Juve 4ዋዜማ ራዲዮ- ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውና የጁቬንቱስ ክለብ በመባል የሚታወቀው ማኅበር ለአፍቃሪዎቹ የይድረሱልኝ ጩኸት እያሰማ ነው፡፡ ካለፉት ሳምታት ጀምሮም Save Juventus የሚል የፊርማ ዘመቻ የጀመረ ሲኾን ለዘመናት ለ60 ዓመታት ከተገለገሉበት አባላቱና ከደጋፊዎቹ በሺዎች የሚቆጠር የድጋፍ ፊርማ እየጎረፈለት ይገኛል፡፡

የማዕከሉ የመዘጋት ዜና የመጣው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር በይዞታው ላይ የይገባኛል ጥያቄ በማንሳቱና ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰዱ ነው ተብሏል፡፡ ፍርድ ቤትም ባልተጠበቀ መልኩ ማኅበሩ ለ6 አስርተ ዓመታት ይዞት የቆየውን ይዞታ ለኪራይ ቤቶች አስተዳደር እንዲያስረክብ በይኖበታል፡፡

በኢትዮጵያ ለሚኖሩ የጣሊያን ኮሚኒቲ አባላት በዋናነት እንዲሁም ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን ጭምር መልካም የጊዜ ማሳለፊያ፣ መዝናኛና ተመራጭ የስፖርት ማዘውተሪያ ኾኖ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀው ይህ ማዕከል የሚገኘው ከመስቀል አደባባይ፣ ኤግዚቢሽን ማዕከል ጀርባ ከሴንጆሴፍ ትምህርት ቤት ጎን ነው፡፡ ሰፋፊ የመኪና ማቆምያና ሜዳዎች ያሉት ይህ ቦታ በ15ሺ ካሬ ሜትር የተንጣለለ ግቢ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ሲሰጥ ኖሯል፡፡

ለሕጻናትና ወጣቶች የስፖርትና ሥነ ጥበብ ማጎልበቻ ማዕከል፣ ለአዋቂዎች የሬስቶራንት አገልግሎት፣ ለዲፕሎማቲክ ኮሚኒቲው የባህል ልዉዉጥ መድረክ በማሰናዳት፣ የሥዕልና ፊልም አውደ ርዕይ ማሳያ በማዘጋጀት፣ መዝኛና የስፖርት ሜዳ አገልግሎት በመስጠትም በይበልጥ ይታወቃል፡፡ 

ማኅበር ለትርፍ ያልተቋቋመ ሲኾን ኢትዮጵያ ዉስጥ የተመሠረተውም እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1957 ዓ.ም ነበር፡፡ በዚያን ዘመን የክለቡ መሥራቾች በኢትዮጵያ የጣሊያን ኮሚኒቲ አባላት ሲኾኑ በጊዜው ከፊታውራሪ ተሾመ ብሩ ቦታውን ለ25 ዓመታት በኪራይ ወስደው ሥራ እንደጀመሩ ይነገራል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላም አሁን በግቢው ዉስጥ የሚገኘውን ሕንጻ ሙሉ ወጪ በመሸፈን አስገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ማዕከሉ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሚኖሩ የጣሊያን ኮሚኒቲ አባላትና ለአገሬው ሁሉን አቀፍ የመዝናኛ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ለትርፍ ያልተቋቋመና ከአባላቱ በሚመረጡ የቦርድ አባላት ሲመራ የቆየ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም ነበር፡፡

ምንም እንኳ ማኅበሩ ከደጃዝማች ተሾመ ብሩ ቦታውን ለ25 ዓመታት በኪራይ የወሰደ ቢኾንም በደርግ ታውጆ የነበረው የከተማ ቦታ የሚመለከተው አዋጅ የክለቡን ይዞታ ሳይነጥቀው ቆይቷል፡፡ ይልቁንም በአዋጅ 47/1967፣ አንቀጽ 6 መሠረትም ቦታው ለማኅበሩ በመጽናቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት የጁቬንቱስ ክለቡ አስተዳደር ግብር ሲከፍልበት ቆይቷል፡፡ ኾኖም በነዚህ 60 ዓመታት ዉስጥ የይዞታ ማረጋገጫ ሕጋዊ ካርታ እንዴት ሳያገኝ ሊቆይ እንደቻለ ግልጽ አይደለም፡፡

Juve 3እ.አ.አ በ1998 የደጃዝማች ተሾመ ብሩ ሕጋዊ ወራሾች በይዞታው ላይ የይገባናል ጥያቄ አንስተው ለ6 ተከታታይ ዓመታት የተከራከሩ ሲኾን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እ.አ.አ በ2004 ዓ.ም ባሳለፈው ዉሳኔ ቦታው ተገቢነቱ ለጁቬንቱስ ክለብ ነው በሚል ይዞታው ለማኅበሩ እንዳጸናለት የክለቡ የቦርድ አባላት ያብራራሉ፡፡ ያም ኾኖ ማኅበሩ መደበኛ አገልግሎቱን ይቀጥል እንጂ የይዞታ ካርታ ወዲያዉኑ በእጁ ሊያስገባ አልቻለም፡፡

ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ባልተጠበቀ ሁኔታ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ይዞታው ለኔ ይገባኛል ሲል አቤቱታ ያነሳው፡፡ ፍርድ ቤትም ይዞታው ለኪራይ ቤቶች አስተዳደር ይገባዋል በሚል “ያልተጠበቀና አስደንጋጭ” የተባለ ዉሳኔ እንደወሰነ በማኅበሩ ቅጥር ግቢ ለክለቡ ወዳጆች በተሰራጨ በራሪ ወረቀት ተብራርቷል፡፡

ኪራይ ቤቶች በበኩሉ ቦታውን ለመንግሥት ተሿሚዎች የሚኾኑ በርካታ አፓርትመንቶችን ለመገንባት እንደሚፈልገው ታውቋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ለሚሾማቸው መካከለኛና ከፍተኛ ካድሬዎች የሚኾኑ መኖርያ ቤቶች እጥረት ፈተና እንደሆነበት የኪራይ ቤቶች አስተዳደር በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

ጁቬንቱስ ክለብ ለ60 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ በዚህ ሁኔታ ይዞታውን መነጠቁ ያሳዘናቸው የማኅበሩ የቦርድ አባላት የመጨረሻ ያሉትን የፊርማ ማሰባሰብ ሂደት ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች የጀመሩ ሲኾን የማዕከሉ አባላትና ተጠቃሚዎችም በፍርድ ቤት ዉሳኔ ላይ የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

ጁቬንቱስ ክለብ ዘርፈ ብዙ ስፖርታዊና ኪነጥበባዊ አገልግሎቶችን ለረዥም ዓመታት የሰጠ እውቅ የባሕል ማዕከል ሲኾን በዉጭ ዜጎችና በአገር ዉስጥ ባለሐብቶች በይበልጥ የሚዘወተር የጣሊያን ባህላዊ ሬስቶራንት በዉስጥ ይዟል፡፡ በሳምንት አንድ ጊዜ የሚካሄድ ያገለገሉ ቁሳቁሶች ለገበያ የሚቀርቡበት ቅዳሜ ገበያ (garage sale)፣ የፉትሳል ሜዳ፣ የመረብ፣ የቅርጫትና የሜዳ ቴኒስ ማዘውተሪያዎች፣ የፊልም ፌስቲቫል ማሳያዎች፣ የሙዚቃ ኮንሰርት ማካሄጃ፣ የማርሻል አርት ስፖርት አዳራሽ፣ የሥዕል አውድ ርዕይ እልፍኝ በዉስጡ ይዟል፡፡

አዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚገነቡ ፎቆችና የልማት ጥያቄዎች የተነሳ ይህን ማዕከል የመሰሉ የባሕልና ሥነ ጥበብ ማካሄጃ ሕዝባዊ ቦታዎችን እያጣች ትገኛለች፡፡ ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በልማት ስም የእግር ኳስ ሜዳዎችና የሕዝብ አደባባዮች እየተለቀሙ በመታጠራቸውና ለግንባታ በመወሰዳቸው ነዋሪዎች በመዝናኛ ቦታ እጦት ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ አሁን ላይ አሉ የሚባሉ መሰል ቦታዎች የሚገኙትም በኤምባሲ ግቢዎችና ኤምባሲዎች በሚያስተዳድሯቸው ማዕከሎች ብቻ ነው፡፡

ጁቬንቱስ ክለብ፣ ግሪክ ክለብ፣ አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ፣ ጎተ ኢንስቲትዩት፣ የራሺያ የባሕል ማዕከል፣ በአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ እንዲያብብ፣ ማኅበረሰባዊ አገልግሎት እንዲዳብር፣ የወጣቶችን ተሰጥኦ በመኮትኮት ከሚተጉ ተቋማት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በከተማዋ ከነዚህ ቦታዎች ዉጭ ተመሳሳይ ሕዝባዊና ማኅበረሰባዊ አገልግሎት የሚሰጡ ሥፍራዎች እየተመናመኑ መጥተዋል፡፡ 

የዋዜማ ዘጋቢ ያጋገረቻቸው አንድ የከተማ ንድፍና አስተዳደር ባለሞያ የጁቬንቱስ ክለብ መዘጋት አዲስ አበባን የዲፕሎማቶች መናኸሪያ ለማድረግ በመሪ ፕላን ከተያዘው ትልም የሚቃረን ድርጊት ኾኖ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡