Merga Bekana NEBE head
Merga Bekana NEBE head

ዋዜማ ራዲዮ- ባለፈው ግንቦት ወር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስራ አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ምዝገባ ፍቃድ ሰርዟል፡፡ የተሻሻለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ 573/2000 መሰረት ያደረገው የቦርዱ እርምጃ በዓይነቱ ታይቶ የማይታወቅ ነው፡፡ ቦርዱ ለውሳኔ የተገደድኩት ፓርቲዎቹ የስራ ጊዚያቸውን ባጠናቀቁ አመራሮች ምትክ የተተኩ ሰዎችን ባለማሳወቃቸው፣ የኦዲቲንግ ክፍተት ያለባቸው በመሆናቸው፣ ትክክለኛ አድራሻቸውን አሟልተው ባለማሳወቃቸውና ጠቅላላ ጉባዔ በጊዜው ባለማካሄዳቸው ነው ይላል፡፡

ከተሰረዙት አስራ አራት ፓርቲዎች ውስጥ አስራ አንዱ ብሄረሰብተኮር ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሦስቱ ህብረብሄራዊ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከአስራ አራቱ ውስጥ ዘጠኙ በደቡብ ክልል የሚንቀሳቀሱ የብሄረስብ ድርጅቶች ናቸው፡፡

ቦርዱ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው ብሄረሰብተኮሮችም ሆኑ ህብረብሄራዊ ተቃዋሚ ድርጅቶች ከምንጊዜውም በላይ በተዳከሙበትና በተበታተኑበት ወቅት ላይ ነው፡፡ አንዳቸውም በኢህአዴግ ስልጣን ላይ አደጋ መደቀን የሚችሉ አይደሉም፡፡ ታዲያ ለምን ሊያጠፋቸው ፈለገ?

[የቻላቸው ታደሰን የድምፅ ዘገባ እዚህ ያድምጡ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

ዋነኛው መላ ምት ኢህአዴግመራሹ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከገጠሙት ህዝባዊ ግፊቶች ጋር ይያያዛል፡፡ ባንድ በኩል በአዲስ አበባ መሪ ዕቀድ ሰበብ በተቀሰቀሰው የኦሮሚያው መጠነሰፊ አመፅ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ከርሟል፡፡ በሌላ በኩል በማንነትና አስተዳደራዊ አከላለል ዙሪያ የተነሱ ጥያቄዎችን መፍታት ባለመቻሉ ግጭት ተቀስቅሶ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይ የኮንሶ፣ ቁጫ፣ ቅማንትና ወልቃይት ጥያቄዎች መነጋገሪያ መሆናቸው አልቀረም፡፡

መንግስት ከተራ ውንጀላ ባሻገር አስተማማኝ ማስረጃ ማቅረብ ቢያዳግተውም የኦሮሚያውን አመፅ የቀሰቀሱት፣ ያደራጁትና የመሩት እንደ ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስና ኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ያሉ ብሄርተኮር ድርጅቶች ናቸው ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም የተከሰቱትን ግጭቶች አስመልክቶ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ብሄርተኮር ተቃዋሚ ድርጅቶችን ተጠያቂ ማድረጉ መላ ምቱን ያጠናክራል፡፡ ይህ ሁሉ የብሄረሰብተኮር ድርጅቶች መብዛት ያልታሰበ አደጋ እንዳይደቅንበት ኢህአዴግ መስጋቱን ሊያመለክት ይችላል፡፡

የብሄረሰብ ፖለቲካ ድርጅቶችን በተመለከተ ኢህአዴግ ውልውል ውስጥ የገባ ይመስላል፡፡ ባንድ በኩል በርካታ ብሄረሰቦች ባሏት ሀገር በተለይ የማንነትና አስተዳደራዊ አከላል ጥያቄ የሚያነሱት ብሄረሰቦች እየበዙ ከሄዱ በስርዓቱ ላይ ህጋዊ፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች መፍጠራቸው አይቀሬ መሆኑን የተገነዘበ ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል የማንነትና አስተዳደራዊ ጥቄዎች ተበራክተው ይታዩ የነበረው በደቡብ ክልል ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ጥያቄው ወደ ትላልቆቹ አማራና ትግራይ ክልሎችም ተዛምቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ለብሄረሰቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት ራሱን ቀዳሚ ጠበቃ አድርጎ የሾመው ኢህአዴግ ብሄረሰብተኮር ድርጅቶችን በማዳከም እንዲህ ዓይነት ጥያቄያችን ከወዲሁ ለመቀነስ ፈልጎ ይሆን? የሚል ጥርጣሬ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ የዞን አስተዳደር ለማግኘት እያደረገ ባለው ትግል ከመንግስት ጋር ግጭት ውስጥ በገባው በኮንሶ ብሄረሰብም አንድ ብሄረሰብተኮር ተቃዋሚ ድርጅት መሰረዙ ይህንኑ ጥያቄ አጭሯል፡፡

በሌላ በኩል ደሞ የተበታተኑ ደካማ ብሄረሰብተኮር ፖለቲካ ድርጅቶች መኖራቸው የስልጣን ቁጥጥሩን ለማስቀጠል ይጠቅሙታል፡፡ ምንም እንኳ ብልጭ ድርግም የሚል ፀረኢህአዴግ ህዝባዊ መነቃቃት እየተፈጠረ መሆኑ ባይካድም ለኢህአዴግ ግን ብሄርተኮር ተቃዋሚ ድርጅቶችን ለማዳከም ትክክለኛ ጊዜ አይመስልም፡፡ ከጠቅላላ ብሄረሰብተኮር ድርጅቶች ብዛት አንፃር ሲታይ አሁን ህጋዊ ፍቃዳቸውን የተነጠቁት ድርጅቶች ቁጥራቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

በሀገሪቱ ከስልሳ በላይ ተቃዋሚ ድርጅቶች ህጋዊ ሰውነት አግኝተው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን አብዛኛዎቹ ብሄረሰብተኮር ጥቃቅን ድርጅቶች ናቸው፡፡ ሆኖም ምን ያህሎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች መመዝገቢያ አዋጅ መሰረት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ምርጫ ቦርድ የተሟላ መረጃ ስለማይሰጥ ወቅታዊ ሁኔታቸውን ለማወቅ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ አዋጁ ጠበቅ ያሉ ህጋዊ መስፈርቶችን የያዘ ቢሆንም ብዙዎቹ ግን በየጊዜው ህጋዊ መስፈርቶችን ማሟላታቸው እጅጉን አጠራጣሪ ነው፡፡

የጥቃቅን ፖለቲካ ድርጅቶችን ተክለ ሰውነት የሚያውቁ የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት ግን ኢህአዴግ የድርጅቶቹን በስም መኖር ባይፈልገው ኖሮ አብዛኛዎቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተቃውሞ ፖለቲካ መድረክ ድምጥማጣቸውን ባጠፋው ነበር፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት የብሄረሰብተኮር ተቃዋሚ ድርጅቶች መፍላት ኢህዴግን ጠቀመው እንጂ አልጎዳውም፡፡ ለዚህም ይመስላል የቦርዱ ውሳኔ የጥቂት ብሄረሰብተኮር ድርጅቶችን ፍቃድ በመንጠቅ የቆመው፡፡

ውሳኔው የየኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረትን ፍቃድም ሰርዟል፡፡ ህብረቱ በተከታታይ በተደረጉ ብሄራዊ ምርጫዎች ተሳትፎው የሚታወቅ ሲሆን 1997 ምርጫም ጥቂት መቀመጫዎችን ማግኘት ችሎ ነበር፡፡ በኋላ ግን ተዳክሞ ቆይቷል፡፡

ውሳኔው የመድረክ አባል በሆነው በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሚመራው የደቡብ ህብረትም ላይ አርፏል፡፡ የህብረት ምዝገባ መሰረዝ የድርጅቱን ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን ያለ ተቃዋሚ ድርጅት ያስቀራቸዋል፡፡ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግሬስ ሊቀመንበር ከሆኑት ዶክተር መረራ ጉዲና ጋር እየተቀያየሩ ሲመሩት በኖሩት መድረክም ውክልና አይኖራቸውም፡፡ ፕሮፌሰሩ መድረኩን ሲመሩ የነበረው የኢትዮጵያ ማህበራዊ ዴሞክራሲ ደቡብ ህብረት አንድነት ፓርቲ በተሰኘው ድርጅታቸው በኩል ነበር፡፡ የህብረቱ ፍቃድ ተሰረዘ ማለት የፓርቲው ብሄርተኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሌላ ህጋዊ ፖለቲካ ድርጅት እንዲፈልጉ ወይም ከተቃውሞ ፓርቲ ፖለቲካ ጭራሹን ጡረታ እንዲወጡ ያስገድዳቸዋል፡፡ የፕሮፌሰሩ ፓርቲ ቀደም ሲል የሁለት ፖለቲካ ድርጅቶች ውህደት ነበር፡፡

ድንገተኛው ውሳኔ በትልቁ የተቃዋሚ ድርጅቶች ስብስብ በሆነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ ላይም ከባድ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ የፕሮፌሰሩ ፓርቲ ሲወጣ በመድረክ አባልነት የሚቀጥሉት ተቃዋሚ ድርጅቶች አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ፣ ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስና የሲዳማ አርነት ንቅናቄ የተሰኙት የብሄረሰብ ድርጅቶች በቻ ይቀራሉ፡፡ መድረክ አንድነት ፓርቲ ከመድረኩ አባልነት ባለፈው ዓመት ከታገደ ወዲህ ድምፁ ተዳክሟል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከአንድነት መታገድ በኋላ ብሄርተኮር የሆኑት የመድረክ አባል ድርጅቶች ከገዥው ኢህአዴግ ጋር መሰረታዊ የፖሊሲ ልዩነታቸው እምብዛም ነው፡፡

ህብረት በተቃውሞ ፖለቲካው መድረክ አለመኖሩ ሌላም አንድምታ አለው፡፡ ለብዙ ዓመታት በደቡብ ክልል ዋነኛው የኢህአዴግ ተቃዋሚ ሆኖ የቆየው ህብረቱ ነበር፡፡ ያሁኑ ውሳኔ ግን ደቡብ ክልል በተቃዋሚነት ያለውን ድርጅታዊ ውክልና ጭምር ያሳሳዋል፡፡ አሁን በደቡብ የሚቀረው ተቃዋሚ ድርጅት ረዥም የፖለቲካ ሰውነት ያለውና ለሲዳማ ብሄር የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት ሲታገል የኖረው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡

1997 ምርጫ ወዲህ በመንግስት ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ እንዲሁም በውስጣዊ ሽኩቻ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንደተዳከመ ቀጥሏል፡፡ ኢህአዴግም ህጋዊና ፖለቲካዊ መንገዶችን ተጠቅሞ ህብረብሄራዊ ተቃዋሚ ድርጅቶች እንዳይፈጠሩ፣ የተፈጠሩትም እንዳይፋፉ የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ ተደጋጋሚ ውንጀላ ይቀርብበታል፡፡ አሁን በተቃውሞው ፖለቲካ መድረክ እዚህ ግባ የሚባል ተቃዋሚ ድርጅት የለም፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር በመዘርጋት የሚታወቀው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትም በቅርቡ ባካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት በውስጣዊ ቀውስና ውጫዊ ጫና ተዳክሞ መቆየቱን በይፋ አምኗል፡፡

በሀገሪቱ ከስልሳ በላይ ተቃዋሚ ድርጅቶች ተፈልፍለው ለዴሞክራሲ ወይም ሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ዕድገት ጠብ ያደረጉት ነገር አለ ወይ? ለሚለው ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ በራሱ በኢህአዴግ አንደበት ከሚሰበከው ትርክት በስተቀር፡፡ ብዙዎቹ የብሄረሰብ ድርጅቶች የአንድ ወይም ጥቂት ሰዎች ፓርቲዎች መሆናቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ በአዋጁ መሰረት ፍቃዳቸው የተሰረዘባቸው ፓርቲዎች አቤቱታቸውን በፍርድ ቤት አቅርበው መሞገት የሚችሉ ቢሆኑም እስካሁን ውሳኔውን ተቃውመው ለፍርድ ቤት ሲጮሁ አልተሰሙም፡፡

በጠቅላላው የምርጫ ቦርድ ውሳኔ የሚያሳየው ኢህአዴግ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መምታት መፈለጉን ነው፡፡ ባንድ በኩል ህብረብሄራዊ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ህጋዊ ሰውነት በመንፈግ ማዳከም፡፡ ከተሰረዙት ፓርቲዎች ውስጥ ሦስቱ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች መሆናቸውም ይህንኑ ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለትናንሽ ብሄርሰብተኮር ድርጅቶችን መልዕክት ማስተላለፍ፡፡ እርምጃው ግን ብሄርተኮር ድርጅቶች የብሄር ጥያቄዎችን ከመፍጠር ወይም ከማራገብ እንዲቆጠቡ የማስጠንቀቂያ ደወል ከመስጠት ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡ ምንም እንኳ ብዙ ፓርቲዎች ህጉን አክብረው ስለመንቀሳቀሳቸው በርካታ የሚነሱ ጥየቄዎች ቢኖሩም ብዙ ደካማና ጥቃቅን ፓርቲዎችን ሲያልፍ የኖረው ምርጫ ቦርድ ባሁኑ ወቅት ላይ እርምጃ ለመውሰድ መፈለጉ ውሳኔውን ፖለቲካዊ አስመስሎታል፡፡