(Photo by Hassan Ali ELMI / AFP)

ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ የምትልከው ጫት ከወራት በፊት በእጥፍ እንዲጨምር ተደርጎ ነበር። አሁን ዋጋው ቀድሞ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ትዕዛዝ መተላለፉን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከሁለት ቀናት በፊት ለሁሉም ባንኮች በበተነው ደብዳቤ መሰረት ወደ ሶማሊያ የሚላክ የጫት ምርት በኪሎ ግራም ይከፈል የነበረው 10 የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ወደ አምስት ዶላር ዝቅ ዝቅ እንዲል መወሰኑን ገልጿል።

ማዕከላዊ ባንኩ ከንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጥር ወር ላይ በተጻፈለት ደብዳቤ ወደ ሶማሊያ የሚላከው ጫት ከ5 የአሜሪካ ዶላር ወደ 10 የአሜሪካ ዶላር ሆኖ ሲላክ እንደነበር ጠቅሶ ፣ ሐምሌ 6 ቀን 2014 ዓ.ም በድጋሜ ከሚኒስቴሩ በተላከ ደብዳቤ ወደ ሶማሊያ የሚላከው ጫት ዋጋ በኪሎ ግራም ወደ አምስት የአሜሪካ ዶላር ዝቅ እንዲል መወሰኑንና ባንኮችም ይህን እንዲያስፈጽሙ ሲል በደብዳቤው አሳውቋል።

ወደ ሶማሊያ የሚላከው ጫት ዋጋ ቀድሞ ወደነበረበት እንዲመለስ የተወሰነው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በጉዳዩ ላይ ከመከሩበት በኋላ ነው ተብሏል። 

ከጥር 2014 ዓ.ም በኋላ ሲተገበር የነበረው የጫት ዋጋ ለጊዜው ቀርቶ በሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ውሳኔ እስኪተላለፍ ድረስ ወደ ሶማሊያ የሚላክ ጫት በኪሎ ግራም 5 የአሜሪካ ዶላር እንዲሸጥ መወሰኑን የብሄራዊ ባንኩ ደብዳቤ ያሳያል።

ሶማሊያ ዋነኛ የኢትዮጵያ የጫት ምርት ተቀባይ ስትሆን ፣ ጫትም የኢትዮጵያ ቀዳሚ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ነው። በበጀት አመቱ 11 ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የጫት ምርት 372 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህም ምርቱን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ከሚያስገኙት ውስጥ አራተኛ ደረጃን ያሰጠዋል።

በዚህ አመትም መንግስት ለ40 አመታት ስራ ላይ የነበሩ የጫት ንግድ አሰራሮችንና ዋጋን ማስተካከሉ ለገቢው ማደግ በምክንያትነት ይጠቀሳል።የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየውም በዚህ አመት ጫት የወጪ ንግድ አፈጻጸሙ 90 በመቶ ነው።አሁን አዲስ የተደረገው የዋጋ ማሻሻያ ገቢው ላይ ተጽእኖ ሊያሳርፍ ይችላል።

በኢትዮጵያ 4.1 ሚሊየን ገበሬዎች እንደሚሳተፉበት በሚነገረው የጫት ምርት ባለፈው አመት 3.1 ሚሊየን ኩንታል እንደተገኘ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን ምርቱም በኢትዮጵያ 340 ሺህ ሄክታር ይሸፍናል። ኦሮምያ ክልል ቀዳሚ የጫት አምራች ክልል ሲሆን ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ እና ሲዳማ ክልሎች ይከተላሉ። [ዋዜማ ራዲዮ]