Crown condo site
Crown condo site
  • ባለ ‹‹4 መኝታ ቤቶች›› ተገንብተዋል የተባለው ሐሰት ነው

ዋዜማ ራዲዮ- በ40/60 ልማት ላይ የተሳተፉና ለዋዜማ ዘጋቢ የሚያውቁትን መረጃ ያቀበሉ አንድ የንግድ ባንክ የግንባታ ክትትል ባለሞያ ውል የማይፈጸሙባቸው 324 ‹‹ባለ 4-መኝታ ቤቶች›› በመጪው ዓመት ምናልባትም ከከተማው ምርጫ በኋላ ከድርጅት ለሚወከሉ ካድሬዎች ሊሰጡ እንደሚችሉ የሚያመላክት መረጃን ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም በተለምዶ ‹‹ባለ 4-መኝታ ቤቶች›› እየተባሉ የሚጠሩ 40/60 ቤቶች እንደሚባለው በዲዛይን ስህተት የተሠሩ እንዳልሆኑም እኚህ ባለሞያ ማስተባበያ ሰጥተዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ‹‹ለሙከራ በሠራኋቸው የሰንጋ ተራና የክራውን ሳይቶች ባለ አንድ መኝታ አልገነባሁም፣ ባለ 4 መኝታ ቤቶችን ግን በዲዛይን ስህተት ሠርቻለሁ ሲል መቆየቱ ይታወሳል፡፡

‹‹መጀመርያዉኑ 4 መኝታ የሚባል ዲዛይን አልተሠራም፤ የተገነባው ባለ 1 ባለ2 እና ባለ3 መኝታ ነው፡፡ በዲዛይን ስህተት ነው የሚባለውም ሐሰት ነው›› ሲሉ እኚህ ከዋዜማ ጋር ቆይታ ያደረጉት ባለሞያ ተችተዋል፡፡ 4 መኝታ የሚባለው ነገር የመጣው ከውል ጋር መታረቅ ያልቻለን የካሬ ሜትር ልዩነትን ለመሸፈን ተብሎ እንጂ ‹‹4 መኝታ›› ያለው ቁጠባ ቤት ሲጀመርም የሚታሰብ ነገር አይደለም›› የሚሉት ባለሞያው ‹‹ባለ አንድ መኝታ አልገነባንም›› የተባለውም መንግሥትን ትዝብት ውስጥ የሚጥል እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ‹‹ሁሉም ቤቶች ዕቃ ማስቀመጫና የሠራተኛ ማረፊያ ጠባባብ ክፍሎች አሏቸው፤ ያንን ቆጥረው ነው በዲዛይን ስህተት 4 መኝታ ገነባን የሚሉት›› ብለዋል፡፡

ይህንኑ ሐሳባቸውን የሚያጠናክር ማስረጃዎችን ከዋናው የፕላን ቅጂ ጋር ያቀረቡት ባለሞያው እርሳቸው ፕሮጀክቱ ላይ መሳተፍ ከጀመሩ ጀምሮ ቤቶቹ ‹‹ባለ 4 መኝታ›› ተብለው እንዳልተወሰዱና ኋላ ላይ ግን የካሬ ሜትር ተቃርኖ መኖሩ ሲታወቅ  መስተዳደሩ ባለ 4 መኝታ በዲዛይን ስህተት ምክንያት ተገነባ ብሎ ማውራት መጀመሩን ይናገራሉ፡፡

‹‹…ከአባተ ጋር በነበረ ስብሰባ ላይ እነዚህ ቤቶች ወደፊት ውል ካልተፈጸመባቸው ምን እናደርጋቸዋለን?›› የሚል ነገር ተነስቶ እንደነበር አውቃለሁ የሚሉት ባለሞያው፤ ምክትል ከንቲባው አቶ አባተ በወቅቱ  ሰፊ ቤት ሰጥተነው ቤቱ ይሰፋብኛ ብሎ ይቅርብኝ የሚል ዜጋ ይኖራል ብዬ አላምንም፤ ካለ ግን እሰየው፣ ቤቱቹን እኛው እንወስዳቸዋለን›› ማለታቸውን ስብሰባው የተካፈሉ ባልደረቦቼ ነግረውኛል ይላሉ፡፡

ከተራዘመ የግንባታ ሂደት በኋላ ባለፈው የሰኔ ወር ዕጣ ወጥቶባቸው ለባለዕድለኞች እየተላለፉ የሚገኙት እነዚህ የሰንጋ ተራና የክራውን 40/60 ቤቶች የወለል ስፋታቸው ከውል ውጭ መሆኑ ለረዥም ጊዜያት ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ ይህን ተከትሎ መስተዳደሩ ‹‹የዲዛይን ስህተት አጋጥሞኝ ነው›› ቢልም እውነታው ከዚህ እንደሚለይ እኚህ ባለሞያ በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡

‹‹ሲጀመር የዲዛይን ችግር ብሎ ነገር የለም፡፡ ዲዛይን ታይቶ ሳይጸድቅ ሲሚንቶ አይቦካም፡፡›› የሚሉት ባለሞያው ኾኖም የወለል ስፋት ልዩነት ቀድሞ በውል ላይ ከሰፈረው ጋር ለምን ሊቃረን እንደቻለ፣ ወይ ቤቱን ወይ ውሉን ለምን ቀደም ብሎ ማስተካከል እንዳልተቻለ ለርሳቸውም ግልጽ አይደለም፡፡

‹‹ዞሮ ዞሮ ችግሩ እንደሚባለው በቅርብ የተደረሰበት ሳይሆን ቀደም ብሎም ይታወቅ ነበር›› ይላሉ፡፡ እንደ ችግር መታየት የጀመረው ግን ኋላ ላይ ነው፡፡ ለማስተካከል ብዙም ያልተሞከረው ምናልባት ‹‹ባለ4 መኝታ›› ቤቶቹ ለድርጅት ሰዎች ለመስጠት እንዲያመች ይሆን ወይ ተብለው ከዋዜማ የተጠየቁት እኚህ የግንባታ ክትትል ባለሞያ ‹‹አይመስለኝም›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹…መስተዳደሩ በዚህ ደረጃ ነዋሪውን ሆን ብሎ ያጭበረብራል ብዬ አላምንም፤ ምናልባት በመሥሪያ ቤቶች መካከል አለመናበብ የተከሰተ ይመስለኛል፣ ያን ለመሸፈን እንደማምለጫ የተጠቀሙበት ነገር ነው የሚሆነው›› ይላሉ፡፡

‹‹የዲዛይን ችግሩን››ተከትሎ ‹‹የባለ 3 መኝታ ቤት›› ቆጣቢዎችየባለ 4 መኝታ ቤቶችን የማይወስዷቸው ከሆነ መስተዳደሩ ሙሉ ክፍያ ፈጽሞ ቤቶቹን ለራሱ እንደሚያስቀራቸው በይፋ መግለጹ ይታወቃል፡፡

ቤቶቹ ለምን በውሉ መሠረት ሳይገነቡ ቀሩ ለሚለው ጥያቄ በቤት ቆጣቢዎች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥረው የነበሩት እነዚህ መንግሥት ‹‹ባለ 4 መኝታ›› ቤቶች እያለ የሚጠራቸው ቤቶች ከኔ እውቅና ውጭ በዲዛይን ስህተት የተፈጠሩ ናቸው ቢልም ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑት እኚህ የዋዜማ ምንጭ ግን ይህ ነጭ ውሸት እንደሆነ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡

‹‹…ምን መሰለህቤቶቹ ንግድ ባንክ ውል ከማዘጋጀቱ በፊት ግንባታቸው ተጀምሮ ነበር፡፡ ቆጣቢዎች ከፈጸሙት ውል ጋር የሚቃረኑ የሆኑት ግን በመስተዳደሩ እንዝላልነት እንጂ በዲዛይን ስህተት አልነበረም፡፡››ካሉ በኋላ፣ ‹‹…እውነት ለመናገርአሁንም ቢሆን ‹‹ባለ 4 መኝታ›› የሚባል ቤት አልተገነባም፡፡ የሆነው ምንድነውኦሪጅናል ዲዛይኑ ላይም ማየት እንደሚቻለው ሁሉም ቤቶች አንዲት ጠበብ ያለች ዕቃ ቤትና የሠራተኛ ማረፊያ (Maid’s Room) እንዲኖራቸው ተደርገው ነው የተዘጋጁት፡፡ ኪችንና ሽንት ቤትን እንደ ወጥ ክፍል እንደማትቆጥረው ሁሉ በዲዛይን ቋንቋ ዕቃ ቤትና የሠራተኛ ማረፊያ እንደ መኝታ ቤት መቁጠር የተለመደ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው በሁለቱም ሳይቶች ላይ ባለ አንድ መኝታ፣ ባለ ሁለትና ባለሦስት መኝታ አፓርታማ ቤቶች የየራሳቸው ተጨማሪ ክፍሎች የተገነቡላቸው፡፡ ይቺን ካሬ የማትሞላ የሠራተኛ ማረፊያ ክፍል ምክንያት አድርገው ነው ቆጣቢውን እያወናበዱት ያሉት›› ይላሉ፡፡ በዚህ የተነሳ የባለ አንድ መኝታ ቤት ቆጣቢዎች ከውድድር ውጭ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

ያም ኾኖ የቤቶቹ ስፋት ከውል ውጭ መሆኑን ባለሞያው አልካዱም፡፡ ‹‹…እውነት ነውባንካችን ከቆጣቢዎች ጋር ከገባው ውል አንጻር የቤቶቹ ካሬ ሰፋ ብሏል፡፡ እንጂ በዲዛይን ስህተት ባለ 4 ክፍል መኝታ ተገነባ የሚባለው በፍጹም የተሳሳተ ነው፡፡ እኛ ያቀረብነው ሐሳብ ሁሉም ውል ፈጻሚ ባለ አንድ መኝታ ተመዝጋቢዎችን ጨምሮ ማለቴ ነው በገባው ውል መሠረት እኩል ይወዳደር፣ የካሬ ሜትሩን ስፋት የተራዘመ ጊዜ ተሰጥቷቸው እንዲከፍሉ ይደረግ›› የሚል ነበር፡፡ መስተዳደሩ ግን ለምን እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ ችግሩን በዲዛይን አሳቦ የባለ አንድ መኝታ ተወዳዳሪዎችን ከጨዋታ ውጭ ማድረጉ አግባብ እንዳልነበረም በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

ቤቶቹ ከመመረቃቸው በፊት ከንግድ ባንክና ከመስተዳደሩ ቤቶች ልማት ጋር የነበሩ ውይይቶቹን ያነሱት ባለሞያው ‹‹እኛ ያላለቁ ቤቶችን አንረከብም፣ ከውል ውጭ ቆጣቢዎችን የተጋነነ ክፍያ አንጠይቅም የሚል አቋም ይዘን ቆይተን ነበር ይላሉ፡፡

‹‹የቤቶቹን የካሬ ስፋት ከውሉ ጋር መቃረኑን ተከትሎ ምን ቢደረግ ይሻላል?›› በሚል ቤቶቹ ከመመረቃቸው ቀደም ብሎ ተከታታይ ውይይቶች አካሄደናል ያሉት እኚህ የዋዜማ ምንጭ የንግድ ባንክ ተወካዮች የውል ማሻሻያ እንዲደረግ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን ምክትል ከንቲባው አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው ውል ብናሻሽል ለትችት እንዳረጋለን፣ የቤት ሥራቸውን በትትክል አልሰሩም ነው የምንባለው፣ ከዚህ ይልቅ ባለ አንድ መኝታዎችን ከውድድር ብናወጣቸው ነው የሚሻለው፣ ሌሎቹን ካሬ ጨመርንላቸው እንጂ አልቀነስንም፣ ቤቱ ሰፋብኝ ብሎ መዋዋል ያልፈለገ መብቱን እናከብርለታለን፤ እኛም የቤት እጥረት አለብን እኮ፣ የሚተርፉትን ቤቶች ተረክበን ለአመራሮቻችን እንሰጣቸዋለን›› ሲሉ በአንድ የውስጥ ስብሰባ መናገራቸውን እንደሚያውቁና በኋላም በዚሁ ጉዳይ ላይ የተናጠል ውሳኔ መወሰናቸውን ያስታውሳሉ፡፡

‹‹እርሳቸው የሚመሩት ተከታታይ ስብሰባ ነበር የሚደረገው፡፡ ምን ያህል ዋጋ ጭማሪ እናድርግ? የቤቶቹ ስፋት ካሬ መጨመሩ ክፋት ባይኖረውም ከውል ውጭ መሆኑ ሊያስተቸን ይችላልና ምን ብናደርግ ይሻላል በሚሉ ነጥቦች ላይ ስብሰባ ተካሄዷል፡፡ አንድም ቤቶቹ ላይ በጊዜ ዕጣ ማውጣት ያልተቻለው በነዚህ አለመግባባቶች ምክንያት ነበር፡፡ በዲዛይን ችግር የተነሳ የመኝታ ቤት ቁጥር ጨምሯል በሚል ማስተባበያ ሰጥተን ቤቶቹን ለኛው እናስቀራቸው የሚል ነገር የመጣው ግን ኋላ ላይ ነው፡፡›› ይላሉ ባለሞያው፡፡

ዋዜማ 40/60 ቤቶች የመጀመርያ ዲዛይን ቅጂ ያገኘች ሲሆን የወለል ፕላኑ እንደሚያመለክተው 12 ፎቆች የሚረዝሙት ሕንጻዎች 10 ወለሎቹ ተመሳሳይ አቀማመጥን የሚከተሉ በወለል 6 አባወራዎችን ብቻ የሚይዙ እንደሆኑ ለመረዳት ችላለች፡፡ በእያንዳንዱ ወለል ሁለት ባለ አንድ መኝታ፣ ሁለት ባለ ሦስት መኝታ እና ሁለት ባለ አንድ መኝታ ክፍሎችም ይገኛሉ፡፡ ሁሉም ክፍሎች ዕቃ ክፍልና የሠራተኛ ማረፊያን ያካትታሉ፡፡ እያንዳንዱ ሕንጻ ሁለት ሊፍቶች የተገጠሙለት ሲሆን የቆሻሻ መወርወርያ (ጋርቤጅ ሹተር) እንዲሁም የአደጋ ጊዜ መውጫ ደረጃዎችንም ተነድፈውለት ነበር፡፡

በሁለቱም ሳይቶች በድምሩ 19 ሕንፃዎች ተገንብተዋል፡፡ ሕንፃዎቹ መጀመርያ ጊዜ ሊገነቡ የነበረው ባለ አንድ መኝታ ቤት 55 ካሬ ሜትር፣ ባለ ሁለት መኝታ ቤት 75 ካሬ ሜትርና ባለ ሦስት መኝታ ቤት 100 ካሬ ሜትር የነበረ ቢሆንም፣ በተደረገው የዲዛይን ለውጥ ካሬ ሜትሮቹ ተቀይረው፣ ባለ ሁለት መኝታ ቤት 124.97 ካሬ ሜትር፣ ባለ ሦስት መኝታ ቤት 150.09 ካሬ ሜትርና ባለአራት መኝታ ቤት 168.6 ካሬ ሜትር ስፋት እንዲኖራቸው ሆኗል፡፡

ባለ አራት መኝታ የተባሉትን ቤቶች ምናልባት በየዓመቱ ለመንግሥት ሹሞች ከፍተኛ የቤት ጥያቄ እየቀረበለት ማስተናገድ ያልቻለው የቀድሞው የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ በግዢ ሊረከባቸው እንደሚችል ይገመታል፡፡ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በቅርቡ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ኾኖ እንደ አዲስ ከተዋቀረ ወዲህ ከማዕከልና ከክፍለ ከተማ የሚገኙ ባለሞያዎችን በከፍተኛ ወርሃዊ ደመወዝ እየወሰደ ይገኛል፡፡ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮም በቤቶች ግንባታ ዘርፍ ለመሠማራት ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ ለጊዜው በሰንጋ ተራና በክራውን ውል ያልተፈጸመባቸውን ቤቶች በቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ በውል ባይለይም ከመጪው ዓመት የከተማዋ ምርጫ በኋላ ለሚሾሙ መካከለኛ ካድሬዎች እነዚህን ቤቶች እንዲወስዷቸው እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡