻለው ክልሉን ካለፈው አስከፊ ስርዓት አውጥቶ ፍፁም “ሰላማዊ” ቀጣና በማድረጉ ብቻ አይደለም፡፡ በቤተሰብ ደረጃ ለፓርቲው ሕይወቱን የሰዋ የቅርብም ይሁን የሩቅ ዘመድ አለመታጣቱ ሌላ ፓርቲን መናፈቅ ከትዳር ዉጭ እንደመወስለት ያህል የጥፋተኝነት ስሜትን ማሳደር መቻሉ ነው፡፡

“የትግራይ ወጣት በህወሓት ተከፍቷል፣ አዝኗል፣ ገዢዎቹ የሰማዕታቱን ትግል መና እንዳስቀሩበት በጽኑ አምኗል፤ ያም ኾኖ ግን እመነኝ ተስፋ አልቆረጠም” ይላል አብረሃ፡፡ “ታዲያ ቅሬታውን ወደ ሕዝባዊ ተቃውሞ ወይም አመጽ ሊያደርሰው ይችላል?” ተብሎ ሲጠየቅ “ለማመጽ እኮ ተስፋ መቁረጥ ያስፈልጋል፡፡” ሲል አጭር መልስ ይሰጣል፡፡

ቄሱ እንዳሉት አይጧ ለምጣዱ ሲባል እንዳሻት እንድትላወስ ተፈቅዶላታል። በመጪው ጊዜ አይጧ አመሏን ታስተካክላለች ወይስ ምጣዱ እንዳይጎዳ አድርጎ አይጧን የመቅጫ መንገድ ይገኛል? አይጧና ምጣዱ ምንና ምን ናቸው?

[አሉላ ገብረመስቀል ለዋዜማ ሬዲዮ]