Samoraዋዜማ ራዲዮ- የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮችን በብቃት በትምህርትና ስልጠና ዝግጅት እንዲሁም የሀገሪቱን የብሄር ተዋፃኦ ባገናዘበ መልኩ ለማደራጀት አዲስ የምደባ መዋቅር መዘጋጀቱን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከመከላከያ ባለስልጣናት ጋር አርብ ዕለት ባደረጉት ውይይት በአዲሱ አደረጃጀትና ማሻሻያ የአመራር ለውጥ የሚደረግ ሲሆን ይህ ለውጥ ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ባገናዘበ መንገድ እንደሚካሄድና ማንንም የመጉዳትና የመጥቀም ተልዕኮ እንደሌለው አስምረውበታል።
“እዚህ ሀገር በሚፈጠር ቀውስ የመጀመሪያው ተጠቂ መከላከያ እንደ ተቋም እናንተ ደግሞ እንደ ግለስብ ናችሁ”  ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።
ከመከላከያ ስራው በጡረታም ይሁን በሌላ ምክንያት የሚገለል አባል ለአገልግሎቱ ክብርና ድጋፍ ይገባዋል፣ እስከዛሬ ውለታቸው ተረስቶ የተጣሉ ለዚህች ሀገር ዋጋ የከፈሉ የሰራዊት አባላት ልዩ ድጋፍ ሊደረግላቸውና ልናስታውሳቸው ይገባል ብለዋል።
ህገ መንግስቱን ከማስከበርና የሀገር ዳር ድንበር ከመጠበቅ በዘለለ ሰራዊቱ የፓርቲ አገልጋይ ሆኖ ከህግ ውጪ የሚሰራበት መንገድ መዘጋት አለበት ያሉት ዐቢይ አህመድ ሰራዊቱ የትኛውም ፓርቲ በምርጫ ወደ ስልጣን ከመጣ ለማገልገል መዘጋጀት አለበት ብለዋል።
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑና ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የሰራዊቱ አባል እንደነገሩን ቀደም ባሉት ሳምንታት በመከላከያ ሰራዊቱ ማሻሻያ ዕቅድ ላይ ከተወሰኑ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ምክክር ተደረጎ ሀሳብ የማሰባሰብ ስራ ሲሰራ ነበር።
ከሰራዊቱ አመራሮች እንደስጋት የቀረበው የአመራሮች ለውጥ መደረግ ያለበት በሂደት እንጂ በአንድ ጀንበር መሆን የለበትም። ጉዳዩ በሰራዊቱ አመራሮች ላይ የሚያስከትለውን ስነ-ልቦናዊ ጫና ለመቀነስ የማላመድ ስራ መሰራት አለበት የሚሉ ሀሳቦች ቀርበዋል።
ስራዊቱን ለማዘመን የቀረበው ሀሳብ አሁን ሰራዊቱ ባለው የተማረ የሰው ሀይል የሚሞከር ባለመሆኑ ሰፊ የአዳዲስ አባላት ቅጥር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይም ተዋጊ ያልሆኑና ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ የቀረቡ አባላትን በከፍተኛ ቁጥር ለማሳደግ ታቅዷል።

አዲሱ ማሻሻያ በርካታ ከህወሀት ጋር በትጥቅ ትግል ቆይተው ወደ ሰራዊቱ የተቀላቀሉ አባላትንና በዕድሜ የገፉትን ወደ ጡረታና አሁን ካሉበት ወርደው እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው። በሰራዊቱ ውስጥ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር 14 በመቶ ያህል ሲሆን የሰራዊቱን ከፍተኛ አመራር ግን 97 በመቶ ያህል ይዘው ይገኛሉ።

ለሰራዊቱ ዘመናዊ ትጥቅ ማቅረብ አንዱ የማሻሻያው ሀሳብ ሲሆን ጉዳዩ በዝርዝር በባለሙያዎች ተጠንቶ ሀገሪቱ ባላት አቅም የዘመናዊ ትጥቅ ባለቤት እንድትሆን ይደረጋል።

ኢትዮጵያ በአመዛኙ የሩሲያ የቻይና የሰሜን ኮርያና ሩማንያ የመሳሰሉ ሀገራት ያመረቱትን ወታደራዊ ቀሳቁስ ለረጅም አመታት የምትጠቀም ሲሆን በተለይ አየር ሀይሉ በምዕራባውያን ሀገራት የተሰሩና በዕርዳታ ጭምር የተገኙ አውሮፕላኖችን የመጠቀም ጉድለት አለበት። የመለዋወጫ ዕቃ አቅርቦትና የዋጋ ውድነትም ከችግሮቹ አንዱ ነው።