ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ለመሰማራት አቶ በላይነህ ክንዴን ጨምሮ የተለያዩ ባለሀብቶች ሰፋፊ መሬት እንደተዘጋጀላቸው ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ዋዜማ የተመለከተችው የ16 ኩባንያዎችና ግለሰቦች የኢንቨስትመንት መሬት ጥያቄ ለአስተዳደሩ ካቢኔ ለውሳኔ መቅረቡን ያሳያል። የመሬት ጥያቄውም ከስፋትና ከመዋእለነዋይ አቅም እንዲሁም መሬቱ ከሚገኝበት አካባቢ ጋር ተጣምሮ ቀርቧል።

መቀመጫውን በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ያደረገው ‘አስመራ ሆልዲንግ ግሩፕ’ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴልና አፓርትመንት በ156 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ካፒታል የሚሰራበት 2213 ካሬ ሜትር መሬት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተዘጋጅቶለታል። ለዚህ ኩባንያ የታሰበው ቦታ ላይ 29 መኖርያ ቤቶች እንዳሉና ስፍራውም የመልሶ ማልማት እንቅስቃሴ ያስፈልገዋል ተብሏል።

አስመራ ሆልዲንግስ በአፍሪቃ አህጉር በማዕድን ፣ የባህር ትራንስፖርት፣ኮንስትራክሽንና ሆቴል ዘርፍ የተሰማራ ኩባንያ ነው።

ጌታስ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴልና ሞልን በ2.5 ቢሊየን ብር  ለመገንባት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ 7, 016 ካሬ ሜትር ቦታ ጠይቆ ውሳኔ እየተጠባበቀ ነው። የተዘጋጀለት ይህ መሬትም ከይገባኛል ነጻ የሆነ እና በመልሶ ማልማት ክልል ውስጥ መሆኑም ተመላክቷል።

በ561 ሚሊየን ብር ዘመናዊ ሞል ለመገንባት የጠየቁት ደግሞ ታዋቂው ባለሀብት አቶ በላይነህ ክንዴ ሲሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔን የሚጠብቅ 8,760 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 እንደተዘጋጀላቸው መረዳት ችለናል።

አትሌት አበበች አለሙ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል በ500 ሚሊየን ብር ለመገንባት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15
1191 ካሬ ሜትር መሬት ተዘጋጅቶላታል ; አርቲስት አደም መሀመድም በተመሳሳይ ክፍለ ከተማና ወረዳ በግማሽ ቢሊየን ብር ሞል ለመስራት 5000 ካሬ ሜትር መሬት ለመረከብ ተዘጋጅቷል። ጀርመን አመንቴ ; ሶላ ትሬዲንግ እና ወረታ ኢንተርናሽናል ሆቴልና ዘመናዊ ሞል ለመሰራት በቦሌና አራዳ ክፍለ ከተሞች ቦታ ለመረከብ የአዲስ አበባ ካቢኔን የመጨረሻ ውሳኔ እየጠበቁ ነው።

 ሌሎች ስምንት ኩባንያዎችም ሆቴልና ንግድ ማእከሎችን ለመገንባት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች መሬት ተዘጋጅቶላቸዋል። የእነዚህ ግዙፍ የመሬት ጥያቄዎች መቋጫ እንዲያገኝም የካቢኔ ውሳኔ ብቻ እንደሚጠበቅ ነው የሰማነው። [ዋዜማ ራዲዮ]