ዋዜማ ራዲዮ-አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ግብር በመሰወር ተጠርጥረው ላለፉት አምስት ዓመታት በእስር ላይ የነበሩት ከፍተኛ ባለሐብቱ አቶ ዮሐንስ ሲሳይ ትናንት ከቤተሰብ ጋር መቀላቀላቸው ተሰምቷል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ግለሰቡን የከሰሳቸው የገቢ ግብር፣ የቫት እና የዊዝሆልዲንግ ግብር በቤተዘመድ በተቋቋመ  ኩባንያ ጋር የአሻጥር ንግድ በመነገድ ሰውረዋል በሚል ነበር፡፡ ለእስር የተዳረጉትም በመጋቢት 2004 ዓ. ም ነበር፡፡ የክሱ የገንዘብ መጠን በገቢዎችና ጉምሩክ የክስ ታሪክ ትልቁ የሚባል ነው፡፡ 

የየሱ ኩባንያ 93 በመቶ ባለቤት የኾኑት አቶ ዮሐንስ ገቢን በመሰወር በተጠረጠሩበት ወቅት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ኢሳያስ ተክሉም በተመሳሳይ ሁኔታ በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር፡፡ አቶ ኢሳያስ አሁንም እስር ቤት ናቸው፡፡

ከአቶ ዮሐንስ እስር ጋር አብረው በቁጥጥር ሥር ዉለው የነበሩት የቤተሰባቸው አባል ወይዘሮ ሂሩት እንዳለ፣ አቶ አበራ መንግሥቱ፣ ጀምበር ተካ፣ አቶ ኃይሉ አሰፋ በተለያየ ጊዜ የዋስ መብት ተከብሮላቸው ከእስር መለቀቃቸው ይታወቃል፡፡

ወይዘሮ ሂሩት የአቶ ዮሐንስ ሲሳይ የአጎት ልጅ ስትሆን፣ አቶ ኃይሉ አሰፋ ደግሞ ሸበል ፒኤልሲ የተሰኘ የየሱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ካምፓኒ እህት ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡ ሸበል በ10 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን የአቶ ዮሐንስ አባት አቶ ሲሳይ ሞላ እና የአቶ ዮሐንስ ወንድም አቶ ያሬድ ሲሳይ በባለቤትነት ሲያስተዳድሩት ቆይተዋል፡፡

አቶ ዮሐንስና ቤተሰቦቹ ከመንግሥት ሰውረውታል ተብሎ የሚገመተው የገንዘብ መጠን ክሱ በተመሰረተበት ወቅት 795 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን በክስ ሂደት ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ተጠግቷል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ አቃቢ ሕጎች ይህ ከፍተኛ ገንዘብ በልዩ የንግድ አሻጥር በአቶ ዮሐንስ ሲሳይ ተሰውሯል ሲሉ ላለፉት ዓመታት ተከራክረው ቆይተዋል፡፡ 

የሱ ኩባንያ በግማሽ ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል በአቶ ዮሐንስ ሲሳይና በወንድማቸው አቶ ያሬድ ሲሳይ የተመዘገበ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ሲመሰረት ቆርቆሮ በማምረት በአገሪቱ ፈር ቀዳጅ ከሆኑ ድርጅቶች አንዱ ነበር፡፡ ኾኖም በወቅቱ በነበረው የኃይል አቅርቦት እጥረት ፋብሪካው ከሙሉ አቅሙ 30 በመቶ ብቻ ለማምረት ተገዶ እንደነበር ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ የቆርቆሮ ምርት ከፍተኛ የገበያ ድርሻ እንዳለው የሚነገረው የየሱ  ፋብሪካ  ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተገኘ ብድር ነበር የተቋቋመው፡፡ ፋብሪካው የራሱ የኃይል ንኡስ መቆጣጠሪያ ተገንብቶለት በገላን  ከተማ ይገኛል፡፡ እስከአሁንም በቆርቆሮ ምርት ከፍተኛ የሚባል የገበያ ድርሻን እንደያዘ መቀጠል ችሏል፣ የጥራትና ደረጃ ጥያቄ ቢነሳበትም፡፡

በቀን አራት መቶ ቶን ቆርቆሮ ያመርታል የተባለው ይህ ኩባንያ ለረዥም ጊዜ በኪሳራ ላይ እንደሚገኝ ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሪፖርት ሲያደርግ እንደቆየ አቃቤ ሕግ ያቀረበው የሰነድ መረጃ ያስረዳል፡፡፡፡

ከ3 ዓመት እስርና የፍርድ ቤት ክርክር በኋላ መጋቢት 28፣ 2007 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት አቃቢ ሕግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኋላ አቶ ዮሐንስን እንዲከላከሉ በይኖባቸው ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል የመከላከያ ምስክር በማቅረብ ዘለግ ያሉ ቀጠሮዎች ሲሰጧቸው ቆይቷል፡፡

ግንቦት 28፣ 2004 ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል አቶ ዮሐንስ በሳምንት 2 ጊዜ ከማረሚያ ቤት እየወጡ ንብረታቸውን  እንዲያስተዳድሩም ተወስኖላቸው ነበር፡፡

የአቶ ዮሐንስን ጉዳይ ላለፉት አምስት አመታት ሲመለከቱ የቆዩት በርካታ ዳኞች ሲሆኑ ከነዚህም ዉስጥ ዳኛ ታሪኳ ተበጀ፣ ዳኛ ኑረዲን ከድርና ዳኛ ከድር መሐመድ ይገኙበታል፡፡ በአንድ ወቅት አቶ ዮሐንስ ኩላሊቴን ታምሜያለሁ ቆሜ መከራከር አልችልም በሚል ለዳኞች የሕክምና ጥያቄን አቅርበው ነበር፡፡  ጠበቆቻቸውም ደንበኛቸው መቆም ሁሉ እንዳቃጣቸውና በግል ሆስፒታል እንዲታከሙ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ አቃቤ ሕጎች በበኩላቸው ተጠርጣሪው ግለሰብ ከፖሊስ ሆስፒታል ሌላ የትኛውም የግል ሆስፒታል መጎብኘት እንዳይፈቀድላቸው ተሟግተው ነበር፡፡ ያም ኾኖ ተጠርጣሪው አቶ ዮሐንስ ቀን ቀን በአጃቢ ሥራ ቦታቸው ይዉሉ እንደነበር ይነገራል፡፡

የአቶ ዮሐንስ ጠበቃ ኾነው የቆዩት አቶ ደሳለኝ ዓለሙ የቀድሞ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ የዋዜማ ምንጮች አቶ ዮሐንስ ትናንት ከቤተባቸው ጋር መቀላቀላቸውን ማረጋገጥ ቢችሉም ፍርድ ቤት ግለሰቡን በነጻ ስለማሰናበት አለማሰናበቱ ያገኙት መረጃ የለም፡፡

አቶ ዮሐንስ ሲሳይ በግለሰብ ደረጃ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከፍተኛውን የገንዘብ መጠን ያበረከቱ ኢትዮጵያዊ ባለሐብት ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ስለ ግለሰቡ እስር በዝርዝር የቀረበ ዘገባ እዚህ ማስፈንጠሪያ ላይ ይመልከቱ-http://wazemaradio.com/%E1%8B%A8%E1%8D%8A%E1%8A%95%E1%8D%8A%E1%8A%94-%E1%8B%B0%E1%88%8B%E1%88%8B-%E1%8B%A8%E1%8A%A8%E1%88%AD%E1%89%B8%E1%88%8C-%E1%8C%8E%E1%89%A0%E1%8B%9B%E1%8B%9D%E1%89%B5/