ዋዜማ ራዲዮ- የትግራይ ክልል ታጣቂ ኀይል በክልሉ ውስጥ በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱንና ሠራዊቱ በኮማንድ ፖስት እየተመራ “ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ” መታዘዙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፌስ ቡክ ገጻቸው ገለጹ።

“የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል። ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል።” በማለት የፖለቲካ ጡዘቱ ወደ ወታደራዊ ግጭት መለወጡን አረጋግጠዋል።

በትግራይ ክልል፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ጎንደር፣ ራያ፣ ወልቃይት ጠገዴ አካባቢዎች የስልክ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ተሰምቷል። ስልክም በትግራይ እንደተቋረጠ ታውቋል።

የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት የሚመራው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተካሮ ሰሞኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል “ራሳችንን ለመከላከል ተዘጋጅተናል” የሚል መግለጫ ሰጥተው ነበር። የክልሉ ልዩ ኀይልና የጸጥታ ክንፎች ዝግጅትና እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው የሚሉ መረጃዎችም ሲደመጡ ከርመዋል።


ባለፈው ሳምንት ትግራይ ለሚገኘው የሰሜን እዝ የተመደቡትን አዲስ ምክትል አዛዥ “ለሹመቱ እውቅና አንሰጥም” በሚል ከመቀሌ አውሮፕላን ጣቢያ እንዲመለሱ መደረጉ ይታወሳል። ይህ እርምጃ በሠራዊቱ አመራሮች አካባቢ ቁጣ መቀስቀሱ ተሰምቶ ነበር።
በፌደራል መንግሥቱ በኩል ህወሃትን በተመለከት ሲንጸባረቅ የነበረው አቋም እሑድ ዕለት በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመውን በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ግድያ ተከትሎ እጅግ ተካሮ ማክሰኞ ዕለት በተደረገው የፓርላማው ስብሰባ ህወሃት በአሸባሪነት እንዲፈረጅ እስከመጠየቅ የደረሰ ንግግር ተደምጦ ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ሚዲያ መግለጫ እኩለ ሌሊት ካለፈ በኋላ የተለጠፈ ቢሆንም ተደረገ የተባለው ካምፕ የመውረርና የመዝረፍ ሙከራ በትክክል በስንት ሰዓት እንደተጀመረ የታወቀ ነገር የለም። ሆኖም፣ ከእርሳቸው መግለጫ መውጣት በፊት መቀሌ ውስጥ የተኩስ ልውውጥ መደመጡን የሚጠቅሱ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ታይተው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትሩ መግለጫቸውን ያሳረጉት “የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ እንዲከታተል፣ በየአካባቢው ሊከሠቱ የሚችሉ ትንኮሳዎች በንቃት እንዲቃኝና ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንዲቆም” በማለት ነው። ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ የህወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ከሰዓታት በፊት “ንረጋጋዕ ኣሓትን ኣሕዋትን!” (እንረጋጋ) ካሉት በቀር የተሰጠ መረጃም ሆነ መግለጫ የለም። ከፌደራል መንግሥቱ በኩልም ከጠ/ሚሩ የጽሑፍ መግለጫ ሌላ የተሰማ ነገር የለም። [ዋዜማ ራዲዮ]