ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ጌታቸው አሰፋ መዝገገብ የተከሰሱ 25 ተከሳሾችን መዝገብ ዛሬ (ሐሙስ) ረፋድ ላይ ተመልክቷል፡፡

አቃቤ ህግ ክሴን ያስረዱልኛል ብሎ ካስቆጠራቸው 131 ምስክሮች ውስጥ ለ55ኛ ፣ 56ኛ እና 57ኛን ምስክሮች መጥሪያ አድርሶ ዛሬ እንዲቀርብ የተያዘ ቀጠሮ ቢሆንም አቃቤ ህግ ግን መጥሪያውን ለምስክሮቹ አለማድረሱን ለችሎቱ ገልፅዋል፡፡

ችሎቱም የእነዚህን ሶስት ምስክሮች የሰረዛቸው መሆኑን የበየነ ሲሆን ቀሪ ምስክሮችን ግን ቀድሞ በተያዘው መደበኛ ቀጠሮ ማለትም የካቲት 17 እንደሚቀጥል ዳኞች ገልፀዋል፡፡

አቃቤ ህግ ማቅረብ ባለመቻሉ እስካሁን የተሰረዙ የምስክሮች ቁጥር 20 መድረሱን ዋዜማ ሬድዮ ከተከሳሾች ጠበቃ ተረድታለች፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አቃቤ ህግ ከዚህ ቀደም ከላይ ከተጠቀሱት ምስክሮች ውጭ 29 ምስክሮችን ስለወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ በወጣው አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀፅ 4 (1) (ሸ) እና (በ) መሰረት የምስክሮች ጥበቃ እንዲደረግለት ፤ ማለትም ምስክሮች ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ ማመልከቻ አስገብቶ ክርክር ሲደረግበት ቆይቷል፡፡

ነገር ግን ችሎቱ በህገመንግስቱ ላይ የተቀመጠውን ምስክሮችን የማወቅ መብትን የሚጋፋ ነው በማለት የፌደሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ ይህንን የአቃቤ ህግን ጠያቄ ትርጓሜ እንዲሰጥበት አመልክቷል፡፡

የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ድርጅት የቀድሞ ባልደረቦች የሆኑት ተከሳሾቹ በድብቅ እስር ቤቶች ሰዎችን በማሰር እና በማሰቃየት የሙስና ወንጀል ፈፅሟል ሲል አቃቤ ህግ ክስ የመሰረተ ሲሆን ከመሀላቸው የመስርያ ቤቱ ዋና ሀላፊ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ 3 ተከሳሾች ጉዳያቸው በሌሉበት እየታየ መሆኑ ይታወቃል፡፡