ዋዜማ ራዲዮ- የግዥ መመርያን በመተላለፍ እና የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከተቋቋመበት አላማ ውጭ 2 የንግድ መርከቦችን በመግዛት ከ544 ሚሊዮን ብር በላይ በህዝብ እና በመንግበስት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲል በ14 የቀድሞ የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ላይ አቃቤ ህግ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወቃል፡፡

ከእነዚህም 3ቱ በዚህ ሳምንት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ክሳቸውን ካቋረጠላቸው መሀከል ናቸው፡፡

የኮርፖሬሽኑ የቀድሞ ዋና ስራ አስኪያጅ ሜ/ጀነራል ክንፈ ዳኘው እና ቀሪ ተከሳሾች ደግሞ አቃቤ ህግ ያስቆጠረባቸውን ቀሪ 3 ምስክሮች ለመስማት ረቡዕ ረፋድ ላይ ጉዳያቸውን በሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ተሰመው ነበር፡፡

ሆኖም 2 ምስክሮች በተመለከተ ፖሊስ አፈላልጎ ማግኘት እንዳልቻለ 3ኛው ምስክር ደግሞ ባስመዘገበው አድራሻ ማይኖር መሆኑን ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ ገፅዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ከሳሽ አቃቤ ህግ በወንጀለኛ መቅጫ የስነስርዓት ህጉ አንቀፅ 145(2) መሰረት ምስክሮች ከዚህ ቀደም ለፖሊስ የሰጡትን ቃል ፍርድ ቤቱ ይያዝልኝ ጠበቆችም ግልባጩን ወስደው አስተያየት እንዲሰጡበት ይሁን ሲል ጠይቋል፡፡

ጠበቆች በበኩላቸው ለተከሳሾች ህግመንግስቱ የሰጣቸውን ምስክሮች እና ማስረጃዎችን የማየት እና የማወቅ መብት የሚፃረር ነው ሲሉ ተከላክለዋል፡፡

አክለውም በፖሊስ ጣቢያ ያለ ከባቢ ምስክሮች ላይ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል የሚገመት ነው ያሉ ሲሆን በፍርድ ቤት ቀርበው በቃለ መሀላ መመስከራቸው እውነታ እንዳለ ያሳያል የእነሱ ቃል ስለመሆኑ ማረጋገጫ በሌለበት ከዚህ ቀደም የሰጡት ቃል ተያይዞ መምጣቱ ግን ፍትህን እና የተከሳሾችን የመከላከል መብት የሚጋፋ ነው በማለት ውድቅ እንዲሆንላቸው ጠይቀዋል፡፡

ችሎቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ ትዕዛዙን መክሮ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ተፈልገው ያልተገኙት ሁለት ምስክሮችን ውድቅ አድርጓል፡፡

ባስመዘገበው አድራሻ ነዋሪ አይደለም የተባለው ምስክር ከዚህ ቀደም ለፖሊስ የሰጠው ቃል ግን በማስረጃነት እንዲያያዝ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

ጠበቆች ግልባጩን ወስደው አስተያየት ስጡበት የተባለ ሲሆን ችሎቱ በማስረጃዎች ላይ ብይን ለመስጠት ለሚያዝያ 2 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡[ዋዜማ ራዲዮ]