Photo Credit- Fortune

[ዋዜማ ራዲዮ] የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ ቀድሞ ከነበረው የሜዲካል ኦክስጅን ፍላጎት አሁን እየጨመረ መምጣቱን እና እጥረት መከሰቱ የህይወት ማዳን ስራውን ፈታኝ አድርጎታል።


ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት አጠቃላይ ሀገሪቱ 850 ኪውቢክ ሜትር ኦክስጅን በሰዓት ይመረት እንደነበር ዋዜማ ከጤና ሚኒስትር ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡


ሆኖም ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በቀን ውስጥ በፅኑ የሚታመሙ ሰዎች ቁጥር 1,300 ቢደርስ በሰዓት 3,200 ኪውቢክ ሜትር ኦክስጅን ማምረት እንደሚያስፈልግ ተንብዮ እና አቅዶ እንደነበር የኮቪድ 19 ምላሽ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሚዛን ኪሮስ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡


“ኦክስጅን አየር ላይ ያለ እና ሰዎች እንደፈለጉት ወደሰውነታቸው ሊያስገቡት የሚችሉት ቢሆንም እንደ ኮሮና ቫይረስ ያሉ ሳንባን የሚያጠቁ በሽታዎች ሲከሰቱ በፅኑ የሚጎዱ ህሙማን የሚያስፈልጋቸውን ያህል ኦክስጅን አጣርተው ወደ ሰውነታቸው ማስገባት ይቸገራሉ፡፡ ለዚህም ነው ሰው ሰራሽ እገዛ የሚፈልጉት” ይላሉ ዶ/ር ኪሮስ፡፡


የታቀደው ቁጥር በሰዓት ከ3ሺህ ኪውቢክ ሜትር በላይ ቢሆንም ባለፈው 1 አመት ሲመረት የነበረው ግን በሰዓት 1, 850 ኪውቢክ ሜትር መሆኑንም አክለዋል፡፡


ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ እነ ቅዱስ ጳውሎስ ያሉ ማዕከላትን ጨምሮ 33 የኦክስጅን አምራቾች ያሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 93 በመቶ ያህሉ የግል አምራቾች ናቸው፡፡


ይሁን እንጂ ከእነዚህ ውስጥ በስራ ላይ ያሉት 20ዎቹ ሲሆኑ በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ ያሉት የተወሰኑት ብቻ መሆናቸውን ዶ/ር ሚዛን ለዋዜማ አስረድተዋል፡፡


ባለፉት ሳምንታት ለተከሰተው ከፍተኛ የኦክስጅን እጥረት ግን ትልቁ የኦክስጅን አምራች የሆነው ጮራ ጋዝና ኬሚካል ድርጅት ማሽኑ መበላሸቱ አስተዋፆ እንዳደረገ ዋዜማ ማረጋገጥ ችላለች፡፡


የጮራ ጋዝ በነበረው ብቸኛ ማምረቻ ማሽን ላይ ከ3 ሳምንታት በፊት ብልሽት ያጋጠመው በመሆኑ ምርቱን ማቅረብ እንዳልቻለ ዋና ስራ አስኪያጁ የሆኑት አቶ ሹምዬ አቦኸይ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ ማሽኑን የሚያስተካክል ባለሞያ ከውጪ እስኪመጣ እየተጠበቀ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

ከጮራ ውጪ ያሉ አምራቾችን በተመለከተ ደግሞ የውጪ ምንዛሬ እጥረት በሙሉ አቅማቸው እንዳይሰሩ ትልቅ እንቅፋት እንደሆነባቸው አስተባባሪው ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡


“ይህንንም ለመፍታት በልዩ ሁኔታ እንዲፈቀድላቸው እያደርግን ነው፡፡” ነው ያሉት ዶ/ር ሚዛን ሌላው እንቅፋት የመብራት መቆራረጥ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን ሀይል ተቋርጦ ሲመለስ ማምረቻ ማሽኖቹን ለማስነሳት በትንሹ እስከ 1 ሰዓት ተኩል የሚፈጅ መሆኑ ብዙ ኦክስጅን እንዳይመረት ያደረገ ምክኒያት ሆኖ ተቀምጧል፡፡

በሚቻለው መንገድ ሁሉ ችግሮቹን ለመፍታት እየጣርን ነው ያሉት አስተባባሪው ፍላጎቱን ሙሉ በሙሉ የሚያሟላ ባይሆንም አሁን ላይ በቀን 2, 000 ሲሊንደር ወይንም በሰዓት 2,100 ኪውቢክ ሜትር ገደማ እየተመረተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ለመጠባበቂያ እንዲሆንም የጤና ሚኒስቴር ተጨማሪ በጀት መድቦ በሚሊኒየም አዳራሽ 1000 ሲሊንደሮች መቀመጣቸውን አክለዋል፡፡


አሁንም ቢሆን ግን ህዝቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ካላደረገ ፍላጎት እና አቅርቦት ማመጣጠን እንደሚከብድ አሳስበዋል፡፡[ ዋዜማ ራዲዮ]