የመንግስት የፖሊስ ባንክ ተብለው ከሚታወቁት ውስጥ አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቢለየን የሚቆጠር ብድር ካለባቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ዕዳውን መሰብሰብ ተቸግሯል። ችግሮቹን ከቀድሞው አመራር የተንከባለሉ ይሁኑ እንጂ አዳዲስ ተግዳሮቶችም ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ዝርዝሩን ያንብቡት።

ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ የመንግስት የፖሊሲ ባንክ ከሚባሉት ውስጥ የልማት ባንክ ባልተመለሰ ብድር ምጣኔ መናር ምክንያት በተደጋጋሚ ስሙ ሲነሳ ቆይቷል። ሌላኛውም የፖሊሲ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ከልማት ባንክ በባሰ መልኩ ባልተመለሰ ብድር ቀውስ ውስጥ መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ መረዳት ችላለች። ይህ ባንክ ከሌሎች የንግድ ባንኮች በተለየ ሁኔታ በየጊዜው በሚያወጣቸው ሪፖርቶች ውስጥ ያልተመለሰ ብድር ምጣኔያውን ይፋ የማድረግ ልምድ የለውም። ሌሎች በሀገሪቱ ያሉ ንግድ ባንኮች በአመታዊ ሪፖርታቸው ላይ የተበላሸ ብድር ምጣኔያቸውን ይፋ ያደርጋሉ። ልማት ባንክም ቢሆን ከሰጠው ብድር 40 በመቶው መበላሸቱን ጋዜጠኞችን ጠርቶ ተናግሯል። ምንም እንኳ የተበላሸ ብድሩ ከዚህ እንዲሚልቅ ተጨባጭ መረጃ ቢኖርም።


     የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግን በቅርቡ ይፋ ባደረገው የዚህ በጀት አመት የስድስት ወር ሪፖርቱ ስለ ትርፉ እንጂ ሌሎች ባንኩ እንደሚያደርጉት የተበላሸ ብድር ምጣኔውን ይፋ አላደረገም። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥር 4 ቀን 2019 ያወጣው ሪፖርትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የተበላሸ ብድር ምጣኔያቸው በአማካይ 2.6 በመቶ ሆኖ ጤናማ ናቸው ይላል፤ በተናጠል ያስቀመጠው ነገር የለም። በመስፈርቱ መሰረት የንግድ ባንኮች ካበደሩት ገንዘብ የተበላሸው ብድር ምጣኔ ከአምስት በመቶ ካላለፈ አደጋ ውስጥ ናቸው አይባሉም።


     የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች አበድሮ እስካሁን ያልተመለሰለት ብድር ግን ጤነኛነቱን አያሳዩም። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ካለበት 300 ቢሊየን ብር ብድር ውስጥ 220 ቢሊየን ብሩን ከንግድ ባንክ በኮርፖሬት ቦንድ የተበደረው ነው። ኤሌክትሪክ ሀይል ይህን ገንዘብ ለንግድ ባንኩ እስካሁን አልመለሰም። ምክንያቱም ተቋሙ ራሱ ትርፋማ መሆን አቅቶት በድጎማ ሲንቀሳቀስ የነበረ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ባለመቻላቸውም ሁነኛ ገቢ ማግኘት ያልቻለ ነው። ለገቢው ማሻሻያም ሀይል የሚሸጥበትን ዋጋም ሲያሻሽል ይታያል።


     በሌላ በኩል በቅርቡ ዋዜማ ራዲዮ እንደዘገበችው ንግድ ባንክ ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በ2008 አ.ም በወቅቱ የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በሚባለው መስሪያ ቤት ተያዥነት ያበደረው ስምንት ቢሊየን ብርም ለንግድ ባንኩ አልተመለሰለትም። ይህ ገንዘብ ለሜቴክ ወደ ብድር የተቀየረለት ንግድ ባንክ ኤልሲ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) ከፍቶ ለሜቴክ በውጭ ምንዛሬ የተለያዩ ጥሬ እቃዎችን ካመጣለት በሁዋላ ሜቴክ ለውጭ ምንዛሬው ተመጣጣኝ የሆነው ስምንት ቢሊየን ብሩን ባለመክፈሉ ነው። ንግድ ባንክም ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በተጻፈለት ደብዳቤ ወደ ብድር ቀይሮለታል። ይሄም ገንዘብ ለንግድ ባንክ አልተመለሰም።


     ንግድ ባንኩ ለመንግስት የልማት ስራዎች ያበደረው ከፍ ያለ መጠን ያለው ገንዘብ እየተመለሰለት ላለመሆኑ የባንኩ የዚህ አመት የስድስት ወር ሪፖርቱ ጠቋሚ ነው። ባንኩ በስድስት ወራቶች ውስጥ ሊመለስለት ከሚገባው ብድር ውስጥ ዘጠኝ ቢሊየን ብሩ አልተመለሰለትም። የባንኩ ሪፖርት እንደሚያሳየው በግማሽ አመቱ ሊመለስለት ከሚገባው ብድር ውስጥ መሰብሰ የነበረበት 31 ቢሊየን ብር ነበር ። የሰበሰበው ግን 22 ቢሊየን ብር ነው። ይህም የሆነው ለመንግስት ፕሮጀክቶች ከተሰጠው ብድር መሰብሰብ የነበረበት ገንዘብ በተገቢው መንገድ ባለመሰብሰቡ መሆኑ ተገልጿል። ለኬሚካል ኮርፖሬሽን የተሰጠ ሶስት ቢሊየን ብር ብድርም ችግር እንደነበረበት ይታወቃል። የስኳር ኮርፖሬሽንም ከንግድ ባንክ የወሰደው ብድርም በስኳር ፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያትም ተበላሽቷል።


     የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና እነዚህ የባንኩ ብድር አሰጣጦች ችግር የነበረባቸው አልነበሩም ወይ ? ተብለው ከሰሞኑ ሲጠየቁ የሰጡት ምላሽ “ እኔ ወደ ባንኩ ከመጣሁ ገና ጥቂት ወራት ነው የሆነኝ ፣ ሊጣራ የሚገባው ጉዳይ ነው” የሚል ነው።


በግለሰቦች ደረጃም ቢታይ እነ ተክለብርሀን አምባዬ እና በላይነህ ከንዴን የመሳሰሉ ባለ ሀብቶች ከባንኩ የተበደሩት በርካታ ቢሊየን ብሮች በወቅቱ መመለሳቸው ጥርጣሬ ውስጥ እንደሆኑ የባንኩ ምንጮቻችን በስፋት ይናገራሉ።


ሌላው አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ ንግድ ባንክ በኤክስፖርት ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ደንበኞቹ ያበደረው ገንዘብ በወቅቱ እንደማይመለስ አመላካቹ ብዙዎቹ የኤክስፖርት ዘርፍ ተበዳሪዎቹ በተበላሸ ብድር መዝገብ ውስጥ መግባታቸው ነው።በዚህ ላይ ባንኩ ከተለያየ ዘርፍ ተበዳሪዎቹ ጋር ከሁለት ሳምንት በፊት ሲወያይ ነበር።


ባንኩ ብድር ላይ የሚሰሩ ሰራተኞቹን ከተበዳሪዎቹ ጋር ያጣምራቸዋል።እነዚህ ሰራተኞች ሪሌሽን ማናጀርስ (የቅርብ ክትትል ባለሙያዎች) ይባላሉ።በእያንዳቸው ስር አምስትም አስርም ተበዳሪዎችን ጉዳይ ይይዛሉ። ከተበዳሪዎች ዕዳውን መሰብሰብ ያልሆነለት ባንኩ በተለይም ለግለሰቦች ለማበደር ብዙም ፈቃደኛ አይደለም።


በነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች የባንኩ የብድር አስተዳደር ሁኔታ ጤናማ አለመሆኑን ማወቅ ይቻላል። የባንኩን ከፍተኛ አመራሮች ስለባንኩ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ለማገናገር ጥረት ስናደርግ ፣ የባንኩ የተበለሸ የብድር ምጣኔ እስከ አራት በመቶ ነው የሚል ርገጠኛ ያልሆነ ምላሽ ነው የሚሰጡት። ነገር ግን እጃችን ላይ ያሉት መረጃዎች የዚህን ፍጹም ተቃራኒ መልክ ነው የሚያሳዩት። ለዚህ ተጠያቂው የበፊቱ የባንክ አመራር መሆኑ በስፋት ይነሳል። ባንኩ አሁን ላይ የሚነሳበት የብሄር ተኮር አደረጃጀት ትችትም ወደ ባሰ እንጂ ወደተሻለ ነገር የሚያስኬደው አይመስልም። [ዋዜማ ራዲዮ]