Kerin Geremew (1)ቁጭት

አቶ ብርሃኑ በጃንሆይ ጊዜ መጽሐፍ አከፋፋይ የነበሩ  አንባቢ- ነጋዴ ናቸው፡፡ ዛሬ ሸምግለዋል፡፡ አብረዎት በዕድሜ ከገፉ መጻሕፍት አንዱን ይጥቀሱ ቢባሉ ‹‹ቀሪን ገረመው›› ለማለት ሁለት ጊዜ ማሰብ አያስፈልጋቸውም ፡፡ የዛሬ 48 ዓመት ‹‹ቀሪን ገረመው- የአርበኞች ታሪክ›› የሕትመት ብርሃን ሲያገኝ በ2 ብር ተረክበው በ3 ብር ያከፋፍሉት ነበር፡፡ ‹‹ይገርመሀል…በወቅቱ ተወዳጅ መጽሐፍ ነበር›› ይላሉ ግማሽ ምዕተ ዓመት በሚንሸራተት ትዝታ፡፡

ያን ጊዜ መጽሐፉ እንደቆሎ ተሸጠና እንደገና ደግሞ ለውጡን ተከትሎ ድንገት ከገበያ ጠፋ፡፡ ነጋዴዎች ቅጂው ከነበራቸው ሰዎች እየገዙ ቅጂውን አበክረው ለሚፈልጉ ሰዎች እስከ 1500 ብር ድረስ ይሸጡት ነበር፡፡ በርግጥም ‹‹ወመዘክር›› ከነበሩ ጥቂት የንባብ ቅጂዎች በስተቀር መጽሐፉ ከአንባቢ እጅ ለዓመታት ተሰውሮ ቆይቷል፡፡ ከዚያ ሁሉ ዘመን በኋላ የሕትመት ብርሃን እንዲያገኝ የኾነውም በአርበኛው ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ የልጅ ልጆች መልካም ፍቃድና በሊትማን ቡክስ አሳታሚነት ነበር፡፡

መዋዕለ ታደሰ ዘወልዴ

ታደሰ ዘወልዴ ‹‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙልዋት›› በሚለው መለኮታዊ አዋጅ ከተላለፈበት ጊዜ አንስቶ ያልነበረ ሁሉ እንዲኖር በተሰጠው መብት መሠረት ተራውን ሲጠብቅ ኑሮ  በሺ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አምስት በሸዋ ጠቅላይ ግዛት መንዝና ይፋት አውራጃ ዉስጥ ከአቶ ዘወልድ ማርያም ሀብተማርያምና ከወይዘሮ ወለተ ማርያም ተወለደ፡፡ ….

ይላሉ አርበኛው ቀኛዝማች ግለ ታሪካቸውን በግርድፍ አንቀጽ ሲያስቀምጡ፡፡ ዘመናዊ ትምህርታቸውን ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ነው የተማሩት፡፡ በ1919 ዓ.ም ወደ ግብጽ አገር ሄደው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ከተመረጡት ሃያ አንድ የኢትዮጵያ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት እስክንድሪያ ከተማ ሊሴ ፍራንሴስ ትምህርት ቤት ገቡ፡፡ ከዚያም ወደ ፈረንሳይ አገር ተሻግረው የቴሌኮሚኒኬሽን ልዩ ትምህርት ሲማሩ ቆዩ፡፡ ኾኖም በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ የፋሺስት ወረራ ስለደረሰ የክተቱን አዋጅ በወዶዘማችነት በመቀበል ከፓሪስ ወደ ማይጨው ዘመቱ፡፡ አንባቢ የዚህን አንቀጽ የመጨረሻ ዐረፍተ ነገር በጥሞና አንድ ጊዜ በድጋሚ እንዲያነብ የዚህ ዳሰሳ ፀሐፊ በአክብሮት ይማፀናል፤ አንቀጹ ስለባለታሪኩ አያሌ ስለሚናገር፡፡

ደራሲው ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ቆራጥ አርበኛ ብቻም ሳይሆኑ ትንታግ ፀሐፊም ነበሩ፡፡ ከፈረንሳይ ማይጨው ዘምተው በአምስት ዓመቱ የመከራ ዘመን ሰሜን ሸዋ ከጠላት ጦር ጋር ሲዋደቁ ከቆዩ በኋላ በድል ማግስት ሌላ ትግል ጀመሩ፡፡ የቀለም ትግል፤ ታሪክን ለትውልድ የማሻገር ሽምቅ ዉጊያ፡፡

‹‹ቀሪን ገረመው-የአርበኞች ታሪክ›› ከሚለውና ሰፊ ተቀባይነት ካገኘላቸው የታሪክ ዘጋቢ መጽሐፍ ሌላ 5 የተለያዩ መጻሕፍትን ለአንባቢ አድርሰዋል፡፡ የሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) የሕይወት ታሪክ አንዱ ነው፡፡ ምክንያተ ጽሑፋቸውን ሲያስረዱም-

   በደካማው አቅሜ ከአምስት ዓመት የጦርነት ትዝታ እኔ የማውቀውን በዘመኑ ለመገኘት ዕድሜ ላልፈቀደላቸው ወገኖቼ ለመተረክ ሞክሬያለሁ፤ አባቶች ‹‹ከጠላት ይታረቃሉ እንጂ ከጠላት ተበድረው አይበሉም›› እንዲሉ (ገጽ 387)

ብለው ይገልጹታል፡፡ ታሪክን ስለመዘገብ ዓላማና ግባቸውን ሲያስረዱ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡-

…በመጨረሻ የማሳስባችሁ ይህን የአምስት ዓመት ተጋድሎ በታሪክ መልክ ጽፌ ለትውልድ ለማበርከት የተገደድኩት አንደኛ በቃል ያለ ነገር ሁሉ ስለሚረሳ አባቶች ስለሀገራቸው ያደረጉት የአምስት አመት መሥዋዕትነት ልጆች በየጊዜው እያነበቡ እንዲያስታውሱት ለማድረግ፣ ሁለተኛ ሀገርን ለመድፈር እጁን የሚያነሳ ሁሉ የጋራ ጠላት ስለሆነ የጋራ ጠላትን ለማጥቃት ሴት ወንድ ሳይል የሁሉንም ትብብር እንደሚጠይቅና ይህም ከዚህ ቀደም የሀገራችንን ነጻነት ያስገኘ መልካም መሣሪያ መሆኑን ከእኔ በኋላ ለሚነሣው ትውልድ የጽሑፍ ማስታወሻ ጥዬ ለመሔድ ስለተገደድኩ ነው፡፡ (ገጽ፣386)

ትግል ተራኪ መጻሕፍት

በአምስት ዓመቱ የፋሺስት ወራራ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የነበረውን የትግል ታሪክ ከዚህ ቀደም ጥቂት ፀሐፍት በድርሳን መልክ እያሰናዱ ትውልድ እንዲማርበት የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡በተለይ በየትግሉ አውድ ላይ ከጠላት ጋር ሲተናነቁ ከነበሩ አርበኞች አፍ በቀጥታ የተቀዱ ታሪካዊ ኩኽነቶችን በአለፍ ገደምም ቢሆን በሕትመት ብርሃን መጎብኘታቸው አልቀረም፡፡ የዚህን ዓይነት ዓላማ ያነገቡ ታሪክ ቀመሰ የጥበብ ሥራዎች መበራከት በዚህ ዘመን የሚታሰብ አልሆነም፡፡ ቢሆንና ቢሳካ ደግሞ ታሪክ ሠሪዎቹን ግለሰቦች ከመዘከር አልፎ ተርፎ ቋሚው ትውልድ ጥልቅ የሃገር ፍቅር ምንነትን ከቃል ባለፈ በተግባር እንዲረዳ እና ለሃገሩ አንድነት ባለው አቅም እና ሙያ ዘብ እንዲቆም ትልቅ የወኔ ስንቅን ባቀበለ ነበር፡፡ በተለይ እንዲህ በጎጥ ተደራጅተን በምንናቆርበት ዘመን እንዲህ ያሉ መጻሕፍት ምንኛ በረዱን፡፡ በዚህ ክረምት ዳጎስ ባለ ይዘት እና ሞላ ባለ ቁመና ገቢያውን የተቀላቀለው ‹‹ቀሪን ገረመው›› የዛሬው ‹‹የምዕራፍ አንድ›› የዋዜማ የዳሰሳ ምርጫችን የኾነውም ለዚሁ ነው፡፡

የይዘት ዳሰሳ

መጽሐፉ በይዘቱ ጥልቅ፣ በትርክት ዘዬው ቀልብ ገዢ ነው፡፡ ሌላው ይቅርና ርዕሱን ገፋ ብሎ ለፈተሸ በራሱ ድንክ ታሪክ ነጋሪ ኾኖ ያገኘዋል፡፡

    …(አገራችን) በአንድ በኩል እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ በላይ የመጣውን ወራሪ እንደ አንበጣ በአየር በአየር ብላ በአየር አስቀርታለች፤ በሌላ በኩል ደግሞ አርበኞቿን በዱር በገደል አሠልፋ …አርባ አመት ሙሉ የተደከመበትን ታንክና ሌላም ዘመናዊ መሣሪያ በ5 ዓመት አስጨርሳ ጠላቷን ባዶ እጁን መልሳዋለች፤ ለታሪኩም ‹‹ቀሪን ገረመው›› የሚል አርእስት የሰጠነው ለዚሁ ነው፡፡ (ገጽ 8)

ለመጽሐፉ መጠሪያ ስያሜ ‹‹ቀሪን ገረመው›› መባል አስፈልጎታል፡፡ ይኸው የነገሩ መነሻ ሊሆን የቻለው አርበኞች በየጊዜው በሚያደርጉት ንግግራቸው ‹‹ቀሪን ገረመው›› ማለት እንደመልካም ቅመም (ኾኖ) የሚሰሟቸውን በመገረም ላይ ያደርሳቸው ነበር፡፡ (ገጽ 7)

ቀኛዝማች ሰሜን ሸዋ ላይ ብቻ ማተኮራቸው ለትውልድ ቀያቸው ማድላታቸው አልነበረም፡፡ እንዲያውም ‹‹ያልኖሩበትን ታሪክ መጻፍ እንዴት ይደፈራል?›› ብለው ይጠይቃሉ፡፡

የኢትዮጵያ አርበኛ በሸዋ ብቻ ሳይሆኑ በቤጌምድርና በሰሜን በጎጃም በትግሬ፣ በሐረርና በቦረና፣ በወለጋ በሌላም ጠቅላይ ግዛት ስላልታጡ ታሪካቸውን አጠቃልሎ ለመጻፍ በዚህ ሁሉ ቦታ በጊዘው የነበረና ጉዳዩን የተከታተለ ሰው ያለ እንደሆነ ነው እንጂ፣ ጠንቅቆ የማያውቅ ወይም ያልተረዳ ሰው ሊጽፈው አይችልም፡፡

መጽሓፉ በጣሊያን የአምስት ዓመት ወረራ ወቅት ለቀሪው፣ለቋሚው የሚተረክ ጀብዱ የሠረቱን ቆራጥ የሀገራችንን አርበኞች ለመዘከር ከዛሬ አርባ አመት በፊት በቀኝ አዝማች ታደሰ ዘወልደ አማካኝነት ነው ለሕትመት የበቃው፡፡እንሆ አሁን ደግሞ ከአርባ ስምንት ዓመት የእፎይታ ጊዜ በኋላ ዳግም ወደ ገቢያ ተመልሷል፡፡

ነገርን ከመሠረቱ እማኝ ኾኖ የሚያስረዳው ይኸ መጽሐፍ በመከራው ጊዜ የነበሩትን አንኳር ጉዳዮች አንድም ያስቀረው ያለ አይመስልም፡፡ የልጅ ኃይለማርያም ማሞን ተጋድሎ፣ የራስ አበበን ጀብድ፣ የልጅ ግዛቸው ኃይሌ፣ የደጃዝማች አበራ ካሣ፣ የአብረሃ ደቦጭ፣ የሞገስ አስገዶም ዝና፣ የሻለቃ መስፍን ስለሺ የለት ዉሎዎች ሁሉ ተዘግበዋል፡፡ በዚህም አያበቃም፡፡ የመርሐቤቴ ዠግኖች ታሪክ፣ የደጃዝማች ገለታ ቆርቾ፣ የነደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ የነ በቀለ ወያ፣ የወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ገድሎች አንድባንድ እግር በግር ተተረክዋል፡፡

ይህን ሁሉ ታሪክ የዘገቡልን ደራሲ በሀገረ ፈረንሳይ ምራቅ የሚያስውጥ የአስኳላ ትምህርታቸውን ገሸሽ አድርገው ገና የትግደሉ ዓውድ ሳይሟሟቅ ነበር  ወደ እናት ሀገራቸው ለመመለስ የወሰኑት ፡፡የእቴጌ ጣይቱን የእምነት ዕዳ ለመክፈል፣ እግራቸውን ለጠጠር፣ደረታቸው ለጥይት አረር ሊሰጡ አጃኢብ በሚያስብል ቆራጥነት ወደ ሃብሽ ምድር ፈጥነው ተከተቱ፡፡በእርግጥ ይህንን ዓይነት እንደእሳተ ጎመራ የሚፋጅ ጥልቅ የሃገር ፍቅር የሁሉም ኢትዮጲያዊ ስነልቡና መገለጫ እንደነበረ በወቅቱ የታሪክ ተዋናይ ከሆኑ ግለሰቦች እማኝነት መረዳት ይቻላል፡፡

የጠቡ መነሻ

1928 ዓ.ም ጣሊያን በማይጨው ጦርነት በአውሮፕላን መርዝ ጢስ እየታጀበ  ድል አድርጎ ወደ መሃል ሃገር ሲገሰግስ ከጣሊያን መርዝ ጢስ እና መትርየስ የተረፉት እፍኝ የማይሞሉት አርበኞች ለስልታዊ ለውጥ ትግል ለመዘጋጀት ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጲያ መስግስግ ጀመሩ፡፡ ጣሊያን እጅግም ብዙ ዘመናዊ ጦር ያልታጠቀውን የኢትዮጲያ ጦር ድል ነስቶ የሃገሪቱን መናገሻ ከተማ አዲስ አበባ ከያዘ በኋላ ሁሉ ነገር ያለቀ የከተመ መስሎት ነበር፡፡በእየደረሰበት ቦታ የሃገሬው ነዋሪ ላይ ያደርስ የነበረው ግፍ ለአእምሮ የሚጠግግ ነበር፡፡ይህ ከልክ ያለፈ ግፍ ግን ውሎ አድሮ ማጣፊያው ከባድ ወደ ሆነ መሪሪ የአርበኝነት ትግል ለመለወጥ ምክነያት ሆነ፡፡በእየግዛቱ በውሰጥ እና በውጭ የተከፋፈለው አርበኛ ለጣሊያን የእግር እሳት ለመሆን ጊዜ አልፈጀበትም፡፡

የትግሉን ምዕራፍ የቀየረ አጋጣሚ

ልጅ ኃይለማሪም ማሞ እንደ አልጄሪያዊው ፍራንዝ ፋኖን ፣እንደ ሊቢያዊው ኦማር ሙክታር አሊ ለወራሪው ፋሽስታዊ ኃይል የአልበገርነት፣የእምቢ አልገዛም ባይነትን ጠንካራ መንፈስ በዛን ዘመን አርበኞች ላይ በማጋባት ጎህ ቀደዱ ፡፡  ሃገር አማን ብሎ ወደ መሀል ሃገር በሚተመው የፋሽስት ወራሪ ኃይል ላይ በደፈጣ ውጊያ ከፍተኛ ኪሳራ አደረሱ፡፡ በዚህም የተነሳ መጪው ዘመን ከጀግኖኞች አርበኞች ጋር ለፋሽስት ኢጣሊያ ጨለማ መሆኑን የተግባር መልዕክት እሰተላለፉ፡፡ በገጽ 15 ላይ እንዲህ ይነበባል

ልጅ ኃይለማሪያም በአሥር ሰዓት ገደማ ላይ ከቤታቸው ተነሥተው ጫጫ ሱኬ ሴራቤ ከምትባለው ቀበሌ ምቹ ቦታ ይዘው ጠበቁት፤ጠላትም ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ አልፋለሁ ሲል አደጋ ጥለው አምስት ካሚኒዮኖች ሰብረው በውስጡ የነበሩትን አንድ መቶ አርባ የሚሆኑ የጠላት ወታደሮች ገድለው ሳባት ማረኩ፤ከእነዚሁ ሁለት ሸሽተን እናመልጣለን ብለው ሲሞክሩ በጥይት ተመትተው ተያዙ፡፡

ይህ የልጅ ኃይለማሪያም ገድል የመንፈስ ጥንካሬ የዘራባቸው የሸዋ ጎበዛዝት ቀፎው እንደተነካበት ንብ በነቂስ ለምተመም አልዘገየም ነበር፡፡ያላቸው ጥይትም ሆነ ስንቅ የሚያወላዳ ስላልነበረ ምሽግ ይዞ ከመዋጋት ይልቅ የደፈጣ ወጊያን ምርጫቸው አደረጉ፡፡ጥሬ በቆሎ ቀርቀጭ እያደረጉ፣ከወንዝ ውሃ እየተጎነጩ፣ በአንድ ቦታ ሳይረጉ ጣሊያንን በደፈጣ ውጊያ መግቢያ መውጪያ አሳጡት፡፡

የአርበኛው ትንቅንቅ ከጽጉረ ልውጥ ፋሺስታዊ ኃይል ብቻ ጋር አልነበረም፤ከራሱ ጉያ ከወጡት ባንዳ ወንድሞችም ጭምር እንጂ፡፡ጣሊያን በገንዘብ የሚገዛቸው ባንዳዎች ወገናቸውን ለመወጋት ግባራቸውን አጥፈው አያውቁም፡፡ የወራሪው ጦር እነዚህን ባንዳዎች ከፊት አሰልፎ እርሱ ከኋላ ደጀን ሆኖ የተፋፋመ ተኩስ ይከፍታል፡፡ጣሊያን ባንዶዎችን የሚያጠምድበት መላ ብዙ ነው፡፡ባላገሩን በጥሪት ፣ከተሜውን ደግሞ በሹመት ነበር የሚደልለው፡፡በዚህም ምክነያት አስከፊውን እና ውጣውረድ የበዛበትን የአርበኝነት ሕይወት እርግፈው አድርገው በመተው በተደላደለ የጠላት እጅ ሥር መተዳደር የመረጡ ባንዳዎች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡

አንገት የመበጠስ ትርኢት

አንገት መቀንጠስ የሮማ ካቶሊካዊ እምነት ተከታዮች የሆኑት የፋሽስት ኢጣሊያ ወታደሮች ከአሁኑ እሳላሚዊ ጽንፈኛ ቡድን/ISIS/ በብዙ ዘመን ቀድመው በሀገራችን አፈር ላይ ሲፈጽሙት የኖሩት ትርኢት እንደነበረ ‹‹ቀሪን ገረመው›› ዓይን እማኝነቱን ይሰጠናል፡፡በወቅቱ አንገት መበጠስ ቀጤማ የመበጠስ ያህል እንኳ የከበደ ተግባር ያልነበረ እስኪመስለን በየገጹ ድርጊቱን እናነባለን- በቀኛዝማች የ500 ገጽ ትርክት ዉስጥ አንድ እጁ ከዚሁ ድርጊት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ጣሊያን በአገሬው ላይ ክፉ ሽብር እና ጥልቅ ፍርሃት ሊነዛ ይህንን ተግባር በአደባባይ እንዲያውም በአውደ ርዕይ መልክ በተደጋጋሚ ጊዜ አቅርቧል፡፡ በገጽ 132 ላይ ለምሳሌ እንዲህ እናነባለን፡-

በመትረየስ  በሮምታ ተኩስ  ገድለው አረማዊው ጠላት አንገታቸውን ቆርጦ ወስዶ የአዲስ አበባ መኳንነትና ሴት ወይዘሮ በአዋጅ ደብረ ብርሃን አደባባይ ላይ አንደ ሌክስፖዚሲዮን ዕቃ አስጎበኛቸው።። የዚህም መርዶ ለራስ አበበ ደረሳቸው፡፡

የጣሊያን ገሃድ የወጣ ጭካኔ ትግሉን ወደኋላ ከመጎተት ይልቅ ይባስ ብሎ ለትግሉ እንደ የኃይል ቋት ሆኖ እያገለገለ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአስደንጋጭ ደረጃ በእየአቅጣጫው ፍልሚያውን አጋመው፡፡ ዕለት በዕለት በረሃ የወረዱትን ወንድሞቹን የሚቀላቀለው አርበኞች ቁጥሩ እያሻቀበ ይሄድ ጀመር፡፡ ‹‹ድፍን የነጭ ክፍለ ጦር በአንድ የትግል ሜዳ ጭዳ ሆነ›› የሚለው ወሬ ዜና መሆኑ ቀረ።በየትግል አውዱ ያልታሰበ እልቂት እየገጠመው የተቸገረው  ጠላት  በእርቅ ሰበብ ለማዘናጋት የተለያዩ ስልት ቀየሰ፡፡ ገጽ 123 ላይ እንዲህ ሰፍሯል፤

ፋሽስቶች በጭካኔ ማለት በአረመኔነት ቢሉት ቢያደርጉት የሸዋ አርበኛ ፍንክች ያባ ቢለዋ ልጅ እንደሚባለው ሁሉ የማይበገር ሆኖ ስላገኙት በዕርቅ መንገድ ሰላም ፈላጊዎች መስለው አማላጆቹን እያከታተሉ ቢልኩም ከአገር ደበኛ ጋራ የምን ፍቅር እያለ ልቡ እምቢ አሻፈረኝ በማለት ጠላትን ግራ በማጋባት የሚይዘውን የሚለቀውን አሳጣው፡፡

እርቁን ኋላ ላይ በጄ ለማለት ከአርበኞች ወገን የተወሰነ ርቀት ለመሄድ ሞክረዋል፡፡ እርቁ ላይ ግን ከሁለት ወገን  የሚሰተዋለውን ጥርጣሬ መሻር ስላልተቻለ፣ ጭራሽ  የስምምነቱን  ውል በሥጋ ወደሙ ለማሰር እስከመወስን ተደርሶ እንደነበር ስናነብ አለመደነቅ አንችልም።

ገጽ 129 ይህን እናነባለን›-

ማዦር ሉኬቲ ተመክሮ እንደመጣ በሥጋ ወደሙ እንማልለት፣ስንምልም የኢትዮጲያ ሰንደቅ ዓላማ በቀኝ የኢጣሊያ በግራይ ቁምና ሁለታችንም ወገኖች/ በየባንዲራችን መዳፋችንን አሳርፈን ባንዲራችንን አንከዳም ስንል እንማማል/  ብለው መልስ ሰጡት፡፡

ጣሊያን ለአምስት ዓመታት ለአንዲት ሌሊት እፎይ ብሎ ጎኑን ሳያሳርፍ፣ በዛፍ ላይ እንቅልፍ ነፍስያው ከሥጋው በእየአፍታው እንደተለየ የሽንፈቱ ቀን  መጋቢት 28፣ 1933 ዓ.ም እውን ሆነ፡፡ መጋቢት 28 ቀን ከሥርዓት ለውጥ በኋላ  በሚያዚያ 27፣ 1933 ዓ.ም  እንደተተካ ይታወቃል፡፡ ለዚህም እንደምክንያት የሚቀርበው ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት እንግሊዝ ወደ ሃገራቸው የተመለሱበት ቀን  ሚያዚያ 27፣ 1933 ዓ.ም በመሆኑ ነው፡፡

ቀሪን ገረመው የአርበኞችን ገድል በሽዋ ክፍለሃገር ማለትም በጅሩ፣ቡልጋ፣ተጉለት፣ምንጃር እና አካባቢው የነበረውን የታሪክ ገድል ግሩም በሆነ ሁኔታ በመተረኩ ረገድ ተዋጦለታል ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ዘመን አንባቢ መነጥር ስንመለከተው ከገጹ መብዛት፣ ከቋንቋው መክበድ፣ ከታሪከ መዘርዝር አንጻር ይህ ትውልድ እንዴት ይወጣው ይኾን ብለን ሐሳብ እንዲገባን እንሆናለን፡፡ ምናልባት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ዳግም የሕትመት ብርሃን ሲያገኝ አሳታሚዎቹ፣ አሳታሚዎቹም ባይሆኑ አርታኢዎቹ ያለንበትን ስልቹ ዘመን ተረድተው ምናል ሙዳየ ቃላት እንኳ ቢያሰናዱለት ብዬ ማሰቤ አልቀረም፡፡

ማጠቃለያ

የዚህ ዳሰሳ ፀሐፊ ከ‹‹ቀሪን ገረመው›› መጽሐፍ ገናናነት ጋር የተዋወቅሁት ቀደም ብዬ በአንድ አጋጣሚ ነበር፡ ያውም በመጽሐፍ መልክ ሳይሆን ተመሳሳይ ታሪክን በተሸከሙ ሌላ አንድ ጉምቱ አዛውንት አማካኝነት፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡

ከወራት ቀደም ከእኚህ አሁን በስም ከማልጠቅሳቸው የዕድሜ ባለጠጋ ጀግና ጋር በነበረኝ ትውውቅ የተነሳ ብዙ የጦርነት ውሎዎችን መስማት ቻልኩ፡፡ ቤተሰባቸው የኚህን አባት ግለ-ታሪክ እንድጽፍ ዉል አፈጣጥሞኝ ነበር ይህን የነጻ ወግ ዕድል ያገኘሁት፡፡ አዛውንቱ ታዲያ በየወጋቸው መሐል ‹‹ቀሪን ገረመው›› ይሉኝ ነበር፡፡

በትርክታቸው ቦታው የነበርኩ ያህል በስሜት ተንጫለሁ፡፡ እኚህ የምላችሁ አርበኛ ልክ እንደ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ሁሉ በአምስት ዓመቱ የፋሺስ ወረራ ጊዜ በሸዋ ክፍል ሃገር ቡልጋ አውራጃ ለሀገር ነፃነት ከጠላት ጋር ሲተናነቁ የነበሩ ናቸው፡፡  አሁንም በሕይወት ካሉን የዓይን እማኞች አንዱ ናቸው፡፡  ይህ ማለት አንድ ክፍለዘመን ለመድፈን የቀራቸው ሦስት ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ማን ይናገር የነበረ፣ማን ያርዳ የቀበር እንዲሉ፡፡

በቀጥታ ከእርሳቸው አንደበት የፈለቁ ታሪካዊ እውነታዎች በፈርጅ በፈርጁ ከማሰናዳቱ ጎን ለጎን ‹‹ቀሪን ገረመው›› የሚሉት ነገር ጥያቄ ኾኖብኝ ቆየሁ፡፡ የቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ መጽሐፍ ነገሩን ገላለጠልኝ፡፡ አዛውንቱን በየዕለቱ እንግሊዝ ኤምባሲ ጀርባ ከሚገኝ መጠለያቸው እየሄድኩ በሰማሁ ቁጥር ታዲያ ወደ አእምሮዬ እየመጣ ሲከነክነኝ የነበረው ነገር በየቤቱ እንደ ተራ  የተዘነጉ፣ እንዳገለገለ ዕቃ የተጣሉ ይችን አገር ያቀኑ ስንት ጀግኖች ይኖሩን ይሆን የሚለው ነው፡፡

ብዙ “ቀሪን ገረመዎች” አስታዋሽ አጥተው፣ ታሪካዊ ገድላቸውን ሃገር እና ወገን ትምህርት ሳይቀስምበት እንደተቀበረ ቀርቷል፡፡አሁንም ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ያለን ዕድል በሕይወት ላሉ ጀግኖች አርበኞች የሚገባቸውን ትኩረት ባለመንፈግ ነው፡፡ ‹‹ካዲስኮ አደባባይ፣ ዲኤች ገዳ አደባባይ፣ ጀርመን አደባባይ፣ ዲያስፖራ አደባባይ›› ብለን ሰፈሩን ሁሉ በቆርቆሮ የሰየምነው ነገር ለካንስ ጀግና አልባ ሆነን አይደለም፡፡ ታሪክ ዘንግተን እንጂ፡፡