Benshangul

  • መከላከያ ሰራዊት ዛሬ ረፋዱን ወደ ስፍራው ከደረሰ በኋላ ግጭቱ ረግቧል

ዋዜማ ራዲዮ፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ አሶሳ ስኔ 18  ምሽት ላይ የተቀሰቀሰ ብሄር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተባብሶ ለሰው ህይወት መጥፋትና መቁሰል እንዲሁም መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

ከኦሶሳ ሆስፒታል ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን የስምንት ስዎች ህይወት ሲያልፍ በርካታ ስዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፣ በሆስፒታል እየተረዱ ነው።
“የበርታ ማህበረሰብ አባላት የሆኑ ወጣቶች ከጫት ተራ ጀምረው መሀል ከተማ ድረስ ሰው እየደበደቡ ንብረት ሲዘርፉ የክልሉ ፖሊስ ምንም አይነት መከላከል ሳያደርግልን ህዝቡ ወደ በርታ ሲሄድ ፖሊሶች ተኩሰው 3 ሰው በጥይት መተዋል” ሲል የከተማው ነዋሪ ተናግሩዋል።

“ተድበስቦ ነው እንጂ ከበፊትም በርታዎች “ሀበሻ ይውጣ” እያሉ ትንኮሳ ያደርጉ ነበር”  ነዋሪዎቹ እንደሚያስረዱት።
ባለፈው ሳምንት የፊት ጭንብል የለበሱ ሰዎች ከተማ ውስጥ ህብረተሰቡን ሲደበድቡ ነበር ብለዋል ነዋሪዎች፡፡

መከላከያ ሰራዊት ዛሬ ረፋዱን ወደ ስፍራው ከደረሰ በኋላ ግጭቱ ረግቧል ህብረተሰቡንም አረጋግቷል ፡፡
የአሶሳ ማዘጋጀ ሀላፊ አቶ ቶፊቅ አብዱልቀዩም “መጀመሪያ ጠቡ የተነሳው በወጣቶች መሀከል ነው በግጭቱ 3 ሰዎች ሲሞቱ 1 ሰው ላይ ከፍተኛ ጉዳት 4 ሰዎች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን 40 ሰዎች በቁጥጥር ስር ሆነው ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ነው” ሲሉ ነግረውናል፡፡

” አሁኑ ሰአት የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ወጣቱን እያወያዩ ነው” ብለዋል አቶ ቶፊቅ፡፡

የክልሉ መንግስት ሀላፊዎች በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። የክልሉ የኮምኒኬሽን ቢሮ ጉዳዩ በከፍተኛ ሀላፊዎች መግለጫ ይሰጥበታል ከማለት ውጪ ምላሽ ለመስጠት ሳይፈቅድ ቀርቷል።