maize

  • የግንባታ ብረት ዋጋ ላይ የታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መንግስት የሚመካበትን የግንባታ ዘርፍ ሊያስተጓጉለው እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል
  • የቤት ቆጣቢዎች  ተጨማሪ ገንዘብ ሊጠየቁ  ይችላሉ

(ዋዜማ ራዲዮ) ሀገሪቱ ከአንድ አመት በፊት የገጠማት ህዝባዊ አመፅና የመንግስት ግብታዊ የሀብት አስተዳደር ችግሮች ተደምረው አሁን ሀገሪቱ የከፋ አጣብቂኝ ውስጥ ከቷታል።

የበቆሎ ዋጋ በኩንታል አንድ ሺህ ብር ደርሷል። የግንባታ ብረት ዋጋ ላይ የታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መንግስት የሚመካበትን የግንባታ ዘርፍ ሊያስተጓጉለው እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል።

በኢትዮጵያ የእህል ገበያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአንድ ኩንታል ወይም የመቶ ኪሎ ግራም በቆሎ ዋጋ 1000 ብር (አንድ ሽህ ብር) ደርሷል።

የበቆሎ ዋጋ በዚህ ደረጃ የናረው በምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎች የተፈጠረውን ድርቅ ተከትሎ በተለይም በቆሎን በዋነኛነት የሚመገቡ ከጎረቤት ሀገራት የግዥ ፍላጎት በማሳየታቸውና በቆሎ ለኢትዬጵያ ህዝብ ቀዳሚ ቀለቡ ባለመሆኑ ምርቱን በግዥ ከኢትዬጵያ ማግኘት እንዲችሉ ለመንግስት ባቀረቡት ጥያቄና የኢትዮጵያ መንግስት ባሳየው እሽታ ምክንያት መሆኑን የዋዜማ ምንጮች ይገልፃሉ።።

 ኬንያን የመሳሰሉት በቆሎ ተመጋቢ ሀገራት በገጠማቸው ድርቅ ምክንያት በቆሎን ከኢትዮጵያ አምራቾች ለመግዛት በጠየቁት መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት በቅባት እህል ላኪነት የሚታወቁት ሚሊዬነሩ በላይነህ ክንዴ  1000 ቶን በቆሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥታ ትዕዛዝ ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ፍቃድ በመሰጠቱ የሀገር ውስጥ የበቆሎ ገበያው ተሰምቶም ሆነ ተሽጦ በማያውቅ ደረጃ መናሩ እየተገለፀ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት በብቸኝነት ለጎረቤት ሀገራት በቆሎ እንዲያቀርቡ ለአቶ በላይነህ ክንዴ ፍቃድ መስጠቱ በሌሎቹ አስመጪና ላኪ ነጋዴዎች ዘንድ ግልፅ ተቃውሞ እየቀረበበት ይገኛል ምክንያቱም አቶ በላይነህ ክንዴ ለውጭ ገበያው የሚያቀርቡትን በቆሎ ከእርሻቸው በማምረት የሚያገኙ ሳይሆን ከገበሬው ላይ በመልቀም በመሆኑ ከሌሎች በተለዬ ሁኔታ  መፈቀዱ አግባብ ካለመሆኑም በላይ ብቸኛው አቅራቢ በመሆናቸው የሀገር ውስጥ  ገበያውን በፈለጉት መጠን በመጠቀም እንዳይረጋጋ ምክንያት ሆነዋል ሲሉም ምንጮች ገልፀዋል

የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ለኢትዬጵያ የውጭ ምንዛሪ በማስገባት በቀዳሚነት ስማቸው የሚጠራው አቶ በላይነህ ክንዴ ወደሀብት ማማ ብቅ ያሉት በቅርብ አመታት ሲሆን ግለሰቡን በቅርቡ የታተመው የፎርብስ መፅሔት ኢትዬጵያዊያን ሚሊዬነሮች ካላቸው ዝርዝር ውስጥ አቶ በላይነህን በቁጥር አንድ ላይ ያስቀመጠ ሲሆን ይህን መረጃ መሰረት በማድረግ የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን መዘገባቸውን ተከትሎ አቶ በላይነህ በፎርብስ ዘገባ እና ደረጃ ደስተኛ አለመሆናቸውንና እኔ በብቸኝነት መጠቀሴ አግባብ አይደለም በማለት የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ማስተባበያ እንዲሰሩላቸው መጠየቃቸው ተሰምቷል።

ከቅርብ አመታት ወዲህ የውጭ ምንዛሪን ለኢትዬጵያ መንግስት በማስገባት ስማቸው በቀዳሚነት የሚጠራው የቅባት እህሎች ነጋዴው አቶ በላይነህ ክንዴ የዛሬ ሁለት አመት አካባቢ መንግስት የኢትዬጵያ ሆቴልን እና ዙሪያውን ለመሽጥ ያወጣውን ጨረታ በማሽነፍ መግዛታቸው ይታወቃል።

በኢትዬጵያ የበቆሎ ዋጋ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ገበያው መናሩ የሀገር ውስጥ የእህል ምርት ዋጋና ፍላጎት ላይ ከባድ ጫና በመፍጠር አሁን ያለውን 8 ሚሊዬን በላይ የሚደርሰውን የምግብ እርዳታ ፈላጊ ቁጥርን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል በበርካቶች ዘንድ ግምት ተወስዷል። በአሁኑ ወቅት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢትዬጵያዊያን ለእለት ጉርሳቸው የሚሆነውን በቆሎ በችርቻሮ የሚገዙት 1, 200 ብር ሂሳብ መሆኑ እጅግ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል። 

 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለባንኮችና ለሌሎች ለሚመለከታቸው ተቋማት ጭምር  በቀጥታ ትዕዛዝ በመስጠት አቶ በላይነህ ክንዴ ለጎረቤት ሀገራቱ በብቸኝነት 1000 ቶን በቆሎ እንዲያቀርቡ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ድጋፍ እንዲሰጡ መመሪያ ከመሰጠቱም በላይ የግብርና ህብረት ስራ ማህበራት በቆሎውን ከገበሬወች በመሰብሰብ ለአቶ በላይነህ ወኪሎች እንዲያስተላልፉ መመሪያ መተላለፉንም ምንጮች ገልፀዋል

በተያያዘ ዜና በቅርብ ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአርማታ ብረት ዋጋ እየናረ መምጣቱ የግንባታ ኢንደስትሪውን ወደኋላ እንዳይጎትት ስጋት ፈጥሯል፡፡ በኪሎ 16 ብር ጀምሮ ይሸጥ የነበረ ብረት ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደ 28 ብር እና ከዚያም በላይ እያደገ መጥቷል፡፡

በአዲስ አበባ አንዳንድ የግል ባለሐብቶች የብረት ዋጋው ረገብ እስከሚል በማለት አነስተኛ የግንባታ ፕሮጀክቶቻቸውን ለጊዜው ለማቆም መገደዳቸውን እየተናገሩ ነው፡፡

የብረት ዋጋ ወደነበረበት ካልተመለሰ ምናልባት ከዓመታት በፊት በሲሚንቶ ዋጋ ንረት ተፈጥሮ የነበረው የግንባታ ኢንደስትሪ መቀዛቀዝ ዳግም ሊከሰት እንደሚችል የሚተነብዩም አልጠፉም፡፡

የአርማታ ብረት ንረቱ በተለይም 97 . ጀምሮ እስከዛሬም ባልተገባደደው የቁጠባ ቤቶች ልማት ላይ ጥላውን እንዳያጠላበት ስጋት አለ፡፡ መንግሥት ከያዝነው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ከፍተኛ የበጀት ቀውስ ገጥሞት የቤት ግንባታዎችን ለማስቀጠል የተፈተነበት ዓመት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በርካታ ተቋራጮች ገንዘብ በጊዜው ሳይለቀቅላቸው በመቅረቱ የወሰዷቸውን የቁጠባ ቤት ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ ተቸግረውም ነበር፡፡ የብረት ዋጋ ንረቱ በዚሁ ከቀጠለ መንግሥት ከጠበቀው በላይ ወጪ እንዲያወጣ ስለሚገደድ አሁን እየተገነቡ ካሉ ቤቶች ከፊሎቹ ለጊዜውም ቢሆን ባሉበት እንዲቆሙ ተደርጎ ወደሚቀጥለው ዓመት ሊሸጋገሩ ይችላሉ እየተባለ ነው፡፡

በኢፌድሪ የከተማ ልማት ውስጥ የሚሰሩ አንድ ባለሞያ የብረት ዋጋ በዚህ መልኩ እየናረ መሄድ ወደፊት ቆጣቢዎች ከተዋዋሉትና በየወሩ መቆጠብ ከሚችሉት ዋጋ ከፍ ያለ ክፍያ እንዲጠየቁ ምክንያት ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡ እንደርሳቸው አባባል መንግሥት ከዚህ በኋላ እንዲህ ዓይነት ወጪዎችን ላለመደጎም ወስኗል፡፡ ንግድ ባንክ በቅርቡ ዕጣ ባወጣባቸው የሰንጋ ተራና የክራውን 40/60 ቤቶች በካሬ ሜትር 1ሺህ 718 ብር ጭማሪ ከቆጣቢዎች ለመጠየቅ የተገደደው የግንባታ ግብአቶች ዋጋ አንጻራዊ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ እንደሆነ ይታወሳል፡፡

መንግሥት ለቤቶች ልማት የሚውሉ የአርማታ ብረቶችን ግዢ በግዙፍ መጠን ከአገር ውስጥና ከውጭ ኩባንያዎች ሲሸምት ቆይቷል፡፡ በዋጋ ረገድ የተሻሉ ናቸው ባይባሉም አገር በቀል ፋብሪካዎችንና የብረታ ብረት ኢንደስትሪውን ለማገዝ በሚል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግዢዎች ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከሚገኙ ድርጅቶች ብቻ እንዲከናወኑ ዉሳኔ ተላልፏል፡፡

በአገር ውስጥ ብረት አምራቾችና ብረት አስመጪዎች መሐል ለዓመታት የዘለቀ አለመግባባት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ የብረት አስመጪዎች የአገር ቤት ብረት አምራቾች በየጨረታው እያገኙ ያሉት ልዩ ማበረታቻ ተገቢ እንዳልሆነ ከመከራከር አልቦዘኑም፡፡ ብረት አገር ቤት በመመረቱ የዋጋ ተወዳዳሪነት ማምጣት እንዳልተቻለ፣ ከምርቱ 85 በመቶ የሚይዘውን ጥሬ ዕቃ ከውጭ የሚመጣ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንዳልተቻለ፣ የአገር ውስጥ ምርቱ የጥራት ጥያቄ የሚነሳበት በመሆኑ ተገቢ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

ቻይና የብረት ዋጋን በድጎማ ጭምር  በዓለም ገበያ ላይ በመርጨቷ ባለፈው ዓመት አጋማሽ በብረት ዋጋ ታሪክ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ታይቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሚያዚያ 2008 ለምሳሌ የአንድ ቶን ዋጋ እስከ 90 ዶላር መውረድ የቻለበት ወቅት እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ጭንቅ ውስጥ መሆኗ አስመጪዎችንም ሆነ የአገር ውስጥ ብረት አምራቾችን በእኩል እያስጨነቀ ይገኛል፡፡ በተለይም የውጭ ምንዛሬን በጥቁር ገበያ ከሦስተኛ አገር ለማስተላለፍ የሚገደዱ አስመጪዎች ተጨማሪ ወጪያቸውን በሚሸጡት ምርት ላይ ለመጫን ስለሚገደዱ አሁን አሁን ለሚፈጠሩ የዋጋ ንረቶች ምክንያት ሆነዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 11 የሚሆኑ ብረት አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ላይ ናቸው፡፡ ሌሎች አምስት  ምርት ያልጀመሩና ገና ፋብሪካ ተከላ ላይ እንዳሉ ይነገራል፡፡ ከአስራ አንዱ ሥራ ላይ ከሚገኙት ዉስጥ አምስቱ ብቻ በኢትዮጵያዊያ የተያዙ ሲሆን ቀሪዎቹ በሽርክና አልያም በዉጭ ኩባንያዎች የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ለብረታ ብረት ኢንደስትሪው ቅርብ የሆኑ ባለሞያዎች እንደሚናገሩት የፋብሪካዎች አገር ውስጥ መሆን ብቻውን የሚጨምረው ፋይዳ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ይህም የሆነው ፋብሪዎቹ የወዳደቁ ብረቶችን አቅልጦ ቅርጽ ከማውጣት ያለፈ እሴት የሚጨምር ሥራ የመሥራት አቅም ስለማይኖራቸው ነው፡፡ የብረት ማዕድን ፍለጋ በአገሪቱ በጣት የሚቆጠሩ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ዘርፍ ነው፡፡