ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት ዛሬ ረፋድ ላይ ተሰይም የእነ ስብሀት ነጋ እና ሌሎች 2 መዝገቦችን ተመልክቷል።


አቶ ስበሀት ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው የገለፁት ጠበቆች ከዚህ ቀደም በፖሊስ ሆስፒታል ቢታከሙም ከህመማቸው አንፃር የሚመጥን እንዳልነበር አስረድተዋል። በመሆኑም ከዚህ በፊት ክትትል ያደርጉበት በነበረው አዲስ ህይወት ሆስፒታል እንዲታከሙ እንዲፈቅድ ችሎቱን ጠይቀዋል።


ተጠርጣሪዎች በሀኪሞቻቸው የመታየት መብት እንዳላቸው በሚደነግገው የህገመንግስቱ አንቀፅ 21/2 መሰረት ተጠርጣሪው በግል ሀኪም ቢታከሙ የሚከለክል ሁኔታ አላየሁም ያለው ችሎቱ የግል ሀኪማቸው የህክምና መሳሪያዎቹን ይዞ ባረፉበት ቦታ እንዲያክማቸው አዟል።


የህመማቸው ሁኔታ ከፍተኛ መሳሪያውችን የሚጠይቅ ከሆነ ደግሞ ሀኪማቸው በችሎት ቀርቦ ቃለመሀላ ከፈፀመ በኋላ አስፈላጊው እጀባ ተደርጎላቸው በሆስፒታል ሆነው እንዲታከሙ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ይህ የማይሆን ከሆነ የይግባኝ አቤቱታ የማቅረብ መብታቸውም የተጠበቀ መሆኑን ችሎቱ አሳስቧል።ከዚህ ጎን ለጎን የፌደራል ፖሊስ ባለፉት የምርመራ ቀናት የ85 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን እና የጦር መሳሪያዎችን ማሰባሰቡን ለችሎቱ ገልጿል።ሆኖም ተጨማሪ የምርመራ ስራዎች ስለሚቀሩት 14 ተጨማሪ ቀናት ጠይቋል።


ምርመራው በጅምላ መሆን የለበትም በማለት የተቃወሙት የተጠርጣሪዎች ጠበቆች። ይህን ሁሉ ጊዜ ለምርመራ ከተሰጠ በኋላ አሁንም በጅምላ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ የለበትም ብለዋል።


ማን ምን አይነት ወንጀል እንደፈፀመ በግልፅ ሊቀመጥ ይገባል በማለት ተከራክረዋል።
ፖሊስ የእያንዳንዱን ወንጀል ለይቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ የሰጠው ችሎቱ ተጨማሪ 13 ቀን ፈቅዷል። [ዋዜማ ራዲዮ]