Commercial Bank of Ethiopia-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሰራተኞ የታዘዙ ቼኮች እንዳይመነዘሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቅርጫፎቹ በደብዳቤ ማሳወቁን ዋዜማ ራዲዮ ካገኘችው የደብዳቤው ቅጂ ተረድታለች።

ንግድ ባንክ ትእዛዙን ያስተላለፈው የፌዴራል መንግስት በተናጠል አውጄዋለሁ ያለውን የተኩስ አቁም ተከትሎ መቀመጫውን አዲስ አበባ ካደረገው የትግራይ ክልል  ጊዜያዊ አስተዳደር ደረሰኝ ባለው ደብዳቤ ላይ ተመስርቶ እንደሆነ ገልጿል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ” ሽብርተኛ” ድርጅትነት የተፈረጀው ሕወሓት ከፌዴራል መንግስት ጋር የገጠመውን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ያሉ የባንክ ሂሳቦች እንደታገዱ ደብዳቤው አስታውሷል።

የፌዴራል መንግስት ጦር መቀሌን ጨምሮ መላው የትግራይ ክልል ለወራት ከተቆጣጠረ በኋላ ክልሉን ለቆ ሲወጣ ክልሉን ሲያስተዳድሩ የቆዩት የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት ወደ አዲሰ አበባ እንደተሰደዱ ይታወሳል።

በትግራይ ያሉ የባንክ ሂሳቦች የታገዱ ቢሆንም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ከክልሉ የተለያዩ የባንክ ሂሳቦች (ሙያተኞቹ B እና Z አካውንቶች ከሚሏቸው) ወጭ እንዲሆን ያዘዙት ቼክ ስላለ ይሄንንም ቼክ በተለያዩ መንገዶች ለመመንዘር ጥረት ሊደረግ ስለሚችል ሀሉም የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ጥንቃቄን እንዲያደርጉና ቼኩን እንዳይመነዝሩ ከንግድ ባንኩ ፕሬዝዳንት ትእዛዝ እንደተላለፈላቸው ደብዳቤው ገልጿል።

የታዘዙ ቼኮችን ለመመንዘር የሚደረጉ ጥረቶች ካሉ የንግድ ባንኩ ሰራተኞች ለሚመለከተው አካል የሚያሳውቁባቸው ስልክ ቁጥሮችም በደብዳቤው ተዘርዝረዋል። እግዱ የተላለፈበት ትክክለኛ ምክንያት በደብዳቤው ላይ አልተገለጸም።

 መንግስት የሕወሓት የገንዘብ ምንጭ ይሆናሉ ብሎ ባሰባቸው የገንዘብ እንቅስቃሴዎች ላይ ተከታታይ እርምጃን መውሰዱ የሚታወቅ ነው። ንግድ ባንኮች በማስያዣ ብድር መስጠት እንዲያቆሙ ፣ በህገወጥ ሀዋላ ላይ መወሰድ የጀመረው አሰሳ ፣ እንዲሁም የንብረት በተለይ የቤት ሽያጭ ላይ የተላለፉት እገዳዎች የዚሁ አካል መሆናቸው ይታወቃል። [ዋዜማ ራዲዮ]