NBE Governer Yinager Dessie

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በማስያዣ ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ ብድር ላይ ጥሎት ከነበረው እገዳ የነዳጅ ምርት አከፋፋይ ድርጅቶች የብድር እገዳው እንዲነሳላቸው መወሰኑን ለሁሉም የንግድ ባንክ ፕሬዝዳንቶች በላከው ማስታወሻ መግለፁን ዋዜማ አረጋግጣለች።


የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ለከፍተኛ አሻጥር ተጋልጧል ፣ በዚህም ሳቢያ ከባድ የዋጋ ንረት ተፈጥሯል በሚል ነበር በማስያዣ ላይ የተመሰረተ ብድርን የንግድ ባንኮች ለጊዜው እንዳይሰጡ የከለከለው።ሆኖም ክልከላውን በሂደት ዘርፎችን እየለየ ሲያነሳ ቆይቷል።


ከትናንት ጀምሮ የነዳጅ ምርት አከፋፋይ ድርጅቶች የባንክ ብድር እንዳያገኙ ከሚከለክለው ገደብ ውጭ እንዲሆኑና የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለባንኮች አሳውቋል። የነዳጅ ምርት አከፋፋይ ኩባንያዎቹ የብድር ተጠቃሚ የሚሆኑትም ከመንግስታዊው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር በገቡት ውሎ መሰረት እንደሚሆንም የብሄራዊ ባንኩ ውሳኔ ያሳያል።


ብድር ላይ ተጥሎ የቆየው ገደብ ስራቸው ላይ ተጽእኖን እንዳሳረፈ የነዳጅ ምርት አከፋፋዮች በተደጋጋሚ ቅሬታን ሲያቀርቡ ተደምጠዋል። ኩባንያዎቹ ቀደም ብሎ በነበረው አሰራር ነዳጅን ለማደያዎች ለማከፋፈል ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በዱቤ መውሰድ ይችሉ ነበር ። ከጊዜ በሁዋላ ግን ነዳጅን በዱቤ ሳይሆን እጅ በእጅ ገንዘብ ከፍለው ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንዲረከቡ ተደርጓል። ይህ ውሳኔ በራሱ ችግር ፈጥሮብናል የሚሉት ኩባንያዎቹ የባንኮች ብድር ላይ ገደብ መጣሉ ደግሞ የበለጠ እንቅፋት ሆኖብናል በማለት ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል።


ብሄራዊ ባንክም የነዳጅ ምርት አከፋፋይ ድርጅቶች ከትናንት ጀምሮ ከብድር እገዳው ነጻ እንዲሆኑ ከባንኮች እንዲበደሩ ወስኗል።ነገር ግን የብድር እገዳው የተነሳው ከመንግስታዊው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ውል ገብተው ነዳጅን ተረክበው ማከፋፈል ለሚችሉ  ኩባንያዎች እንጂ ከአከፋፋዮቹ ተረክበው ለገበያ የሚያቀርቡትን ለጊዜው እንደማይመለከትም ለባንክ ፕሬዝዳንቶች በተላከው ማስታወሻ ላይ ተመልክቷል።


 ብሄራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም በጎንደር አካባቢ ላሉ የሰሊጥ አምራቾች ፣ ባንኮች በሀራጅ ላወጡት ንብረት ፣ ለሰራተኞቻቸው የሚሰጥ እና የጸደቁ የቤት ብድሮች ጨምሮ አምስት የብድር አይነቶች ከብድር እገዳው ውጭ እንዲሆኑ መወሰኑ ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]