FILE

በሰሜኑ ጦርነት ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ በአንድ በኩል የመንግስት ኋይሎች በሌላ ወገን ሲያደርጉት ከነበረው ፍልሚያ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን፣ የደረሰው ጉዳትም እጅግ ዘግናኝ መሆኑን የሚያትት የምርመራ ሪፖርት በኢትዮጵያ ስብዓዊ መብት ኮምሽን በኩል ዛሬ ይፋ ተደርጓል። ዋዜማ ራዲዮ የሪፖርቱን አብይ ነጥቦች ተመልክታለች። አንብቡት

ዋዜማ ራዲዮ-የኢትጵያ ሰብዓዊ  መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. የትግራይ ታጣቂዎች በአፋርና አማራ ክልሎች በከፈቱት ወታደራዊ ጥቃት በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎም በሁለቱም በጦርነቱ በተሰለፉ ወገኖች ተፈጽሟል ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡

ኢሰመኮ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም. ድረስ ባሰማራው 29 አባላት ያሉት ቡድንና ‹‹ምክንያታዊ አሳማኝነት›› በተሰኘ የማስረጃ ምዘና ስልት አማካኝነት በአፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ በቆየው ጦርነት ሰፋ ያለ ምርመራ ማካሄዱን አስታውቋል፡፡

ሪፖርቱ እንደሚያሳው በአንድ ወገን ህወሃት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይም ኦነግ ሸኔ በመባል ከሚጠሩት ታጣቂ ኃይሎችን እና በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ማለትም የአገር  መከላከያ ሠራዊትና በአማራ እና አፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎችንና ተባባሪ ሚሊሺያዎች አማካኝነት የመብት ጥሰቱ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

የምርመራው ይዘት በዋነኝነት በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ ያኮረ ቢሆንም  ቢሆንም፤ በተወሰነ መጠን በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉ የአየር ላይ ጥቃቶችን በሚመለከትም ክትትል እና ምርመራ  መደረጉ ተብራርቷል፡፡

ምርመራው የጦርነቱ ሰለባ በነበሩት በአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ ዞን፣ኪልበቲ ረሱ ዞን፣ አውሲ ረሱ ዞን ፤ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ሰሜን ወሎ ፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣  ሰሜን ሸዋ ዞን ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በርካታ ከተሞችና በትግራይ ክልል ደቡብ ምሥራቅ  ዞን ተፈጸሙ የተባሉ የአየር ላይ ጥቃቶችንና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን በሚመለከት ከተጎጂዎች፣ ከምስክሮች እና ከሚመለከታቸው ምንጮች መረጃዎችና ማስረጃዎችን እንዳሰባሰበ የተቋሙ ሪፖርት ያመላክታል፡፡

በዚህ ጦርነት ወቅት በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ ወገኖች በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ልዩ ጥበቃ የሚደረግላቸው በሲቪል ሰዎች ላይ በተለይም በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን እንዲሁም በሲቪል ሰዎችና ቁሶች ላይ ተገቢው ጥንቃቄ ያልተደረገበት፣ የመለየት መርህን ያልተከተለና ያልተመጣጠነ ጥቃት እንደተፈጸመ አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርት እንደሚያመላክተው በአፋርና በአማራ ክልሎች ምርመራ አካሄድኩባቸው ባላቸው ስፍራዎች ሆነ ተብለው የተፈጸሙ ሕገወጥ ግድያዎችን ሳይጨምር፤ በጦርነቱ ውስጥ በሲቪል ሰዎች ላይ በደረሰ የሕይወትና የአካል ጉዳት ብቻ ቢያንስ 403 ሲቪል ሰዎች ለሞት እንዲሁም 309 ሲቪል ሰዎች ለቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡

ለአብነትም የትግራይ ታጣቂዎች ሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በአፋር ክልል ጋሊኮማ ቀበሌ የጋሊኮማ ተራራ ላይ ሰፍረው የነበሩ የአፋር ልዩ ኃይሎችን በሚያጠቁበት ወቅት ሲቪል ሰዎችን ሳይለዩ በፈጸሙት ጥቃት 27 ሕፃናትን ጨምሮ 107 ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውንና 35 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን ሪፖርቱ አስነብቧል፡፡

የትግራይ ታጣቂዎች ከነሃሴ12 እስከ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በደባርቅ ወረዳ የአዲጋግራ፣ የአብርሃም እና የአዳጋት ቀበሌዎችን በመያዝ፤ የአርሶ አደሮችን ቤት እንደ ምሽግ አድርገው በመዋጋታቸው በመከላከያ ሠራዊት በተተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች 6 ሲቪል ሰዎች እንደገደሉ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ‹‹ለመንግሥት ኃይሎች ሰላይ ናችሁ፤ የግላችሁን የጦር መሳሪያ አምጡ፤›› በሚል በሕገወጥ መንገድና  ከዳኝነት ውጪ በተፈጸመ ግድያ በአማራ እና የአፋር ክልል በትግራይ ኃይሎች ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ 

ኮሚሽኑ በህገወጥ መንገድ ተገደሉ ከተባሉት ሰዎች መካከል በዋነኝነት በሰሜን ወሎ ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ ከነሃሴ 24 እስከ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ብቻ 47 ሰዎች ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን በአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ አሰለሌ ቀለበት ወንበር ቀበሌ አምቦውሃ ጎጥ ኅዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ለቀብር የተሰበሰቡ ሲቪል ሰዎች ላይ በመተኮስና ቤት ለቤት በመግባት 40 ሲቪል ሰዎች፣ በአፋር ክልል ካሳጊታ ከተማ አትኮማ አካባቢ የ9 ዓመት ሕፃንና የ18 ዓመት ወጣት ሴት በትግራይ ታጣቂዎች ደረት እና ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመትተው የተገደሉ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ ልዩ ቦታው እንቶሊ አካባቢ በታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም. በመከላከያ ሠራዊት ወታደሮች የተገደሉ ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎች ይገኙበታል፡፡

የትግራይ ታጣቂዎች በሲቪል ሰዎች ላይ በጭካኔ የመደብደብ፣ የማዋረድ እና የማሰቃየት፣እግር ላይ ሚስማር መምታት ማሰቃየትና፣ ብልትን በካራ መተልተል፣እግርና እጁን ገልብጦ ማሰር አይነት ጭካኔ የተሞላበትና ኢሰብአዊና አዋራጅ አያያዝና ቅጣት መፈጸሙንና ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልንና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀልን ሊያቋቁም በሚችል መልኩ የእገታ እና አስገድዶ መሰወር ተግባራትን መፈጸማቸውን በሪፖርቱ አመላቷል፡፡

በተጨማሪም ሪፖርቱ  በአፋር ክልል ቡርቃ ቀበሌ ሙዴና አካባቢ ለገበያ የወጡ 8 ሰዎች በትግራይ ተጣቂዎች  በግዳጅ መወሰዳቸውንና  ኮሚሽኑ ምርመራውን እስካከናወነበት ጊዜ ድረስ ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን እንደማያውቁ አስረድቷል፡፡

የምርመራ ሪፖርቱ በደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት ወረዳ ንፋስ መውጫ ከተማ የትግራይ ታጣቂዎች አስገድደው ደፍረዋት ብዙ ደም የፈሰሳት ሴትና ከህመሟ በማገገም ላይ በነበረችበት ወቅት በድጋሜ ሊደፍሯት የነበረችን ሴት የሰጠችወን ቃል እንደሚከተለው አስቀምጦታል፣

‹‹አንደኛው  ታጣቂ ሊደፍረኝሱሪዬን ሲያወልቅ ደም ሲመለከት አስጠላሁት እናተፋብኝ፤ ሰደበኝ እኔም ተስፋ ቆርጨ ራሴን ላጠፋ እያሰብኩ ስለነበር አልፈራሁትም፤ መልሼ ስሰድበው ተናዶ የጠመንጃውን አፈ ሙዝ በማህፀኔ ውስጥ ከተተው።ሕመሙ ከአቅም በላይ ስለነበር ራሴን ሳትኩ፡፡ አሁን ለፊስቱላ በሽታ ሕክምና እየተከታተልኩ ነው

በተመሳሳይታጣቂዎች በመፈራረቅ  የአስገድዶ መድፈር ጥቃት የተፈጸመባትና በኋላም ሕክምና ስታደርግ በተላላፊ በሽታ እንደተያዘች ያወቀች፣የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ደርሶባት ጥቃቱ በተፈጸመባት ማግስት በገመድ ታንቃ ሞታ የተኘች፣ የ2 ዓመት ሕፃን ልጇ ባለበት ለ3 የተደፈረች፣  አስገድዶ መድፈር የደረሰባቸው የ60 ዓመት አረጋዊት፣ የኦነግ ሸኔ ለፍተሻ በገቡበት መኖሪያ ቤት የነበረችን ሴት ብሔሯ አማራ መሆኑን ጠይቀው በቡድን የተደፈረችና በርካታ መሰል ጥቃቶች እንዳደረሱ የገለጸው ሪፖርቱ የትግራይ ታጣቂዎች በሴቶች ላይ የፈጸሙት ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃትን ስልታዊ በሆነ መንገድ ለጦርነት አላማ እንዳዋሉት የሚያስረዳ ሪፖርት ማግኘቱንና የጦር ወንጀልም ሊሆኑ እንደሚችሉ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

በንብረት ላይ የተፈጸመ ዘረፋ፣ ገፈፋ እና ውድመትን ጨምሮ ያመላከተው የምርመራ ሪፖርቱ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በነበሩ እና ኮሚሽኑ ምርመራ ባደረገባቸው አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በተደራጀ መልኩ የትግራይ ታጣቂዎች በመንግሥት አስተዳደር ተቋማት፣ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (በተለይ የጤና ተቋማት እና የትምህርት ተቋማት) ፣ በግል ንብረቶች እና በንግድ ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋ፣ ገፈፋ እና የንብረት ውድመት መፈጸሙን አስረድቷል፡፡

በመጨረሻም ኮሚሽኑ የጦርነቱ ተሳታፊዎች በአባሎቻቸው ለተፈጸሙ ጥሰቶች ኃላፊነት በመውሰድና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሰሩና ፆታዊ ጥቃት የፈጸሙትን ጨምሮ የሰብአዊ መብት እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ሰዎችና ቡድኖች ሁሉ ተጠያቂ ለማድረግ ገለልተኛ፣ ተአማኒ እና የሰብአዊ መብቶች ደረጃውን የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት በአስቸኳይ እንዲጀመር ሲል አሳስቧል፡፡

ኢሰመኮ በመግለጫው እንደስነበበው ይህ የመብት ጥሰት ሪፖርት እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የትግራይ ኃይሎች በጥር ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአፋር ክልል ዳግም በከፈቱት ወታደራዊ ጥቃት 5 ወረዳዎችንና የአብአላ ከተማን ተቆጣጥረው  እንደሚገኙ ያስታወቀ ሲሆን በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲቪል ሰዎች  መሞታውን እንዲሁም በርካቶች ለአካል እና ለሥነልቦና ጉዳት መዳረጋቸውን የገለጸ ሲሆን ፆታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶችም እንደተፈጸመባቸውና በተጨማሪም በመሰረተ ልማቶች ላይ ሰፊ ዘረፋ እና ውድመት  መከሰቱን አስታውቋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]