youthዋዜማ ራዲዮ- ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት የወጣቶችን ፍላጎት የሚያረኩ ፖሊሲዎችን ተግብሬ የወጣቱን ችግር ደረጃ በደረጃ እየቀረፍኩ ነው በማለት ደጋግሞ ቢገልጽም መርሃ ግብሮቹ ግን እንዳሰበው ውጤታማ አልሆኑለትም፡፡ ከወጣቱ ጋር ያለው ግንኙነትም ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡ ባለፈው ዓመት በተቀጣጠለው ህዝባዊ አመጽ ተሳታፊ የሆኑት ባብዛኛው በዘመነ-ኢህአዴግ የተወለዱ ወጣቶች መሆናቸውም አንዱ ማሳያ ነው፡፡ አመፁን ተከትሎም ከ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ ጀምሮ ሲተገብረው የኖረውንየወጣቶች ፖሊሲ እና ዕድገት መርሃ ግብሩ መከለስ መጀመሩን ባለፈው መስከረም አስታውቋል፡፡ በመጭዎቹ አምስት ዓመታት ለስራ ዕድል ፈጠራ የሚውል አስር ቢሊዮን ተንቀሳቃሽ ገንዘብ መመደቡንም ይፋ አድርጓል፡፡

 ይሁንና አሁንም ወጣቶችን በፖለቲካዊ ቁጥጥር ስር ለማዋል በሚያስችል አደረጃጀት የሚጠረንፈው ገዥው ፓርቲ እና ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት መርሃ ግብሮቹን ከወጣቱ ቁልፍ ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች ጋር ለማጣጣም ይፈቅዳሉን? መንግስት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለሚተገብረው ዕቅዱ የሚፈለጉት የአሰራር ለውጦች ከገዥው ድርጅት መሰረታዊ ነባር መርሆች ጋር ይጣጣማሉን? መንግስትስ ወጣቱ አሉብኝ የሚላቸውን በነጻነት የመደራጀት እና ሌሎች የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን በቅን ልቦና ተረድቶ መፍትሄ ለመስጠት ዝግጅት አለውን? የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ግድ ይላል፡፡ ቻላቸው ታደሰ ጉዳዩን በዝርዝር ተመልክቶታል

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት በህዝባዊ አመፁ በታዩት ግጭቶች ዋነኛ ተሳታፊዎቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ መንግስት ለወጣቶች ሰላማዊ ተቃውሞ የሰጠው ከመጠን ያለፈ የሃይል ምላሽ እና ርምጃውን ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም በመንግስት እና ወጣቶች መካከል ስር ሰዶ የቆየውን ሸካራ እና ጥርጣሬ የተሞላበት ግንኙነት ክፉኛ እንዲያሽቆለቁል እንዳደረገው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አዋጁን ለማስፈፀም የተቋቋመው ማዘዣ ጣቢያም በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ካሰራቸው ከ20 ሺህ በላይ ዜጎች መካከል አብዛኛዎቹ ወጣቶች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ በቅርቡ ግን የአሜሪካ መንግስት ልዑካን መንግስት ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን እንዲወስድ ለመገፋፋት ባለፈው ሳምንት አዲሳባ በገባ ማግስት ግን ማዘዣ ጣቢያው ዘጠኝ ሺህ ያህሉን እስረኞች ሊለቅ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ወጣቶች ለኢህአዴግ ምን አሉት?

የወጣቶች አመጽ የመንግስትም ሆነ የሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት በወጣቶች ወቅታዊ ሁኔታ እና ዕጣ ፋንታ የሚወሰን መሆኑን ለመንግስት በቂ መልዕክት አስተላልፏል ማለት ቢቻልም መንግስት ግን እስካሁን በተግባር ወሳኝ ማሻሻያዎችን ሲወስድ አልታየም፡፡ የታየ ለውጥ ቢኖር ብሄራዊ የወጣቶች ፖሊሲ እና ዕድገት መርሃ ግብሩን መከለሱ እና ለስራ ዕድሎች ፈጠራ የአስር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ በጀት መመደቡ ብቻ ነው፡፡

መንግስት ክለሳው ያስፈለገው በኢኮኖሚ ዕድገቱ ሳቢያ የወጣቶች አዳዲስ የኢኮኖሚ ፍላጎቶች በመፈጠራቸው መሆኑን ይገልፃል፡፡ ቀደም ብለው ያልታዩ ዘርፎችን ለማካተት እና የአፈፃፀም ጉድለቶችን ለማሻሻል ተፈልጎ መሆኑ ላለፉት ሁለት ወራት እየገለጸ ይገኛል፡፡ ከሆነ ባሁኑ ሰዓት በክለሳ ላይ ያለው መርሃ ግብር ወጣቶች በልማት እና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ለሚኖራቸው ተሳትፎ ትልቅ ትኩረት እንደሰጠ ተነግሮለታል፡፡ በነባሩ ፖሊሲ ትኩረት ተነፍጓቸው የነበሩት እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን መስመር ዝርጋታ እና ዕድሳት፣የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማስፋፋት እና የቀላል ኢንዱስትሪ ልማት የመሳሰሉ ዘርፎች ትኩረት አግኝተዋል፡፡ የወጣቶች ህገ ወጥ ዝውውር፣ ስደት፣ የባህል ወረራ፣ አደንዛዥ እፅ፣ የሰላምእሴት ግንባታ፣ የትውልድ ቅብብሎሽ ክፍተትን ማጥበብ የመሳሰሉት ጉዳዮችም በክለሳው ልዩ ትኩረት ያገኙ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

በተለይ ስደት ላይ ትኩረት ማደረጉ የዘገየ ቢሆንም በበጎ ጎኑ የሚታይ ነው፡፡ በጎረቤት ሱዳን እና ኬንያ በኩል ስራ ፍለጋ ወደአውሮፓ እና ደቡብ አፍሪካ የሚሰደዱ ወጣቶች ቁጥር በየጊዜው ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም፡፡ በቆዳ ስፋቱ ትንሹ ከሆነው የሐረሬ ክልል ብቻ በስድስት ወራት ውስጥ 10 ሺህ ወጣቶች በህገ ወጥ መንገድ ሊወጡ ሲሉ መያዛቸው በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ መገለፁ ይታወሳል፡፡ ባለፈው ሰኔ የአውሮፓ ህብረትም የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ እና ደቡብ ክልሎች የወጣቶችን ፍልሰት ለመግታት የሚያስችሉ የስራ ዕድሎችን እንዲፈጥር ለማገዝ ለአራት ዓመታት የሚዘልቅ የ20 ሚሊዮን ዩሮ ዕርዳታ አፅድቋል፡፡

መንግስት በዋናነት ከፖሊሲው ከሽፋውብኛል የሚላቸው ግቦች ፍትሃዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን እና ስራ አጥነትን መቅረፍ ናቸው፡፡ በህዝባዊ አመፁ ማግስት ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግርም ወጣቶች ለሁከት የተዳረጉት መርሃ ግብሩ የስራ ዕድል ፈጠራ ፍላጎታቸውን ማርካት ባለመቻሉ ቅሬታ ተሰምቷቸው እንደሆነ ነበር ያሰመሩበት፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩም በተደጋጋሚ የተናገሩት ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ እንዲያውም መንግስት በዚህ ሳይወሰን በውጭ ያሉ አክራሪ ሃይሎች ወጣቱን ነዳጅ እና ክብሪት አስታጥቀው የሁከት መሳሪያ አድርገውታል በማለት የወጣቶችን ድርብርብ ብሶት ውጫዊ ገጽታ ጭምር ሰጥቶታል፡፡

ከአባላት ውጪ- ወደ ውጪ!

ከመንግስት አንደበት የሚሰሙት ዜናዎች ወጣቶች በነጻነት መደራጀት አለመቻላቸውን፣ በመገናኛ ብዙሃን ያለቸው ሽፋን አናሳነት እና በዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር እና በውሳኔ ሰጭ ተቋማት ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን እንደ ቁልፍ ችግር አምነው የተቀበሉ አይመስሉም፡፡ መንግስት አሁንም የወጣቶች ዋነኛ ጥያቄ እና ችግር ኢኮኖሚያዊ መሆኑን በፅኑ ያምናል፡፡ የወጣቶች የመደራጀት ነፃነት እና ሌሎች የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በቂ ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ብዙ አመላካቾች አሉ፡፡ ለዚህ አካሄድ ዋነኛው ምክንያት ገዥው ፓርቲ የሚከተለው የወጣቶች አደረጃጀት በመንግስት የተነደፈው የወጣቶች መርሃ ግብር ካስቀመጣቸው ግቦች እና ስትራቴጂዎች ጋር የማይጣጣም በመሆኑ እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡ በርግጥ የወጣቶች የዕድገት መርሃ ግብር የወጣቶችን በነጻ መደራጀት ዋናው ምሰሶው መሆኑን ቢጠቅስም በተግባር ገናና ሆኖ የሚታየው ግን የፓርቲው የወጣት አደረጃጀት ነው፡፡

ኢህአዴግ በወጣት አደረጃጀት ላይ ፖለቲካዊ ቁጥጥርን ግባቸው ያደረጉ ሁለት ስልቶችን ሲከተል የኖረው፡፡ አንደኛው ስልት በፓርቲው ስር እስከ ቀበሌ መዋቅር ያላቸውን የወጣት ሊጎች ማቋቋም ነው፡፡ የወጣት ሊጎቹ የተዋቀሩት አባላቱ ደሞ የገዥው ፓርቲ አባላት ወይም ደጋፊዎች እንዲሆኑ ተደርጎ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ዩኒቨርስቲ የሚገቡ አብዛኛዎቹን ተማሪዎች በመመልመል የፓርቲ አባልነት መታወቂያ ያድላቸዋል፡፡ ከዚያም በየዩኒቨርስቲው ባሉት ብሄርን መሰረት ባደረጉ የመሰረታዊ ድርጅት መዋቅሮች ስር በህዋሶች ይታቀፋሉ፡፡

ሌላኛው ስልት ደሞ ስራ አጥ ወጣቶችን በአንሰተኛ እና ጥቃቅን ማህበራት አደራጅቶ የብድር አገልግሎት አቅራቢ በመሆን ፖለቲካዊ ቁጥጥሩን ማጥበቅ ነው፡፡ በጥቃቅን ማህበራት ተደራጅቶ ከመንግስት ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማግኘት ደሞ የወጣት ሊግ አባል መሆን እንደ መስፈርት ይወሰዳል በማለት ወጣቶች ያማርራሉ፡፡

በጠቅላላው ከወጣት ሊግ አደረጃጀት እና ከጥቃቅን ማህበራት ውጭ ያለው ወጣት ከፍትሃዊ ውክልና እና ተጠቃሚነት የተገለለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በገዥው ፓርቲ የቁጥጥር ፖሊሲ ሳቢያም ሀገር ዓቀፍ ጠንካራ ነጻ የወጣት ማህበራት ማበብ አልቻሉም፡፡ ጥቂቶች በነፃነት ለመደረጃት የሞከሩም ከመንግስት እና ገዥው ድርጅት በሚቃጣባቸው በትር ተሸመድምደው መፈራረሳቸው ዓሊ የሚባል አይደለም፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ በሚለኒዬሙ በዓል ማግስት ከሦስት ሺህ በላይ ወጣቶችን ባንድ አዳራሽ ኮልኩለው “ዋናው ነገር ያልተደራጀ ወጣት አይኑር” ማለታቸው የኢህአዴግን ወጣቶችን በራሱ ዙሪያ ለማደራጀት ያለውን አባዜ ያመላከተ ነበር፡፡ ያንኑ አካሄድ የተከተሉት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያምም ባለፈው ነሐሴ ተመሳሳይ ቁጥር ካላቸው ከየክልሉ እና ከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር ያደረጉት ውይይት የወጣቶችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ወደጎን ገሸሽ ያደረገ ነው ተብሎ በታዛቢዎች ተተችቷል፡፡ ወጣቶቹም ቢሆኑ ሀገሪቱ በገጠማት ቀውስ ላይ መሰረታዊ ጥያቄዎችን አላነሱም፡፡ ይህም ወጣቶቹ ያላባቸውን የአደረጃጀት ነፃነት ጉድለት፣ ተወክለው የመጡበትን ፖለቲካዊ መስፈርት እና መድረኮቹ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚፈለጉ መሆናቸውን ቄልጭ አድርገው ስለማሳየታቸው ሌላ አብነት መጥቀስ አያሻውም፡፡

የኢህአዴግ ርዕዮተ ዓለም ልሳን በሆነችው አዲስ ራዕይ መፅሄት በቅርቡ የወጣ አንድ ሃተታ ግን ኢህአዴግ ባለፉት ጊዚያት ብዙሃን ማህበራት በነፃ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ በኩል ድክመት እንደነበረበት አምኗል፡፡ ድርጅቱ አሰራሩን በመገምገም ማህበራት በነፃነት እንዲደራጁ እና እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርጉ አዳዲስአቅጣጫዎችን ማስቀመጡም ተገልጧል፡፡ ስለዚህ አዲሱ አቋም ባንድ በኩል ድርጅቱ በወጣት አደረጃጀት ላይ እስካሁን ሲከተለው የነበረው ፖሊሲው መክሸፉን ማመኑን ይጠቁማል፡፡ በሌላ በኩል ደሞ ኢህአዴግ ህዝባዊ አመፁን ተከትሎ በመደረጃት ነጻነት ላይ ያለውን ፖሊሲውን እንደገና መፈተሽ መጀመሩን ያሳያል፡፡ ይሄ የአቋም ለውጥ ግን በመንግስት በአደባባይ ለመተግበር ዝግጅት ስለመኖሩ የሚጠቁሙ ምልክቶች አይታዩም፡፡

አዲስ ራዕይ የሰሞኑ ሃተታ ከዚሁ ጋር አያይዞ “ለወጣቶች የሚሰጠው የስነ ዜጋ ትምህርት እና መገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ አንድነትን እና ብሄራዊ ስሜትን በመፍጠር ረገድ አሉታዊ ሚና መጫወታቸውን ኢህአዴግ ይቀበላል” ሲል ያተለመደ አቋም አንፃባርቋል፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች የብሄርተኝነት ስሜቶችን እያጎለበቱ መምጣታቸው ግን ለራሱም ስልጣን አደጋ መሆኑን የተረዳ ይመስላል፡፡ ለዚህም ይመስላል ወጣቱን በብሄር አደረጃጀት ከፋፍሎ፣ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን እያናናቀ ሲሰብክለት ከኖረ በኋላ በያዝነው ዓመት መባቻ ላይ ወጣቱ ትውልድ ብሄራዊ ስሜት እንዲያዳብር በመገናኛ ብዙሃኑ ሳይቀር ቅስቀሳ ማድረግ የጀመረው፡፡ ኢህአዴግ ይሄን የሚለው ለጊዚያዊ መተንፈሻ ይሁን ለመሰረታዊ የአቋም ለውጥ ለጊዜው ማወቅ ቢያስቸግርም ብሄርተኝነትን ለጊዜው ለማዳከም አስቦ ሊሆን እንደሚችል ግን ጠንከር ያሉ ግምቶች አሉ፡፡

በኢትዮጵያ በወጣቶች ፖሊሲ እና ዕድገት መርሃ ግብር የወጣት ዕድሜ ክልል ተብሎ የተቀመጠው ከ15 እስከ29 ያለው የዕድሜ ክልል ነው፡፡ ከሀገሪቱ ጠቅላላ ህዝብ ብዛት ውስጥ በዚህ የዕድሜ ክልል የሚገኘው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ደሞ 28 ሚሊዮን እንደሚገመት የስነ ህዝብ መረጃው ያሳያል፡፡ ከዘጠና ሁለት ሚሊዮን ህዝብ 70 በመቶው ከሰላሳ ዓመት ዕድሜ በታች የሚገኝ ወጣት ነው ማለት ነው፡፡

ስራ አጥነት ሲብስ እንጂ ሲቀንስ አልታየም

ከመንግስት ተቋማት የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከዚህ የወጣቶች ቁጥር መካከል ባሁኑ ወቅት 77በመቶ የሚሆነው ከተሜ ወጣት ስራ አጥ ነው፡፡ በክለሳ ላይ ያለው የወጣቶች ፖሊሲ እና ዕድገት መርሃ ግብር ሲተገበር ግን በፌዴራል ደረጃ ብቻ 75 ከመቶ ወይንም ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ለሚሆኑ የከተማ ወጣቶችየሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ እጅግ የተጋነነ ነው የተባለለትን ትንበያውን አስቀምጧል፡፡ መንግስት ግን አሁንም ስራ አጥነትን ለመቅረፍ ብድር እንዲያቀርቡለት ተስፋውን የጣለባቸው ካሁን በፊትም የነበሩት የጥቃቅን እና አነስተኛ ብድር ተቋማት፣ ልማት ባንክ እና መደበኛ ባንኮች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ግን ነባሩ ፖሊሲ በተፈለገው ደረጃ ያልተሳካው እነዚሁ ተቋማት ባለባቸው የብድር አቅርቦት እጥረት እና የቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት መሆኑን መንግስት አምኗል፡፡ እናም አሁንም መሰረታዊ ተቋማዊ እና የአሰራር ለውጥ ሳይደረግ የታሰበው ዕቅድ እንደምን እንደሚሳካ ግልፅ አይደለም፡፡

ኢህአዴግን በቅርብ ያጠኑ ምሁራን እንደሚሉት የድርጅቱ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መርሆ እና የልማታዊ መንግስት ፖሊሲው ተዳምረው ለነጻ የወጣት አደረጃጀቶች እና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች እና ሁለንተናዊ ፖለቲካዊ ተሳትፎዎች ድንጉጥ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ በዚህ ባሪው ሳቢያ የወጣት ማህበራት ብቻ ሳይሆኑ በጠቅላላው ሲቪል ማህበራት ተዳክመዋል፡፡ የሲቪል ማህበራት እና የግሉ ዘርፍ የስራ ዕድል የመፍጠር አቅማቸውም ክፉኛ መመናመኑ በበርካታ ጥናቶች የተረጋገጠ ሃቅ ነው፡፡ መንግስት ስራ አጥነትን መቅረፍ ጨምሮ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ፍላጎቶች ማሟላትን ከሞላ ጎደል በብቸኝነት ተሸክሞታል ለማለት ያስደፍራል፡፡ የፖለቲካው ብቻ ሳይሆን የማህበራዊው እና ኢኮኖሚያዊው ምህዳር በዋናነት ያለቅጥ በተለጠጠው የመንግስት መዋቅር መያዙ አደገኛ አካሄድ መሆኑን ፕሮፌሰር ሳራ ቮግ እና ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ክላፋም በጥናቶቻቸው ደጋግመው ተችተውታል፡፡ መንግስት ግን ከአቋሙ ዝንፍ አላለም፡፡

ወጣቶችና ኢህአዴግ – መች ይተዋወቁና!

በጠቅላላው ከህዝባዊ አመፁ በኋላም መንግስት እና ወጣቱ አንድ ቋንቋ እየተናገሩ ያሉ አይመስልም፡፡ በወጣቶች የተመራው ደም አፋሳሽ ህዝባዊ አመፅ በመንግስት በኩል ያመጣው መሰረታዊ ለውጥ የለም፡፡ አሁንም መንግስት የወጣቶች ጥያቄ ከሥራ አጥነት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መጓደል ጋር ብቻ የተያያዘ ነው በሚለው ግንቤው ገፍቶበታል፡፡ መንግስት በወጣቶች አደረጃጀት ነፃነት እና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዙሪያ ለሚነሱት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይቅርና ገና በቂ ዕውቅና እንኳን ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ የወጣቶች በነጻነት የመደራጀት እና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ሳይከበሩላቸው ኢህአዴግ-መራሹ እንደምን ስራ አጥነትን እንደሚቀርፍ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሰፍን ለመረዳት ያስቸግራል፡፡ አዲሱን የስራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ ከዴሞክራሲያዊ መብቶች ነጥለን ብናየው እንኳ መንግስት አሁንም የተማመነው በየደረጃው ያሉ የመንግስት እና የፓርቲ አመራሮች በጥልቀት ስለታደሱ የወጣቶችን መሰረታዊ ችግሮች በአፋጣኝ እቀርፋለሁ በሚለው የተለመደው ፕሮፓጋንዳው ላይ ብቻ ነው፡፡