• ሰፋፊ የግጦሽና የእርሻ ቦታ የያዙ አርሶ አደሮች 5 ኮከብ ሆቴል፣ ሞልና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንዲገነቡ ይበረታታሉ

ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዙርያ የሚገኙ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ የምስክርነት ወረቀትን ያለ አንዳች ውጣ ውረድ እንዲሰጣቸው የሚያዝ አዲስ መመርያ ተዘጋጀ፡፡


ዋዜማ እጅ የገባው ይህ አዲስ መመርያ በምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ተፈርሞ ለሁሉም ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮዎች በቀጣይ ሳምንታት የሚላክ ይሆናል፡፡


‹‹የአርሶ አደር የመኖርያ ቤትና የከተማ ግብርና መጠቀሚያ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት አሰጣጥና ዘላቂ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወጣ የአፈጻጸም መመርያ ቁጥር 20/2013›› የሚል ርእስ የተሰጠው ይህ መመርያ አርሶ አደሮች ያለምንም ውጣ ወረድ የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ መንገዶችን ቀላል የሚያደርግ ሲሆን ሰፋፊ ቦታ ይገባናል የሚሉ አርሶ አደሮችም ከተማው ውስጥ ግዙፍ ሞሎች፣ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎችንና 5 እና ከዚያ በላይ ኮከብ ያላቸውን ሆቴሎች በተናጥል፣ በጋራና፣ ከኢንቨስተሮች ጋር በመሻረክ እንዲያለሙ የሚያግዝ ነው፡፡


በምክትል ከንቲባ አዳነች የተፈረመበት ይህ ሰነድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማ ካቢኔ በወሰነው መሠረት የአርሶ አደር የመኖርያ ቤትና የከተማ ግብርና መጠቀሚያ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መመርያውን ተከትላችሁ በአስቸኳይ ወደ ሥራ ግቡ በሚል ክፍለ ከተሞችንና የታችኛውን የከተማውን የአስተዳደር መዋቅር ያዛል፡፡

የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው መመርያውን በመጪዎቹ ሳምንታት ለትግበራ ይልኩታል ፡፡


በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት በልማት ሰበብ አርሶ አደሮችን አፈናቅሏል ሲል የሚጀምረው ይህ በይዘቱ ፍጹም አዲስ የሆነ መመርያ መንግሥት አርሶ አደሩን የመኖርያ ቤትም የግብርና መጠቀሚያ ባለይዞታም ሳያደርገው የምስክር ወረቀትም ሳይሰጠው በመቆየቱ መጸጸቱንና ትክክል እንዳልነበረም ያወሳል፡፡ ይህ ሁኔታም አርሶ አደሩን የገዛ ይዞታውን እንዳያለማው አስሮት ቆይቷል ይላል ሰነዱ፡፡

ከዚህ መመርያ አባሪ ሆኖ የቀረበው የመግቢያ ሀተታ እንደሚለው ይህ አርሶ አደሮችን ያለ ይዞታ የማንከራተቱ ነገር በተከታታይ በሕዘቦች ዘንድ ወቀሳን ማስከተሉን ይተነትንና ነገሩ አሁን ከወቀሳነት አልፎ ፖለቲካዊ አጀንዳ እየሆነ ገፍቶ መምጣቱ ‹መስተዳደሩ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በተግባር ማሳየት እንዳለበት እንዲያምን አድርጎታል ይላል፡፡


በአርሶ አደር የተያዙ የመኖርያና የእርሻ ይዞታዎች ከእንግዲህ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ በአስቸኳይ እንዲሰጣቸው፤ አርሶ አደሮች ከከተማ ግብርና ባሻገር በይዞታቸው ላይ ከትልልቅ ኢንቨስተሮች ጋር እየተጣመሩ ይዞታቸው ላይ ከፍተኛ ልማት እንዲጀምሩ እንዲደረግ የሥራ መመርያን ይሰጣል፡፡


እነዚህ አርሶ አደሮች በሕግ አግባብ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር እየተደራጁ ወደ ከፍተኛ የከተማ ልማት እንዲገቡም ይበረታታሉ ይላል፡፡ የዚህ መመርያ ዓላማም አርሶ አደሮች የአኗኗር ዘይቤያቸውን እንዲቀይሩም ለከተማዋ ገጽታ መለወጥም ድርሻ እንዲኖራቸው ነው በማለት ያወሳል፡፡ አሁን ይህ መመርያ ለምን እንዳስፈለገ ሰነዱ ጨምሮ ሲያስረዳም፣


‹‹እስከአሁን በነበረው አሰራር አርሶ አደሩ ለግሉ መኖርያ 500 ካሬ መሬት ይሰጠው የነበረ ቢሆንም የተቀረው የእርሻ መሬቱ በተልካሻ የካሳ ክፍያ ይነጠቅብኛል በሚል በሕገ ወጥ መንገድ መሬቱን ለሌሎች ሲያስተላልፍ ቆይቷል፤ ይህን ለሕገ ወጥ ግንባታ በር ከፍቷል›› ይልና ‹‹ይህን ተከትሎም አርሶ አደሩ የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ መምጣቱ ለዚህ አዲስ መመርያ መዘጋጀት አንድ ምክንያት ነው›› ሲል ያስቀምጣል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 33 ንኡስ አንቀጽ 2 መሰረት ነው ይህ አዲስ መመርያ የተዘጋጀው፡፡


በዚህ መመርያ መሰረት በአርሶ አደር የተያዙ በታዎች በከተማ አስተዳደሩ ወሰን ውስጥ አርሶ አደሩ ለመኖርያና ለከተማ ግብርና ሥራዎች እየተጠቀሙበትና እያስተዳደሩት ያለ ማንኛንም መሬት ያጠቃልላል፡፡ የመሬቱ ስፋት ትልቅ መሆን፣ የአንድ አርሶ አደር ይዞታ በጣም በርካታ መሆን በመመርያው ላይ ለውጥ የሚያመጣ አይደለም፡፡ ይህም አርሶ አደሩን ይገባኛል የሚለውን መሬት እንዴትም ሰፊ ቢሆን አስጠብቆ እንዲቆይ ብሎም ከባለሀብቶችና ከአቻ አርሶ አደሮች ጋር በመሆን እንዲያለማውና ወደ ዘላቂ ሚሊዮነርነት እንዲሻጋገር የሚያደርግ ነው፡፡


በዚህ መመርያ መሰረት ለአርሶ አደሮች የሚታደለው የመጠቀሚያ የምስክር ወረቀት ለአርሶ አደር የእርሻ ወይም የግጦሽ ወይም የደን ይዞታዎች የተለያየ የከተማ ግብርና ይዞታዎች የመጠቀም መብት እንዳለው የሚያረጋግጥ ሰነድ ነው፡፡
የዚህ መመርያ ዓላማ በሰነዱ ተደጋግሞ እንደተገለጸው አርሶ አደሩ ከእንግዲህ ይዞታዬ የሚለውን ሰፋፊ መሬት እንዳስጠበቀ እንዲቆይና በግሉ ወይም ከመሰል አርሶአደሮች ጋር እንዲሁም ከከፍተኛ ባለሐብቶች ጋር በይዞታው ላይ የልማት ስራዎችን እየሰራ ዘላቂ ባለሀብት እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡


ይህ መመርያ ተፈጻሚነቱ በአዲስ አበባ ከተማ በአርሶ አደርና በአርሶ አደር ልጆች ለመኖርያና ለግብርና ሥራዎች አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ማናቸውም የመሬት ይዞታዎች ላይ ነው፡፡


አርሶ አደሩ የይዞታ ማረጋገጫ የሚሰጠው ቦታው የሱ ስለመሆኑ የአገራባች ይዞታ ባለቤቶች ሲመሰክሩለትና የአርሶ አደር ኮሚቴ ለዚሁ ምስክርነት ሲሰጥ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ ውስብስብ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሂደቶችም በዚህ መመርያ ተቃለዋል፡፡
አርሶ አደሩ ወይም የአርሶ አደሩ ልጅ የምስክርነት ወረቀት የሚጠይቅበት መሬት የራሱ ይዞታ ስለመሆኑ በወረዳ ደረጃ በኮሚቴ ሲረጋገጥም ማንኛውም የአርሶ አደር ልጅ ነኝ የሚል ለቦታው የይዞታ የምስክር ወረቀት ማግኘት ብቻም ሳይሆን ለመኖርያ ቤት መስሪያ የሚሆን 150 ካሬ መሬት ያገኛል፡፡

የምስክር ወረቀት የተጠየቀበት መሬት አርሶ አደሩ ለልጁ ሰጥቶ ልጁም እየተጠቀመበት መሆኑ በኮሚቴው ከተረጋገጠ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ ሳይጠየቅ ለአርሶ አደሩ ልጅ የምስክርነት ወረቀት ይዘጋጃል፡፡


ይህ በወረዳ ደረጃ የሚዋቀረው ኮሚቴ ነባር አርሶ አደሮች በራሳቸው ከወረዳ ጋር የሚመሰርቱት ኮሚቴ ሲሆን ከዚህ ቀደም በነበሩ ዓመታት በተለይም የቀድሞ ከንቲባ ታከለ ኡማን መምጣት ተከትሎ ይህ በየወረዳው የተዋቀረ ኮሚቴ ለመሬት ቅርምት ቁልፍ ሚና ሲጫወት እንደነበር ይታወሳል፡፡


የታከለ ኡማ አስተዳደር ከተማው ውስጥ ኪስ ቦታዎች እየተቀለሙ እንዲታጠሩና የይገባኛል ጥያቄ እንዲነሳባቸው፣ ከዚያም የአርሶ አደር ልጅ ነኝ በሚል በአርሶ አደር ኮሚቴ በሚሰጥ ምስክርነት ብቻ በርከታ ቦታዎች በሕገ ወጥ መንገድ ታጥረው እንዲቸበቸቡ በር እንደከፈተም ይነገራል፡፡


አሁንም በዚሁ አሰራር የምሰክርነት ወረቀት እንዲታደል የሚያዘው መመርያ ካርታ የተጠየቀበት መሬት ከአርሶ አደር ቤተሰብ በውርስ የተገኘ ከሆነም ለመሬቱ የይዞታ የምስክርነት ወረቀት ወዲያውኑ እንዲሰጥ ያዛል፡፡ አርሶ አደሩ ስለይዞታው የሚያስረዱ ተጓዳኝ ሰነዶች ማለት የግብርና ደረሰኝ፣ የውርስ ስጦታ መብራት ውሃና ስልክ ያስቀጠለበት ተቀራራቢ ሰነዶችም በራሳቸው በቂ ሆነው የይዞታ ምስክር ወረቀት ያሰጣሉ ይላል፡፡


መሬቱ ወይም ቦታው የምስክር ጠያቂው መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ ለግብርና መጠቀሚያ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ለመስጠት የቦታ ብዛትም ሆነ ስፋት ገደብ እንደሌለውም አዲሱ መመርያ በማያሻማ ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡
በዚህ መመርያ አርሶ አደሩ የኔ ነው የሚለው ቦታ የፕላን ታቀርኖ ላይ ያረፈ እንኳ ቢሆን የአርሶ አደር ቦታዎችም አገልግሎት አይከለከሉም፡፡ የፕላን ተቃርኖ ማለት ቦታው ለመንገድና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ወይም ለሕዝባዊ አገልግሎትና ሌሎች የተለዩ አገልግቶች በፕላን የተቀመጠ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡

በዚህ መመርያ መሰረት የአርሶ አደሩ ልጅ ለብቻው የግብርና መሬት ካለውም ምንም ያህል ቦታው ሰፊ ቢሆን የምስክር ወረቀት ይሰጠዋል፡፡ ምናባት ከዚህ ቀደም ካሳ ሳይከፈል የአርሶ አደር መሬቱ የመሬት ባንክ ውስጥ ገብቶ ከነበረም በክፍለ ከተማ መሬት ባንክና ማስተላልፍ ጽሕፈት ቤት በኩል የማጣራት ሥራ ተሰርቶ መሬቱ ከመሬት ባንክ እንዲወጣ ተደርጎ ለአርሶ አደሩና ለአርሶ አደር ልጆች እንዲሰጠ ይደረጋል፡፡

በኮንዶሚንየም አካባቢ የሚገኙ መሬቶችም ቢሆን የአርሶ አደር ይዞታዎች ከሆኑ ወይም እንደነበሩ ከተረጋገጠ ከጋራ መኖርያ ቤቶች ጋር እንዳይደራረቡ ተደርጎ አገልግሎት ይሰጣቸው ይላል አዲሱ መመርያ፡፡
አርሶ አደሩ የምስክር ወረቀቱን ካገኘ በኋላ ቦታውን ለፈቀደው የግብርና አገልግሎት ከማዋል ጀምሮ የይዞታ መብቱን የማልማትና የማውረስ ሙሉ መብትን ይቀዳጃል፡፡


ይህ ብቻም አይደለም፣ የአርሶ አደሩ ቤት በ1997 ለተነሳው መስመር ካርታ ላይ ቢታይም ባይታይም ለመኖርያ በ500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በነባር ይዞታ ስሪት የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ይሰጠዋል፡፡ ለአርሶ አደር ልጆችና አርሶ አደሩ ጋር ለተጠጉ ማናቸውም የቤተሰብ አባላትም 150ካሬ መሬቶች ይታደላሉ፡፡


በመመርያው መሰረት ዕድሜያቸው 19 እና ከዚያ በላይ ሆነው የአርሶ አደሩን ገቢ በመጋራት ከአርሶ አደሩ ጋር አብረው ለሚኖሩ የአርሶ አደር ልጆች ይዞታው ላይ ቤት ኖረም አልኖረም 150 ካሬ ይሰጣቸዋል፡፡


የግብርና እርሻ መሬቱን ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ለከፍተኛ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ማዋል ሲፈልግ ከከንቲባው ወይም ከንቲባው ከሚወክሉት ሰው ብቻ ፈቃድ እያገኘ እንዲስተናገድ ልዩ መብትንም ያጎናጽፋል መመርያው፡፡ ሆኖም የከተማ ግብርና መጠቀሚያ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የተሰጠበትን ይዞታ ገበሬው መብቱን በማናቸውም ሁኔታ ሕግ ከሚፈቅደው አግባብ ለልጆቹ ከማስተላለፍ በስተቀር በሽያጭ ወይም በስጦታ ለሌላ ሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ አይፈቀድለትም፡፡


አርሶ አደሮቹ 5ሺ እና ከዚያ በላይ ካሬ ቦታ የይዞታ ማረጋገጫ ሲሰጣቸው ግዙፍ የገበያ ሕንጻዎች፣ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎችና ባለ5 ኮከብና ከዚያ በላይ ሆቴሎችን እንዲገነቡ ሁኔታዎች ይመቻቹላቸዋል፡፡ ይህን እንዲያደርጉ የሚፈቀድላቸው ግን መሀል ከተማ ይዞታ ካላቸው 5ሺ ካሬ የይዞታ ማረጋገጫ ሲያገኙ ከተማ ዳር ደግሞ ከ5ሺ እስከ 10ሺ ካሬ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሲያገኙ ብቻ ነው፡፡


የቦታ ስፋት ስታንዳርድ ባልወጣላቸው የቦታ ይዞታዎች ላይ አርሶ አደሮች የልማት ጥያቄ ሲቀርቡ በቅድሚያ በፕላንና ልማት ኮሚሽን በኩል ስታንዳርድ እንዲወጣላቸውና ከዚያም አርሶ አደሮቹ እንዲሳተፉበት ይደረጋል፡፡
መመርያው አርሶ አደሩ ለእርሻና ለመኖርያ ሲጠቀምበት የነበረን ቦታ በራሱና ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ለማልማት ሲያስብ ቦታው ወዲያውኑ ከሊዝ ነጻ ሆኖ የግንባታ ፈቃድ ይሰጠዋል ይላል፡፡


አርሶ አደሩ በራሱ ይዞታ ላይ ከሌሎች ኢንቨስተሮች ጋር የማልማት ሐሳብ ሲኖረው ደግሞ የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት በሚያስጠብቅ መልኩ ታይቶ የሚስተናገድበት ሁኔታ ይመቻቻል ይላል፡፡


መመርያው ወደ ክፍለ ከተሞች ሊሰራጭ ገና በዝግጀት ላይ ቢሆንም ከጥር 2፣ 2013 ጀምሮ የጸና እንደሆነ ያትታል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ የጎንዮሽ መለጠጥ ጋር ተያይዞ ያለ በቂ ካሳ የእርሻና የመኖርያ ቦታቸው ተወስዶባቸዋል የሚባሉ አርሶ አደሮች በተለያዩ ጊዝያት የኮንዶሚንየም፣ የገንዘብ፣ የመሬትና የልዩ ልማት ቦታ ተጠቃሚነትን ሲያገኙ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]