ዋዜማ ራዲዮ- ነሀሴ 28 /2008 ዓም የቂሊንጦን ማረሚያ ቤት አቃጥላችኃል ተበለው ተከሰው ከነበሩ 38 ተከሳሾች ውስጥ የቀሩ 4 ተከሳሾች ነሀሴ 1/2011 ዓም ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን ዛሬ ነሀሴ 13/2011 ክስ ማቅለያ ካላቸው እንዲያቀረወቡ ትእዛዝ በተሰጠው መሰረት ማቅለያ የለንም ባልፈፀምነው ወንጀል ክስ አቅልሉልን አንልም ስላሉ ፍርድ ለመስማት ለጥቅምት 7/2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል ፡፡

በነ ማስረሻ ሰጤ ምዝገብ ተከሰው ከነበሩ 38 ተከሳሾች ውስጥ 31ኛ ተከሳሽ ጌታቸው እሸቴ 32ኛ ቶፊቅ ሽኩር 33ኛ ሸምሱ ሰይድ እንዲሁም 34ኛ ፍፁም ጌታቸው በወንጀል ህጉን አንቀፅ 540 እና 464 (ለ) ላይ እንዲከላከሉ በተወሰነው መሰረት ክሳቸውን በመከታተል ላይ የቆዩ ሲሆን ነሀሴ 1 2011 ዓ ም ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት በነበረው ችሎት ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ብሎ ብይን የሰጣቸው ሲሆን ይህንን ተከትሎ እኛን የሚመለከት ፍርድ አይደለም በማለት ችሎት ውስጥ ያሉ መቀመጣዎችን መሰባበር ከችሎት ከወጡ በኀላ ድንጋይ በመወርወር ተኩስ እስኪከፈት ድረስ ሁከት ተቀስቅሶም ነበር።

የመሀል ዳኛው ድርጊቱን በምን ምክንያት እንደፈፀሙ ተከሳሾቹን ለችሎቱ እንዲያስረዱ የጠየቁ ሲሆን 34ኛ ተከሳሽ ፍፁም ጌታቸው “በዚ ችሎት ፍትህ እናገኛለን የሚል እምነት ነበረን ለዛም ነው ክሳችንን በትእግስት ስንከታተል የነበረው…. 159 ተከሳሾች ፈታችሁ 4 የድሀ ልጆች ላይ ነው የፈረዳችሁት፡፡ ችሎቱ ምንም አልተቀየረም” ብሏል፡፡

የመሀል ዳኛው ” ከኛ በላይ ይግባኝ ማለት ትችላላችሁ እኛ የቀረበልንን ማስረጃ መርምረን ነው ብይን የሰጠነው” ብለው ” የዛሬ ቀጠሮ የቅጣት ማቅለያ እንድታቀርቡ ነው” ሲሉ 31ኛ ተከሳሽ እጁን አውጥቶ “የፈለጋችሁን ቅጡን ባልሰራነው ጥፋት ፍርዱን አቅልሉልን አንልም ፡፡ እጀ እረጅሞች ከጀርባችሁ አሉ” ብላል፡፡

በነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ ከአልሸባብ ከኦነግ እና ከግንቦት 7 አመራሮች ጋር በመነጋገር ተልእኮ በመቀበል ነሀሴ 28/ 2008 የቃሊቲ ቃጠሎ አቀናብራችኋል በቃጠሎው ለሞቱ 23 ሰዎች ህይወት እና ለወደመው ንብረት ተጠያቂ ናችሁ ተብለው ከተከሰሱ 38 ተከሳሾች ሚያዚያ 30 /2010 34 ተከሳሾች እንደተፈቱ ይታወሳል፡፡

33ኛ ተከሳሽ ቶፊቅ “ፍርድቤቱ በኛ ላይ ተደራርሮብናል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸውንና ስም ያላቸውን ስትፈቱ ድሆች ላይ ላይ ግን ትፈርዳላችሁ፣ እኔ ባልፈፀምኩት አቅልልኝ አልልህም…. ” ብላል፡፡