Kakuma Refugee camp
Kakuma Refugee camp

(ዋዜማ ራዲዮ) የኬንያ መንግስት ወደ 11ሺህ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበትን ዳዳብ ካምፕ እስከሚቀጥለው ዓመት ጥር ድረስ ሙሉ ለሙሉ እንደሚዘጋ አስታወቀ። ለዳዳብ ካምፕ መዘጋት መንስኤ ነው የተባለው የፀጥታ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ነው።

በናይሮቢ “ዌስት ጌት” የገበያ ማዕከል የደረሰውን ጥቃት ጨምሮ በኬንያ ላይ ያነጣጠሩ የሽብር ድርጊቶች “የሚጠነሰሱት” እና “የሚቀናበሩት” በስደተኛ ካምፖች እንደሆነ የሀገሪቱ መንግስት ይገልጻል። ለዚህም እማኝ የሚያደርገው “አሉኝ” የሚላቸውን “የደህንነት መረጃዎች” ነው።

የኬንያ የአገር ውስጥ ግዛት ሚኒስትር ሜጀር ጄነራል ጆሴፍ ናካይሴሬ ዛሬ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ከካምፖቹ ሁሉ “አደጋ የደቀነው” ዳዳብ እንደሆነ ተናግረዋል። ዳዳብ በኬንያ እና ሶማሊያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው እና የአልሻባብ በትር በተደጋጋሚ ባረፋባት ጋሪሳ ግዛት ውስጥ የሚገኝ ነው።

የዓለም ትልቁ የስደተኞች ካምፕ እንደሆነ የሚነገርለት ዳዳብ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) የመጋቢት ወር መረጃ መሰረት ወደ 220 ሺህ ለሚጠጉ ስደተኞች መጠለያ ነው። ከስደተኞቹ አብላጫውን ቁጥር የያዙት ደግሞ ሶማሊያውያን ናቸው።

የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤቱን ማፍረሱን ባለፈው አርብ በይፋ ያሳወቀው የኬንያ መንግስት ከዳዳብ ሌላ በቱርካና የሀገሪቱ ግዛት የሚገኘውን ካኩማ የስደተኞች መጠለያንም ለመዝጋት ዝቶ ነበር። ውሳኔውን ተከትሎ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ውግዘት እና ትችትን ያስተናገደው የኬንያ መንግስት በካኩማ ላይ ለዘብተኛ አቋም ማሳየት ጀምሯል።

“ዳዳብን የምንዘጋው ባለብን የፀጥታ ስጋት ምክንያት ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች የተናገሩት ሚኒስትር ናካይሴሬ “በአሁኑ ጊዜ ከካኩማ ጋር ምንም ችግር የለብንም” ብለዋል።

በካኩማ ወደ189 ሺህ ስደተኞች የሚኖሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሰባት ሺህ ገደማ ያህሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የዩኤን ኤች ሲ አር ቁጥሮች ያመለክታሉ።

ለስደተኛ ካምፖች መዘጋት የገንዘብ ችግርን እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቅሰው የኬንያ መንግስት በዳዳብ የሚገኙ ስደተኞችን ወደ የሀገራቸው ለመመለስ አሊያም ወደ ሶስተኛ ሀገር እንዲሻገሩ 10 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን አስታውቋል። የስደተኞችን መልሶ ሰፈራ የሚከታተል ግብረ ኃይል ማቋቋሙንም ጨምሮ ገልጿል።