Ethiopia Parliament Building
Ethiopia Parliament Building

(ዋዜማ ራዲዮ) የኢትዮጵያ መንግስት በሁሉም ፌደራል ተቋማት የተመጣጠነ የብሄረሰብ ስብጥር እንዲኖር ህግ ሊያወጣ መሆኑን ለፓርላማው አስታውቋል፡፡ የፐብሊክና ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ሚንስትሯ ለፓርላማው እንደተናገሩት የፌደራል መስሪያ ቤቶች የሀገሪቱን ብሄረሰብ ስብጥር ገፅታ ማንፀባረቅ እንዳለባቸው መንግስት ያምናል ብለዋል፡፡ 
የብሄረሰብ ስብጥርን በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የተመጣጠነ ለማድረግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ስራ ላይ ማዋል በአሃዳዊም ሆነ ፌደራላዊ ስርዓት በሚከተሉ ሀገሮች የተለመደ ነው፡፡ በሌሎች ሀገሮችም እንደታየው ፖሊሲውን የማውጣቱ ሂደትም ሆነ ትግበራው ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ሁሉ በርካታ ችግሮችም ማስከተሉ አይቀርም፡፡

ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት እንዲህ ዓይነቱን ፖሊሲ ለማውጣት የገፋፉት ህጋዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? በፖሊሲው ዙሪያ ሊነሱ የሚችሉት አወንታዊና አሉታዊ ሃሳቦችስ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ፖሊሲው ስራ ላይ ቢውል ምን ዓይነት አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች ይኖሩታል? ተመሳሳይ ፖሊሲ ካላቸው እና ብዝሃነት የሚታይባቸው ሌሎቸ ሀገሮችስ ምን ልምዶች አሏቸው?

ቻላቸው ታደሰ ዝርዝር ዘገባ አዘጋጅቷል

የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ሚንስቴር ሰሞኑን እንዳስታወቀው ሁሉም ብሄረሰቦች በፌደራል መንግስት ተቋማት የተመጣጠነ ውክልና እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ ህግ ለማዘጋጀት እየተዘጋጀ መሆኑን አስውቋል፡፡ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ሚንስትሯ ለፓርላማው እንደተናሩት የህጉ ዓላማ የፌደራል ተቋማት የፌደራል ስርዓቱን መምሰል እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ይህን ፖሊሲ ማውጣት የፈለገበት ፖለቲካዊ ምክንያቶች ይኖሩታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እንዱ ህዝባዊ ተቃውሞ እየበዛበት ሲሄድ የብዙ ብሄረሰቦችን ድጋፍ ለማግኝት አስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ የፖለቲካ ስልጣንን የተቆጣጠረ ኢኮኖሚውንም ይቆጣጠራል ከሚለው ፍልስፍናው የመነጨም ሊሆን ይችላል፡፡

በሌላ በኩል የራሱንና የአጋር ፓርቲዎችን ካድሬዎች በፌደራሉ ቢሮክራሲ ውስጥ ለመሰግሰግ እንዲመቸው ለማድረግም ይሆናል፡፡ ወጥ የብሄረሰብ ተዋፅዖ ፖሊሲ ባለመኖሩ ተጠያቂነትና ግልፅነት ባይኖረውም ኢህአዴግ በውስጣዊ አሰራሩ የተለያዩ ብሄረሰቦች ተወላጆችን በፌደራልና ክልላዊ መንግስት መስሪያ ቤቶች ሲሾም፤ ካድሬዎችንም ሲመድብ እንደኖረ ግን ይታወቃል፡፡

የሀገሪቱ ህገመንግስት በአንቀፅ 39 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ ሁሉም ብሄረሰቦች በፌደራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ በአንቀፅ 87ም መከላከያ ሚንስቴር የብሄረሰቦችን ሚዛናዊ ተዋፅዖ የጠበቀ መሆን እንደሚገባው ተደንግጓል፡፡ ይህም የፖሊሲ ሃሳቡ ህገመንግስታዊነት እንዳለው ያሳያል፡፡

ህገመንግስቱ ስለ ብሄረሰብ ውክልና መርሆዎችን ቢያስቀምጥም ላፉት ሃያ ዓመታት ዝርዝር የብሄረሰቦችን ስብጥር ለማመጣጠን የሚረዳ የፖሊሲ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ አያውቅም፤ ጉዳዩን የሚከታተል የተለየ መንግስታዊ ተቋምም የለም፡፡ እስካሁን ህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት ሁሉም ብሄረሰቦች በህዝብ ብዛታቸው መጠን ውክልና እንዲያገኙ የተደረገው በፌደሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ብቻ ነው፡፡

ሆኖም በተወሰነ ደረጃ አናሳ ብሄረሰቦችና ሴቶች በስራ ቅጥር እና በተለይ ደግሞ በትምህርት ተቋማት በልዩ ድጋፍ ተሳትፏቸውና ውክልናቸው እንዲጨምር የሚያስችል ልዩ የድጋፍ ፖሊሲ (Affirmative Action) ተቀርፆ ሲተገበር መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ መንግስት ስለ ፖሊሲው ውጤታማነት የተሟላና ወቅታዊ ሪፖርት ሲያቀርብ አይታይም፡፡

በመንግስታዊ መዋቅሮቻቸው የዜጎቻቸውን ተዋፅዖ በማመጣጠን ረገድ ህንድ፣ ሲንጋፖር፣ ማሌዥያ፣ ናይጀሪያና ደቡብ አፍሪካ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በጊዜ ወሰንም መገደብ እንዳለበት፤ ተፈፃሚነቱም በቅጥር ላይ ብቻ እንጂ በዕድገት አሰጣጥ ላይ መሆን እንደሌለበት ምሁራን ይመክራሉ፡፡

ተመጣጣኝ የብሄረሰብ ውክልና ለዲሞክራሲና ለልዩ ድጋፍ ፖሊሲ (affirmative action) መጎልበት አስፈላጊ መሆኑን የሚስማሙበት ምሁራን በርካታ ናቸው፡፡ ዜጎች በሀገራቸው የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው፣ ብሄራዊ አንድነት እንዲፈጠር፣ ፍትሃዊነት እንዲሰፍን ይከራከራሉ፡፡

በተቃራኒው ጎራ ያሉ ምሁራን ደግሞ ለማንነት መስፈርት የሚሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በሀገር ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ይሞግታሉ፡፡ የብሄረሰብ ተዋፅዖን በማመጣጠን ፖሊሲ ላይ የሚቀርበው ሌላኛው ትችት በብቃትና ክህሎት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚለው ስጋት ነው፡፡ በእርግጥ ብቃትንና ክህሎትን ከተዋፅዖ ጋር ማመጣጠን የብዙ ሀገሮች ፈተና እንደሆነ ፖሊሲውን በሚተገብሩ ሀገሮች የተደረጉ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ እንዲህ አይነት ችግሮችን ለመፍታት ለምሳሌ የደቡብ አፍሪካው የሚተገበረው የተዋፅዖ ህግ የፖለቲካ ሹመኞች ከሆኑት ዋና ሃላፊውና ምክትሉ በስተቀር በሌሎች ሰራተኞች ላይ የብቃትና ክህሎት (merit) መስፈርትን ስራ ላይ ማዋልን ግዴታ አድርጎታል፡፡

ያም ሆኖ ወጥ የሆነ የፈተና አሰጣጥ በሌለባቸው፣ ትምህርት ቤቶች ጥራት በሚለያይባቸው፣ የተጭበረበሩ ትምህርት ማሳረጃዎች እና ወጥ የሆነ የሰራተኛ ምዘና በሌለባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች በብቃትና ክህሎት (ወይም merit) ላይ ብቻ የተመሰረተው የሰራተኛ ቅጥርም ቢሆን ከችግር የፀዳ እንዳልሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡

የትኛውም ችግር ፈቺ ፖሊሲ ከመውጣቱ በፊት ችግሩ በስፋት መኖሩ መታወቅ እንዳለበት ግልፅ ነው፡፡ መንግስትም እነዲህ ዓይነት ፖሊሲ ሲወጣ በፌደራል መስሪያ ቤቶቹ የብሄረሰብ ተዋፅዖው በከፍተኛ ደረጃ የተዛባ መሆኑን ለማወቅ የሚያስችል የተሟላ ሳይንሳዊ ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ግልፅ ነው፡፡ ሆኖም በተወሰኑ መስሪያ ቤቶች ላይ የተደረገ ናሙና የዳሰሳ ጥናት እንጂ በሁሉም ፌደራል መስሪያ ቤቶች ስላለው የብሄረሰብ ስብጥር ዝርዝር ጥናት ተደርጎ ለፓርላማው አልቀረበም፡፡ በጎረቤት ኬንያ ግን ፖሊሲውን በስፋት መተግበር የተጀመረው ጎሳዎች በመንግስት ተቋማት ያላቸው ስብጥር ምን እንደሚመስል የተሟላ ጥናት ከተደረገ በኋላ ነው፡፡

ሌላኛው መነሳት ያለበት ጉዳይ ረቂቅ ፖሊሰውን የማዘጋጀት ስልጣን የስራ አስፈፃሚው አካል ነው ወይስ የብሄረሰቦችን ተመጣጣኝ ውክልና የሚያንፀባርቀው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው? የሚለው ነው፡፡ ምንም እንኳ እዚህ ግባ የሚባል ህግ የማውጣት ስልጣን ባይኖረውም ህገመንግስቱ ግን ብሄረሰቦችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ስልጣን የሰጠው ለፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ በሀገራችን የብሄረሰብ ውክልና ጉዳይ አንገብጋቢ ጉዳይ ስለሆነ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ሚንስቴር ብቻ ሊያወጣውም ሆነ ሊያስፈፅመው የሚችል አይመስልም፡፡

የሚንስትሯ መግለጫ የሚያሳየው ፖሊሲው የሚቀረፀው ለፌደራል መስሪያ ቤቶች ብቻ እንደሆነ ነው፤ ክልሎችን አያካትትም፡፡ የስራ አስፈፃሚውን አካል ስልጣን ለመወሰን የወጣው አዋጅ እንደሚለው የፌደራል መንግስቱ መስሪያ ቤቶች የሚባሉት ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ኤጀንሲዎች፣ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊሲና ልማት ድርጅቶች ናቸው፡፡ ሆኖም አብዛኛዎቹ የፌደራሉ መንግስት ተቋማት የሚገኙት አዲስ አበባ ውስጥ ነው ፡፡ ማለት ደግሞ የፖሊሲው ተደራሽነት በአብዛኛው በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በመርህ ደረጃ ሲታይ ቢያንስ ትላልቆቹ ክልሎች በኢህአዴግ የሚመሩ በመሆናቸው የፌደራሉን መንግስት ፖሊሲ ተከትለው ተመሳሳይ ህግ ሊያወጡ ይችላሉ፡፡ እንደዚያ ከሆነ በየክልሎቹ ነዋሪ የሆኑ ብሄረሰቦች ሁሉ በክልል መስተዳድር ተቋማት ተመጣጣኝ ውክልና የማግኘት መብት ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን ክልሎች ፖሊሲውን በቀላሉ ይቀበሉታል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ ለአብነት ያህል በደቡቧ ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከጥቂት ዓመታት በፊት የ70/30 የብሄረሰብ ተዋፅኦ ቀመር ለመተግበር የቀረበው መመሪያ አጨቃጫቂ በመሆኑ እስካሁንም ተግባራዊ ሊደረግ አለመቻሉን ማስታወስ ይበቃል፡፡

ፖሊሲው የሚያስነሳው ሌላው ጥያቄ በትላልቅ ከተማዎች የሚኖሩት በአንድ ብሄር ራሳቸውን መፈረጅ የማይችሉ ዜጎች ጉዳይ ነው፡፡ አሜሪካዊው ክርስቶፈር ክላፋም በተደጋጋሚ እንደሚሉት በትላልቅ ከተሞች ራሳቸውን በአንድ ወይም በሌላ ብሄር መፈረጅ የማይችሉ ወይ የማይፈልጉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በህገመንግስቱ የተዘነጉ ዜጎች አሉ፡፡ ከተወሰነላቸው ክልል ውጭ ለሚኖሩ ብሄረሰቦች ወይም ዜጎች ህገመንግስታዊ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያጎናፀፈው አማራ ክልል ብቻ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በየክልሎቹ እንደ መጤ የሚቆጠሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች የክልሉን ስራ ቋንቋ እየተናገሩም እንኳ ከስራ ቅጥር የሚገለሉባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

የብሄረሰብ ተዋፅዖን የማመጣጠኑ ነገር በአንዳድ ብሄሮች ተወላጆች ላይ ከስራ የመፈናቀል ስጋት መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ሆኖም ቢያንስ በመርህ ደረጃ የታሰበው ህግ ወደፊት በሚኖሩ ቅጥሮች ላይ እንጂ ወደ ኋላ ተፈፃሚነት እንደማይኖረው ይታመናል፡፡ የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት እንዲህ ዓይነት ፖሊሲ መተግበር ያለበት ነባር ሰራተኞችን በማፈናቀል ሳይሆን በሟች፣ ስራ በሚለቁና በተለያዩ ምክንያቶች ከስራ በሚሰናበቱ ሰራተኞች ቦታ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ ያም ሆኖ በአፈፃፀም ላይ በርካታ ችግሮች እንደሚስተዋሉ በናይጀሪያ፣ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

እኤአ በ2014 ዓ.ም በተደረገ ጥናት በጎሰኝነትና ታሪካዊ ምክንያቶች ሳቢያ ከኬንያ 48 ጎሳዎች መካከል 80 በመቶ ያህሉን የሲቪል ሰርቪስ ስራ ቦታዎች የተቆጣጠሩት ስድስት ጎሳዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በስልጣንና ሃብት የበላይነት ያላቸውና ከጠቅላላ ህዝቡ 17 በመቶውን ብቻ የሚሸፍኑት ኩኩዩዎች 23 በመቶ የሚሆነውን የሲቪል ሰርቪስ ስራ ድርሻ በመያዝ ከህዝብ ብዛታቸው በላይ የስራ ቦታዎችን ተቆጣጥረዋል፡፡ ኬንያ እኤአ በ2008 ጀምሮ የብሄራዊ አንድነትና ውህደት አዋጅ (በእንግሊዝኛው National Cohesion and Integration Act) እና ተቆጣጣሪ ኮሚሽን አቋቁማ የጎሳ ተዋፅዖን ለማመጣጠን እየሰራች መሆኗን ትገልፃለች፡፡

በዋነኛነት በብሄረሰብ ፌደራሊዝም በተዋቀረችው ኢትዮጵያ የብሄረሰብ ተዋፅዖን የማመጣጠን ጉዳይ የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ አንገብጋቢ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው፡፡ ያም ሆኖ ከምሁራን ባሻገር እስካሁን ዋነኛ የዜጎች ብሄራዊ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ አያዋውቅም፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት ሊቀርብ የሚችለው ሀገሪቱ በአንድ ጠቅላይ ገዥ ፓርቲ መዳፍ ስር መሆኗ ነው፡፡ በፖሊሲው የሚደሰቱ ዜጎች የሚኖሩትን ያህል ስጋት የሚገባቸውም እንደሚኖሩ እሙን ነው፡፡ ​